የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ስለ ኢትዮጵያ ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, shabait
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በ34ኛው የኤርትራ ነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጠንካራ ትችት ሰነዘሩ።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በርካታ ኤርትራውያን በተገኙበት ስታዲየም እና በአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው በዚህ ንግግራቸው "የውጭ ኃይሎች በብልፅግና ወኪላቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ያወጁት ጦርነት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ ያሳያል" ብለዋል።
የኤርትራ ጦር ደም አፋሳሽ በሆነው የትግራይ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ፕሬዝደንቱ በዚህ ንግግራቸው "የውጪ ኃይሎች" ያሏቸው እነማን እንደሆኑ በስም አልጠቀሱም።
ኤርትራ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት ውስጥ ሠራዊታቸውን ከኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ጎን አሰልፈው ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ የጦርነቱ ማብቃትን ተከትሎ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቀዛቀዙ ይታወቃል።
"ሊያቀርቡ የሚፈልጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ" ነው በማለት ከስሰዋል።
ይህንን ለማሳካት ፕሬዚደንት ኢሳያስ የውጭ ኃይሎች ባሏቸው እገዛ የኢትዮጵያ መንግሥት "የጦር መሳሪያ ግዢ እና የወታደራዊ ዝግጅት" ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ፕሬዝደንቱ የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት በኢትዯጵያ ለተካሄደው ለውጥ "ድጋፍ በማድረጉ እና ድንገት በተፈጠረ ለውጥ ምክንያት አይቆጩም" ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰማንያ ዓመታት "በተሳሳተ ፖሊሲዎች እና በዋሺንግተን አጋፋሪዎቻቸው" ምክንያት የተከሰተው "የታወቀ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ እና እርቅ ከፈጠሩ ወዲህ የኢትዮጵያን መንግሥት ላይ ጠንካራ ትችት ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
ላለፉት ሁለት ትውልዶች በኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት ግንባታው ዕድል መጨናገፉን በንግግራቸው የጠቀሱት ፕሬዝደንት ኢሳያስ፣ ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ኢትዮጵያ ወደ ብሔር ፖለቲካ ጽንፍ ማምራቷን አመልክተዋል።
አክለውም በኢትዮጵያ ታይተው የነበሩ ለውጦችን "ተስፋ ሰጪ ሕዝባዊ ምኞቶች" ሲሉ ገልጸው፤ ይህም "የውጭ ኃይሎችን ያስደነገጠ ነበር" ሲሉ ገልጸውታል።
ከከባድ የድንበር ጦርነት በኋላ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በፍጥጫ ላይ ቆይተው የነበሩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ያሻሻሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ነው።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየተሻሻለ ባለበት ጊዜ በተቀሰቀሰው የትግራይ ጦርነት ውስጥ የሁለቱ አገራት ሠራዊቶች በአንድ ተሰልፈው የህወሓት ኃይሎችን ሲወጉ ቆይተዋል።
ጦርነቱ በአሜሪካ እና በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት በተደረጉ ድርድሮች መቋጫ ካገኘ በኋላ የጎረቤት አገራቱ ግንኙነት ከመሻከር አልፎ ወደ ፍጥጫ እያመራ ነው።
በተለይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቶ ይፋ ከሆነ በኋላ በኤርትራ በኩል ስጋት ተፈጥሯል። ይህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር ትብብር በመፍጠር ውጥረቱ ተባብሷል።
በተጨማሪም በይፋ ባይነገርም ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ የምትከሰስ ሲሆን፣ በተመሳሳይም የኤርትራ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት እስከ መክፈት ደርሰዋል።
የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ያሻከረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ሊኖረን ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለባሕር በር እና ስለወደብ ያደረጉት ንግግር እና ያሳዩት ፍላጎት የኤርትራ ባለሥልጣናትን አላስደሰተም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትን በተመለከተ "የቀይ ባሕርን ጉዳይ ሳናነሳ በሰላም ቆይተናል እና አሁን ለምን ዝም አንልም? ከኤርትራ ጋር እንዳንጋጭ ቢቀርብንስ? ከጂቡቲ ጋር ብንጋጭስ የሚል ስጋት ያለባቸው ሰዎች አሉ" ብለው ነበር።
ለዚህ ጥያቄ መነሳት እንደ ምክንያት የጠቀሱት እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት የባሕር መተላለፊያ ስለሌለው "የመልክዓ ምድር እስረኛ" ሆኖ መቀጠሉን አመልክተው ነበር።
ላለፉት 34 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝደንት ኢሳያሳ "በብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የተከሰቱትን በርካታ እና ተደጋጋሚ አደጋዎች ተከትሎ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት የታቀደው 'ለውጥ' በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ እና በሌሎች አጎራባች አገሮችም የፈጠረው የደስታ ስሜት እና ብሩህ ተስፋ በእውነቱ ትውስታችን ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን ተስፋ ሰጪ በሆኑት ዕድሎች የተናደዱ የውጭ ኃይሎች "ሥራ አልፈቱም" ብለዋል።
"ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያወጇቸው ጦርነቶች በብልጽግና (አዲሱ ተተኪያቸው) ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው።"
የዚህ መሸፈኛው ብዙ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ አጀንዳዎቻቸው እና አስቀድመው ያቀዱት የታወቀ መሆኑን በደፈናው ተናግረዋል።
"የውሃን ጉዳይ ያነሳሉ፤ አባይ እና ቀይ ባሕርን፣ የባሕር በር ማግኘትን፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክለውን የኦሮሙማን አጀንዳ፣ የኩሽንና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬቱን ለሚያመቻቸው ሴራ መጠቀሚያ ማድረግ፣ የብሔር ጦርነትን በሁሉም ቦታዎች ማቀጣጠል" ሲሉ ዘርዝረዋል።
"እነዚህ የታቀዱ ጦርነቶችን ለማስጀመር የጦር መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጅዎችን ለማግኘት የሚደረገው የግዢ ጥድፊያ፣ ተጓዳኝ ፉከራዎች እና ወታደራዊ ዝግጅት ሁሉም ያወቀው እና የመዘገበው ነው" ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በዚሁ ንግግራቸው ላይ በኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ እየተፈፀመ ያለው ግልጽ እና "ስውር" የማፍረስ ሴራ የታወቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ ታይቶ የነበረው ተስፋ ሰጪ ዕድል መክሸፉን ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራሳቸውን ምርጫ ወስደዋል" ያሉት ፕሬዝደንቱ "ተቃውሟቸውን ለማጠናከር እየተዘጋጁ ነው" ብለዋል።
"የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት ለታሰበው ተሃድሶ/ለውጥ . . . ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረጉ እና ድንገት በተፈጠረ ለውጥ ምክንያት አይቆጩም" ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የወደብ ባለቤትነት የመሆን እና የመጠቀም መብት እንዳላት መናገራቸውን ተከትሎ ኤርትራን፣ ሶማሊያ እና የግብፅ መንግሥታትን አስቆጥቷል።
ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት በፍጥጫ ውስጥ ከቆዩ በኋላ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝተዋል።
በተቺዎቻቸው ከአገር ውስጥ ጉዳይ ይልቅ በሌሎች አገራት ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ የሚባሉት ፕሬዝደንት ኢሳያስ በነጻነት በዓል ንግግራቸው "ነጻነታችንን ማጠናከር አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ጠንካራ የመንግሥት ቁጥጥር በሚደረግባት ኤርትራ ከፍተኛ የመብት ጥሰት እና ጭቆና ያላባት አገር መሆኗን የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በየጊዜው በሚያወጧቸው መግለጫዎች ላይ ይከስሳሉ።
ከኢትዮጵያ ነጻ ከወጣች በኋላ አንድም ጊዜ ምርጫ አካሂዳ የማታውቀው ኤርትራ ሕግ መንግሥት እና አገራዊ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የላትም።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በንግግራቸው በሱዳን ስላላው ግጭት የተናገሩ ሲሆን፣ በውጭ ኃይሎች ያለውን ጣልቃ ገብነት ተችተዋል።
ኤርትራ በጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን ለሚመራውን ወታደራዊ መንግሥት ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።
በኤርትራ እንዲሁም የተለያዩ የውጭ አገራት የተከበረው 34ኛው የኤርትራ የነጻነት ቀን በወታደራዊ እና በኪነ ጥበብ የታጀበ ነበር።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል።
34 ዓመት በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝደንት ኢሳያስ በንግግራቸው ስለ ዓለም አቀፉ ሁኔታ፣ ስለ ቀጠናዊ ጉዳዮች እና ስለ ጎረቤት አገራት በዝርዝር ተናግረዋል።












