ቦይንግ ከኢትዮጵያና ከኢንዶኔዢያ የአውሮፕላን አደጋዎች ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ጋር ያለ መከሰስ ስምምነት ላይ ደረሰ

ቦይንግ 737 ማክስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቦይንግ የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያ አየር መንገዶች ላይ ከደረሱት ሁለት 737 ማክስ 8 የመከስከስ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ያለ መከሰስ ስምምነት ሊያደርግ መሆኑን የአሜሪካ የፍትህ መሥርያ ቤት አስታወቀ።

በስምምነቱ መሰረት አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ የሚቀርብበት የማጭበርበር ወንጀል ክስ የሚነሳለት ይሆናል።

ቦይንግ የፌደራል አቪየሽን ባለሥልጣናት የሚያካሄዱትን ምርመራ ማደናቀፉን አምኖ ለጥፋቱ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈል ተስማማቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 እና 2019 የደረሱት ሁለቱ የአውሮፕላን መከስከሶች የ346 ሰዎች ሕይወትን ቀጥፈዋል።

መንግሥት የሟቾቹን ቤተሰቦች ማነጋገሩን ገልጾ በርካቶች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል ወይንም በስምምነቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አላሰሙም ብሏል።

ነገር ግን የተወሰኑ የሟች ቤተሰቦች መንግሥትን በጉዳዩ ላይ አጥብቀው ተችተዋል።

እአአ በ2019 በኢትዮጵያ በተከሰተው የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ እህቱን ያጣው ሀቬር ዴ ሉዊስ በውሳኔው የተሰማውን ቅሬታ ቦይንግን በከሰሱ ቤተሰቦች ጠበቆች በኩል ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

"ይህ እርምጃ በመላ አገሪቱ ላሉ ኩባንያዎች ያስተላለፈው መልእክት፣ ምርቶቻችሁ ለደንበኞቻችሁ ደህንነታቸው የተጠበቀ ለማድረግ አትጨነቁ፤ ብትገድሏቸውም ትንሽ የቅጣት ገንዘብ ክፈሉ እና ሥራችሁን ቀጥሉ የሚል ነው" ብሏል።

የተጎጂዎችን ዘመዶች የሚወክለው ጠበቃ ፖል ካሴል በበኩሉ ቤተሰቦቹ ስምምነቱ ውድቅ እንዲደርግ ፍርድ ቤቱን ለማሳመን ይጥራሉ ብሏል።

"ይህ ዓይነቱ ያለመከሰስ ስምምነት ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ እና በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ለተፈጸመው እጅግ ገዳይ ወንጀል ስህተት ነው" ብሏል።

ቦይንግ በጉዳዩ ላይ ስላለው ምላሽ ተጠይቆ ምንም ዓይነት አስተያየት የለኝም ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴርም አስተያየት አልሰጠም።

የአሜሪካ የፍትሕ መሥርያ ቤት አርብ ዕለት ለፍርድ ቤት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ቦይንግ በአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) የሚደረገውን ምርመራ "ለማደናቀፍ እና ለማስተጓጎል ማሴሩን" በዚህም የተነሳ ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቅጣት እንደሚከፍል ተናግሯል።

ቦይንግ በፀረ ማጭበርበር እና በሥነምግባር መርሃ ግብሩ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን መቀጠል ይኖርበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 ከአዲስ አበባ ውጭ በደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ መከስከስ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲቆሙ ተደርገዋል።

በዚህ አደጋ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 157 ሰዎች ሞተዋል።

ይህ አደጋ ከመድረሱ አምስት ወራት ቀደም ብሎ በሊዮን ኤር የሚተዳደረው 737 ማክስ አውሮፕላን ከጃካርታ ኢንዶኔዥያ ተነስቶ በመብረር ላይ ሳለ በጃቫ ባህር ላይ ተከስክሷል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ 189 ሰዎች ሞተዋል።

ሁለቱም አደጋዎች ከተሳሳቱ የበረራ መቆጣጠሪያ ስርዓቶች ጋር የተገናኙ ነበሩ።

እአአ በ 2021፣ የመጀመሪያው የትራምፕ ፕሬዝዳንት ሥልጣን ማብቅያ ላይ፣ ቦይንግ ከአቃቤ ሕግ ጋር ለሦስት ዓመታት ያለመከሰስ ስምምነት ደርሷል።

የፌደራል አቃቤ ሕጎች ቦይንግ ያንን ስምምነት የአሜሪካ ሕጎች ሲጣሱ ለመለየት የሚያስችል ስርዓት እና የሥነ ምግባር መርሃ ግብር ባለመዘርጋቱ እና ባለመከተሉ ጥሷል ብለዋል።

የስምምነቱ ጊዜ ከማብቃቱ ሁለት ቀናት በፊት በአላስካ አየር መንገድ የሚተዳደረውን 737 ማክስ 9 በበረራ ላይ እያለ መስኮቱ ተገንጥሎ ወድቋል።

ባለፈው ዓመት፣ቦይንግ የፍርድ ሂደትን ለማስቀረት በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛነቱን ለማመን ተስማምቷል።

ነገር ግን የፌደራሉ ዳኛ ስምምነቱ ላይ ያላቸውን ስጋት እና የሕግ ክፍተት በመጥቀስ ውድቅ አድርገውታል።

የፍትህ መሥርያ ቤቱ ስምምነቱ እንደተጠናቀቀ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ክሱን ውድቅ ለማድረግ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

መሥርያ ቤቱ ለፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ ላይ "ስምምነቱ ቦይንግ ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ ከፍተኛ ጥቅሞች ላይ ዋስትና ይሰጣል። ይህም ችሎት ፊት በመቅረብ የሚታየውን እርግጠኛ አለመሆን እና የሙግት አደጋ ያስቀራል።"

የበርካታ ሟቾች ቤተሰቦች ጉዳዩ በችሎት እንዲታይ እና የቀድሞ የቦይንግ ኃላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲጠይቁ እና የወንጀል ክሱን ለማቋረጥ የተደረጉ ሙከራዎችን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

በአደጋ የተጎዱ ቤተሰቦችን የሚወክለው ጠበቃ ሮበርት ክሊፎርድ "ይህ የልብ ወዳጆች ስምምነት ነው" ሲል የፍትህ መሥርያ ቤቱን እና የቦይንግን ስምምነት ተችቷል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ መከስከስ የ28 ዓመቷ ሴት ልጇን ያጣችው ፈረንሣዊቷ ካትሪን በርቴት ቦይንግ ከወንጀል ነፃ ለማድረግ የተደረሰው ስምምነት በጣም እንዳስገረማት ተናግራለች።

"መንግሥት በጣም የምወዳት ሴት ልጄን ካሚልን ጨምሮ በ346 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ያደረገውን ቦይንግ ከክስ እንዲያመልጥ የሚያደርስ ጭፍን እምነት አዳብሯል" ብላለች በርቴት።