"ወንዳወንድ ለመሆን" በሚል የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን እየተቀላቀሉ ያሉት አሜሪካዊያን ወጣቶች

"ብዙ ሰዎች ይጠይቁኛል። አባ ሙሴ፤ እንዴት አድርጌ ነው ወንድነቴን ከፍ ማድረግ የምችለው? ይሉኛል።
በአንድ የዩቲዩብ ቪድዮ ቄሱ እንዴት ፈርጣማ እና ልብ ደንዳና ወንድ መሆን እንደሚቻል ይሰብካሉ።
'ቃሪያ' ሱሪ ማድረግ፣ እግርን አጣምሮ መቀመጥ፣ ካውያ መጠቀም፣ መቀንደብን ጨምሮ ሾርባ መመገብ ሴታዊ ባህርይ ናቸው ይላሉ።
አባ ሙሴ ማክፈርሰን የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ ሄቪ ሜታል በተሰኘው ሙዚቃ ታጅበው ክብደት ሲያነሱ የሚያሳይ ቪድዮ ዩቲዩብ ላይ ይገኛል።
በአንድ ወቅት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነበሩ። የቤት ጣራ ጥገና ሥራም ሠርተዋል። አሁን ግን በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ጆርጅታውን ከተማ በሚገኘው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቄስ ሆነው ያገለግላሉ።
ይህ ቤተክርስትያን ሞስኮው የምትገኘው ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ክንፍ ሲሆን ከሩሲያ ውጭ የሚገኙ የሩሲያ አብያተ-ክርስትያናት አካል ነው።
ዋና መቀመጫውን ኒው ዮርክ ግዛት ያደረገው ከሩሲያ ውጭ የሚገኙ የሩሲያ አብያተ-ክርስትያናት ተቋም በአሜሪካ እየተስፋፋ ይገኛል። ለዚህም አብይ ምክንያቱ በርካታ አዳዲስ ተከታዮች ማፍራቱ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ አባ ሙሴ 75 አዳዲስ ምዕመናን አጥምቀዋል።
"እኔና ሚስቴ ከ20 ዓመታት በፊት እምነቱን ስንቀበል ኦርቶዶክስ በሚስጥር ተደብቃ የቆየች ናት ብለን ነበር። ምክንያቱም ሰዎች ስለቤተክርስትያኗ ብዙ እውቀት የላቸውም" ይላሉ።
"ነገር ግን ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የተከታዮቻችን ብዛት በሦስት እጥፍ ጨምሯል።"

በሰንበት ፕሮግራም ወቅት በርካታ በ20ዎቹ እና 30ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ይታደማሉ። ይህች ጥንታዊት ቤተክርስትያን በዘመናዊቷ አሜሪካ በርካታ ወጣቶችን መሳቡ ብዙዎችን አስደንቋል።
የሶፍትዌር ኢንጂነር የሆነው ቴዎዶር የሚወደው ሥራ እና የሚያፈቅራት ሚስት ብትኖረውም ሁሌም ውስጡ ባዶነት ይሰማው እንደነበር ይናገራል።
እሱ እንደሚያምነው ማኅበረሰቡ ወንዶች ላይ የሚያደርሰው "ጫና" ከፍተኛ ነው። ወንዶች የቤቱ የገቢ ምንጭ ሆነው የቤት እመቤት ለሆኑ ሚስቶች ማቅረብ መፈለጋቸው ሊያስወቅሳቸው አይገባም ሲል ይከራከራል።
"ይህ በጣም መርዛማ አስተሳሰብ ነው እንባላለን። እኔ ልንወቀስ ይገባል ብዬ አላምንም" ይላል ቴዎዶር።
አብዛኛዎቹ ምዕመናን ልጆቻቸውን ቤት ውስጥ ነው የሚያስተምሩት። ሚስቶች ከሥራቸው ይልቅ ቤታቸውን ሊያስቀድሙ ይገባል ብለው ያምናሉ።
አባ ዮሐንስ ዊትፈርድ ሂዩስተን የሚገኘው የሩሲያ ቤተክርስትያን ቄስ ናቸው። ልጆችን ቤት ውስጥ ማስተማር ኃይማኖታዊ ሥርዓት እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ "ልጆችንም ይጠብቃል፤ ፆታ መቀየርን፤ አሊያም 57 የፆታ ዓይነቶችን ከመዘርዘር" ይታደጋል ይላሉ።
ከአሜሪካ ኢቫንጀሊካል አብያተክርስትያናት አማኞች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የኦርቶዶክስ ምዕመናን ቁጥር ጥቂት የሚባል ነው። ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር 1 በመቶ ገደማ ነው።
ምሥራቃዊው የኦርቶዶክስ እምነት በሩሲያ፣ ዩክሬን በምሥራቅ አውሮፓ እና ግሪክ አማኞች አሉት። ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ተከታዮች አሉት።
በአውሮፓውያኑ 1917 ከሩሲያ በሸሹ የቤተክርስትያን አገልጋዮች የተቋቋመው ከሩሲያ ውጭ የሚገኘው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አሜሪካ ከሚገኙ ቤተ-እምነቶች ወግ አጥባቂው ተደርጎ ይቆጠራል።
በተለይ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሞስኮው ጋር የተሻለ ግንኙነት ለማድረግ መሞከራቸውን ተከትሎ ቤተክርስትያኑ ተደማጭነት እያገኘ መጥቷል።
እስካሁን ምን ያክል ተከታዮች እንዳፈራ ግልፅ ባይሆንም ፒው ሪሰርች ማዕከል እንደሚለው ከ2007 ጀምሮ ባለፈው ጊዜ የወንድ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አማኞች ቁጥር ከ46 ወደ 64 በመቶ አድጓል።
በቅርቡ እምነታቸውን ከቀየሩ 773 አማኞች አብዛኛዎቹ ወንዶች ናቸው።
የምሥራቃዊው ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ላይ ጥናት የሠሩት ፕሮፌሰር ስኮት ኬንዎርዚ በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ የአዳዲስ አማኞች ቁጥር እየጨመረ ነው ይላሉ።
ለአዳዲስ ተከታዮች መጨመር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለ ማኅበራዊ ሚድያ ነው።
ቄስ ሙሴ በማኅበራዊ ሚድያ በርካታ ተከታዮች አሏቸው። ስድስተኛ ልጃቸውን እየተጠባበቁ እንደሆነ የሚያሳይ ምስል በኢንስታግራም ለጥፈው ከ6ሺህ በላይ 'ላይክ' አግኝተዋል።
በኦርቶዶክስ አማኞች የሚለቀቁ በርካታ ፖድካስቶች እና ቪድዮዎች በተለይ ወንዶች እምነቱን እንዲቀላቀሉ እየገፋፉ ነው።
አባ ሙሴ ጌታ ማገልገለግ የሚቻለው በሁለት መንገድ ነው ሲሉ ተከታዮቻቸውን ይሰብካሉ።
አንደኛው መነኩሴ አሊያም መነኩሲት መሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትዳር መመሥረት ነው። ሁለተኛውን መንገድ የሚከተሉ የወሊድ መቆጣጠር መጠቀም እንዲያቆሙ እና የቻሉትን ያህል ልጅ እንዲወልዱ ይመከራሉ።
"በቤተክርስትያን ታሪክ የወሊድ መቆጣጠርን የሚያበረታታ አንድ ቅዱስ ሰው አሳዩኝ እስቲ" ይላሉ አባ ሙሴ። ግለ-ሩካቤ (ማስተርቤሽን} ራስን ማጎሳቆል ነው ሲሉ የሚኮንኑት ቄሱ "በጣም አሳፋሪ እና ወንድነት የጎደለው ተግባር ነው" ይላሉ።
አባ ሙሴ እንደሚሉት ኦርቶዶክስ ማለት "ወንዳወንድነት ሳይሆን ትክክለኛ ተግባር ነው" ነገር ግን "ምዕራባዊው ዓለም ግን ሴታዊነት ያጠቃዋል።" አንዳንድ የፕሮቴስታንት ቤተክርስትያናት በዋነኛነት ለሴቶች የተሠሩ ናቸው ሲሉም ይወቅሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Buck Johnson
ሰውነቱ በንቅሳት የተሸፈነው የእሳት አደጋ ሠራተኛ የነበረው ባክ ጆንሰን መጀመሪያ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያንን መቀላቀል ያስፈራው እንደነበር ይናገራል።
ነገር ግን አማኞች እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለውታል። አሁን በፖድካስቱ አማካይነት እምነቱን ለማስፋፋት ይጥራል።
የቴክሳስ ነዋሪ የነበሩት አባ ዮሴፍ ግሊሰን ከ10 ዓመታት በፊት ነበር እምነቱን ተቀብለው አሜሪካን ጥለው ከሞስኮው የአራት ሰዓት መንገድ ላይ በምትገኘው ቦሪሶግሌብስኪ ኑሯቸውን ያደረጉት።
"ሩሲያ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ የለም፤ የሲቪል ማኅበራት የሉም፤ ልጆቻችን ቤታችን ማስተማር እንችላለን። ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ የቆየው ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ታሪክን እወደዋለሁ" ሲሉ በአንድ ቪድዮ ላይ ታይተዋል።
አባ ዮሴፍ ሌሎች ወግ አጥባቂ አሜሪካዊያን ወደ ሩሲያ እንደሚጡ ይመክራሉ። ባለፈው ነሀሴ ፑቲን የምዕራባዊያንን ሊበራሊዝም ሸሽተው ለሚመጡ በፍጥነት ቪዛ እንደሚሰጣቸው ተናግረው ነበር።
ቴክሳስ የሚኖረው ባክ እንደሚለው እሱና ሌሎች አማኞች የአሜሪካን የሸመታ ባሕል እርግፍ አድርገው መተው ጀምረዋል።
"ዘላቂ የሆነ ነገር ነው የምናስበው። ለምሳሌ ባሕል፣ ቤተሰብን መውደድ፣ ማኅበረሰብን መውደድ፣ ጎረቤትን መውደድ" ይላል።
"እኔ ኦርቶዶክስ ለሁሉም ትሆናለች ባይ ነኝ። በተለይ ደግሞ በቴክሳስ።"












