ቲክቶክ ዳግም ወደ ፍትሕ አደባባይ እንዲመጣ ያደረገው ወላጆቻቸውን የገደሉት ወንድማማቾች ጉዳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዕድሜያቸው በአስራዎቹ መጨረሻ እና በሃያዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በ1980ዎቹ የተፈጸመ ወንጀል ዳግም ወደ ፍትሕ አደባባይ እንዲወጣ አድርገዋል።
ሁለቱ የሜኔንዴዝ ወንድማማቾች ላይል እና ኤሪክ ወላጆቻቸውን በመኖሪያ ቤታቸው በመሳሪያ ተኩሰው ሲገድሉ አሁን ጉዳያቸውን አንስተው የተከራከሩላቸው የቲክቶክ ዘመን ልጆች አልተወለዱም ነበር።
ነገር ግን ጉዳዩ ዳግም ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎቹ ዘንድ የመጣው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ነው።
ላይል እና ኤሪክ ሜኔንዴዝ ወላጆቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ወንጀል ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም፤ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ግን ፍትሕ ከእነርሱ ወገን ዘንበል ብሏል ዳግም ጉዳያቸው ሊታይ ይገባል ሲሉ መወትወት ቀጠሉ።
ይህ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1996 የተወሰነ ውሳኔ ጉዳዩን በነፍስ ማጥፋት ወንጀልነት ብቻ የታየ ቢሆንም ለአፍላ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ግን በወላጆች የተፈጸመ የወሲብ ጥቃት እና ራስን ለመካለከል የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ ነው የቀረበው።
ወንድማማቾቹ ላይል እና ኤሪክ ሜኔንዴዝ ወላጆቻቸውን በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 20/1989 ነበር የገደሉት።
ሆዜ እና ኪቲ ሜኔንዴዝ ቢቨርሊ ሂልስ በሚገኘው ቅንጡ መኖሪያቸው ውስጥ ከቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የፖሊስ ምርመራ ያስረዳል።
ወንጀሉን የፈጸሙት ወንድማማቾቹ ልጆቻቸው ደግሞ በወቅቱ ዕድሜያቸው 21 እና 18 ነበር።
ፖሊስ ግድያ መፈጸሙን የሚገልጽ ጥሪ በደረሰው ወቅት ወንድማማቾቹ በሰጡት ቃል ወላጆቻቸውን ተገድለው ማግኘታቸውን ተናግረው ነበረ።
በኋላ ላይ ለዓመታት በወላጅ አባታቸው የወሲብ፣ አካላዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጥቃት ሲደርስባቸው መቆየታቸውን ገልጸው ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ ግድያውን መፈጸማቸውን አምነዋል።
አክለውም አባታቸው የሚፈጽምባቸውን ጥቃት ይፋ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ተከትሎ ሊገድላቸው እንደሚችል መዛቱን ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግ ግን የቤተሰቦቻቸውን ሀብት እና ንብረት ለመውረስ በመፈለግ ገድለዋቸዋል ሲል ተከራክሯል።
እንደ አውሮፓውኑ አቆጣጠር በ1996 ግድያ ለመፈጸም በማሴር እና በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ይግባኝ የሌለው የዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸዋል።
የእስር ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው እና በምህረት እንዲለቀቁ መጠየቅ የሚችሉት ላይን እና ኤሪክ ሜኔንዴዝ በ1989 በአባታቸው እና በእናታቸው ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ግድያ በተደጋጋሚ ጾታዊ ጥቃትን ስለደረሰባቸው እና የሥነ ልቦና ጉዳት ስለደረሰባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ላይል እና ኤሪክ ሜኔንዴዝ ሰባት ዓመት ከፈጀ ክርክር፣ ሦስት የተለያዩ ችሎቶች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሽፋን ካገኙ በኋለ ያለምንም ይቅርታ ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸዋል።
ለወንድመማቾቹ አሁን ነጻነት የሚያገኙበት ዕድል ተከፍቷል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ተጥሎባቸው የነበረው የዕድሜ ልክ እስራት ፍርድ ተነስቶ ወደ 50 ዓመት የተቀየረ ሲሆን፣ ይህም ምህረት እንዲደረግላቸው መጠየቅ ያስችላቸዋል።
ወንድማማቾቹ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ከታዩ ወንጀሎች ሁሉ በስፋት መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል።
ለዚህም ምክንያቱ የቤተሰቡ ታሪክ፣ ከሆሊውድ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የተሰጡ ምስክርነቶች እና የፍርድ ሂደቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲተላላፍ መደረጉ ነው።
የፍርድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ እና ውሳኔ ሲሰጥ ላይል እና ኤሪክ ወላጆቻቸውን ስለመግደላቸው ማንም ምንም ጥርጣሬ አልገባውም።
ለምን ወንጀሉን ፈጸሙ የሚለው ግን ዛሬም ድረስ መነጋገርያ ሆኖ የፍርድ ውሳኔውን ለመቀየር ተጽእኖ ማሳረፍ ችሏል።
ሆዜ እና ኪቲ የሚኖሩት የአሜሪካ ሕልም
በ1980ዎቹ ባለ የኑሮ ደረጃ ከተለካ የሜኔንዴዝ ቤተሰብ የአሜሪካን ሕልም በአግባቡ እየኖሩ የነበሩ ቤተሰቦች ምሳሌ ናቸው።
ሆዜ የተወለደው ኩባ ሲሆን በአገሩ የተካሄደውን አብዮት ተከትሎ በ1950ዎቹ ወደ አሜሪካ በስደት መጥቷል።
ሆዜ አሜሪካ ሲደርስ የአጎቱ ልጅ ቤት ነበር ተጠግቶ ይኖር የነበረው።
ነጻ የትምህረት ዕድል አግኝቶ ዩኒቨርስቲ ሲገባም ማሪ ሉዚ አንደርሰንንን ተዋወቃት።
ያቺን የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የሚያውቃት ሁሉ ኪቲ እያለ የሚጠራትን ኮረዳ በሁለት ዓመት ብትበልጠውም የፍቅር ጥያቄ አቀረበላት።
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተጋብተው ወደ ኒው ዮርክ አቀኑ።
በዚህ ወቅት ሆዜ በአካውንቲንግ ከኪዊንስ ኮሌጅ ዲግሪውን አግኝቶ ነበር።
ከሳህን አጣቢነት ወደ መዝናኛው ኢንዱስትሪ ተቀላቅሎ ውጤታማ ማናጀር ሆነ።
በ1980ዎቹ ትልልቅ ባንዶችን በስሩ ይዞ ይሠራ የነበረው አርሲኤ ሪከርድስን (RCA Records) በበላይ ኃላፊነት መርቷል።
ከዚያም ልጆቹን ላይል እና ኤሪክን ይዞ ቤተሰቡ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ ለመግባት እንዲያመቻቸው ወደ ሎስ አንጀለስ ፕሪንሲተን የመኖሪያ አድራሻውን ቀየረ።
ሆዜ እና ኪቲ የተገደሉበት መኖሪያ ቤታቸው በቢቨርሊ ሂልስ ዝነኞች በሚኖሩበት መንደር ይገኛል።
ቤታቸው በተለያየ ጊዜ በማይክል ጃክሰን እና በኤልተን ጆን ባለቤትነትም ተይዞ ነበር።
ላይል ዝነኛ የቴኒስ ተጫዋች ሲሆን፣ ዘወትር ስሙን አንስቶ እንደማይጠግበው አባቱ ስኬታማ የንግድ ሰው ለመሆን በሮች ሁሉ የተከፈቱለት ወጣት ነበር።
ኤሪክ በአባቱ ያልተቋረጠ እገዛ እና ድጋፍ ከወንድሙ የተሻለ የቴኒስ ተጫዋች ነው።
በእርሱ የዕድሜ አቻዎች ዘንድም ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ተጫዋች ነው።
እነዚህ ወንድማማቾች ውጤታማ ከመሆን ውጪ አማራጭ ያላቸው አይመስሉም። አባታቸው ሆዜም ቢሆን ልጆቹ በአትሌቲክስ እና በሌሎች መስኮች ሁሉ ውጤታማ እንዲሆኑለት ሳይታክት ጎትጓች፣ ተቆጪ እና አበረታች ነበር።
በ1990 የወንድማማቾቹ የዋና አሠልጣኝ ለሎስ አንጀለስ ታይምስ "ሆዚ ጠንካራ የሆነ የውድድር መንፈስ ያለው ይመስላል። ኤሪክ ውጤታማ እንዲሆን የሚችለውን ሁሉ ያደርግ ነበር" ሲል ተናግሯል።
ነገር ግን እሱ በጣም ኃይለኛ ነበር፣ ያ ደግሞ ውጤቱ ተቃራኒ ነበር። ኤሪክ በራስ የመተማመን ስሜቱ በጣም ያነሰ ነበር፤ ምክንያቱም እሱ የሚያደርገው ሁሉ አባቱ ከሚጠብቀው ያነሰ ስለነበረ።"
ወደ ካሊፎርኒያ ከሄዱ በኋላ ኤሪክ አመፀኛ ሆነ፣ በ1988 በስርቆት ወንጀልም ተሰማርቶ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
ምንም እንኳ ከእስር ቢያመልጥም የሥነ ልቦና አማካሪ ተመድቦለት በየጊዜው ክትትል ያደርግ ነበር።
ላይል ፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የገባ ቢሆንም የሰው ሥራን የራሱ አስመስሎ በማቅረብ ተይዞ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ ታግዶ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰቅጣጭ ወንጀል
ላይል እና ኤሪክ እናት እና አባታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ነው የገደሉት።
ሆዜ የ45 ዓመት ጎልማሳ ኪቲ ደግሞ 47 ዓመቷ ነበር።
ጥንዶቹ በ15 ጥይቶች ተደብድበው የተገደሉ ሲሆን፣ ከደረሰባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት የተነሳ ማንነታቸውን ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።
ፖሊስ በቅድሚያ ግድያው የተፈጸመው በቦምብ ጥቃት እንደሆነ አስቦ ነበር። መጀመሪያ ላይ የግድያውን ምርመራ የያዘው ፖሊስ ጥቃቱ የተፈጸመው በንግድ ተቀናቃኞቻቸው ይሆናል በሚል ትኩረቱን እዚያ ላይ አደረገ።
ሁለቱ ወንድማማቾች ግድያው በተፈጸመ ዕለት ፊልም ለማየት ወጥተው እንደነበር በመግለጽ ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ነገር ግን ኤሪክ መታወቂያውን ረስቶ በመውጣቱ ሲመለሱ ወላጆቻቸው ተገድለው ማግኘታቸውን እና ለፖሊስ መደወላቸውን ገልፀዋል።
የድረሱልኝ ቁጥር በሆነው 911 ላይ የኤሪክን የስልክ ጥሪ የመለሰው የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ በወቅቱ 18 ዓመት የሚሆነው ኤሪክ እያለቀሰ እና ሳግ እየተናነቀው እንደነበር አስተውሏል።
ወላጆቻቸው ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ወንድማማቾቹ ሎተሪ በቅርቡ እንዳሸነፈ ሰው ፈንጠዝያ ውስጥ ገቡ። "ምናቸውም በአሰቃቂ ሁኔታ ወላጆቻቸው ተገድለው ያዩ አይመስሉም ነበር" ይላሉ ሁኔታቸውን የተከታተሉ ምስክሮች። ሆዜ በሞተበት ወቅት አጠቃላይ ሀብቱ 14 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር።
ሁለቱ ወንድማማቾች በስድስት ወር ውስጥ 700,000 ዶላሩን አወደሙት።
የ21 ዓመቱ ላይል ውድ የሆኑት ሮሌክስ ሰዓት፣ ፖርሼ መኪና እና በርካታ ልብሶች እና ፕሪንስተን ውስጥ ምግብ ቤት ገዛ።
ኤሪክ ጂፕ ራንግለር፣ በ50,000 ዶላር የቴኒስ የግል አሠልጣኝ፣ በ40,000 ዶላር ደግሞ ባልተካሄደ የሮክ ሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ኢንቨስት አደረገ።
በርካታ ገንዘብ በስማቸው እንዳለ በማሰብ ወደ ቅንጡ መዝናኛዎች መመላለስ አዘወተሩ።
በእርግጥ በአባታቸው ስም የ5 ሚሊዮን የሕይወት የመድህን ዋስትና ቢኖርም በአንዳንድ ጉዳዮች የተነሳ ሊሰጣቸው አልቻለም።
ወንጀላቸውን ቀርፀው ያስቀመጡት ወንድማማቾች
ከግድያው በኋላ ዶ/ር ኦዚል የቀድሞ ደንበኛው ኤሪክ ጋር ዳግም በመገናኘት የምክክር አገልግሎት መስጠቱን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ ነው ኤሪክ ወላጆቹን መግደሉን የተናዘዘው።
ዶ/ር ኦዚል በትዳሩ ላይ ጁዳሎን ስሚዝ ከምትባል ሴት ጋር ይወሰልት ነበር። ለዚህች ወዳጁ ደንበኛው ኤሪክ ሜኔንዴዝ የነገራትን አጫወታት።
ዶ/ር ኦዚል ሁለቱንም ወንድማማቾቹን ማማከሩን የቀጠለ ሲሆን፣ የፈጸሙትን ወንጀል በቴፕ እንዲቀርፁ አድርጓቸዋል።
ስሚዝ እና ኦዚል የነበራቸው ድብቅ የፍቅር ግንኙነት እየተበላሸ ሲመጣ፣ ስሚዝ ወደ ቤቨርሊ ፖሊስ ሄዳ የሜኔንዴዝ ወንድማማቾች ወላጆቻቸውን መግደላቸውን እንደምታውቅ፣ መፈጸማቸውንም የሚገልጽ ማስረጃ በቴፕ ተቀርፆ መቀመጡን ሪፖርት አደረገች።
ላይል መጋቢት 8/1990 (እአአ) በቁጥጥር ስር ሲውል፣ ለቴኒስ ግጥሚያ እስራኤል የነበረው ኤሪክ ደግሞ መጋቢት 11 እጁን ለፖሊስ ሰጠ።
ለዶክተራቸው የፈጸሙትን ወንጀል በሚመለከት መናገራቸው እና በቴፕ ተቀርፆ መቀመጡ የሕግ እና የሥነ ምግባር ክርክር አስነስቶ የነበረ ሲሆን፣ ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ሁለት ዓመት ፈጅቷል።
በስተመጨረሻም የካሊፎርኒያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተቀረፁት ሦስት የቴፕ ካሴቶች መካከል ሁለቱ በችሎት እንደ ማስረጃ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ውሳኔ በመስጠቱ ፍርዳቸው መታየት ጀመረ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካውያንን በጥፍራቸው ያቆመው የፍርድ ቤት ውሎ
የወንድማማቾቹ ክስ በችሎት ፊት ቀርቦ መታየት የጀመረው እአአ በ1993 ነው።
የችሎቱ ውሎም በቀጥታ በቴሌቪዥን መታየት ጀመረ። በዚህም የተነሳ የችሎት ውሎ እንደ መዝናኛ እና የስፖርት ውድድር በቀጥታ የቴሌቪዥን ታዳሚዎች እየተከታተሉት በስሜት የሚጦዙበት ሆነ።
የቀጥታ ቴሌቪዥን ሥርጭቱ ችሎቱን ብቻ ሳይሆን፣ ከችሎቱ በፊት እና በኋላ ትንታኔዎችን እና አስተያየቶችን ያቀርብ ነበር።
ይህ ልክ እንደ ሶፕ ኦፔራ ድራማዎች አሜሪካውያንን በጥፍራቸው ያቆመ፣ በጉጉት ሰቅዞ የያዘ ጉዳይ ሆነ።
በሀብት የናጠጠው ቤተሰብ ቅሌት፣ ሁለት መልከ መልካም እና ምሥጢራዊ ወንድማማቾች፣ የተደበቀ ወንጀል እንዲሁም በድራማ የታጀበ የቤተሰቡ ሕይወት ለቴሌቪዥን ሥርጭት ጥሩ ማጣፈጫ ነበር።
በችሎት የተሰየሙት ዳኞች እና ጠበቆች፣ ዐቃቢያነ ሕጎች ወንድማማቾቹ ግድያውን የፈጸሙት የወላጆቻቸውን ሀብት ለመውረስ ነው፤ አይደለም ራሳቸውን ለመከላከል ነው እያሉ ይከራከራሉ።
ወንድማማቾቹ አባታቸው ለዓመታት ከስድስት እስከ 18 ዓመታቸው ድረስ እንደ ደፈራቸው በዝርዝር አስረድተዋል።
ላይል ከስድስት እስከ 8 ዓመቱ ድረስ በአባቱ መደፈሩን ሲናገር ኤሪክ ደግሞ ከስድሰት እስከ 18 ዓመቱ ድረስ ጥቃት እንደተፈጸመበት አብራርቶ አስረድቷል።
ይህ ደግሞ ቤተሰቡን እና አሜሪካውያንን በሁለት ጎራ ለይቶ ያሻኩታል።
የኤሪክ ጠበቃ የሆነችው ሌዝሊ አብራምሰን ከላይል ጠበቃ ጄራልድ ቻሌፍ ጋር በመሆን ወንድማማቾቹ ያደጉት ጥቃት በሚፈጽም ወላጅ እጅ መሆኑን ገልጸው ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የፈጸሙት ወንጀል መሆኑን አስረድተዋል።
ላይል የአባቱን ባሕሪ በዝርዝር ያስረዳ ሲሆን፣ ግድያውን ከመፈጸማቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አባታቸው ኤሪክ ላይ የሚፈጽመውን የወሲብ ጥቃት እንዲያቆም ሲጠይቀው አባቱ እንደሚገድለው መዛቱን አስረድቷል።
የመጀመሪያው ችሎት ስድስት ወር ፈጅቷል። ጉዳያቸውን ሰምተው ለመፍረድ የተሰየሙት ዳኞች ግን ወንድማማቾቹ ጥፋተኛ ናቸው የሚለው ላይ ለመስማማት አልቻሉም።
ከዚያም ሌላ ችሎት በ1995 ተሰየመ። በዚህ ወቅት የቴሌቪዥን ካሜራዎች ወደ ችሎቱ እንዳይገቡ ተከለከሉ።
ዳኛውም ሆዜ ልጆቹን ደፍሯል ለሚለው ውንጀላ በቂ ማስረጃ አልቀረበም ሲል ውድቅ አደረገ።
የቅርብ ቤተሰብ ግን ወንድማማቾቹ በአባታቸው መደፈራቸው እውነት መሆኑን እና ላይል ልጅ እያለ ስለጥቃቱ አንደነገራት መሰከረች።
ወንድማማቾቹ መጋቢት 21/1996 በፈጸሙት የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር ላይም የዕድሜ ልክ እስር ያለ ይቅርታ ተፈረደባቸው።
የሜኔንዴዝ ወንድማማቾች አዲስ የፍርድ ቤት ውሳኔ
ግድያው ከተፈጸመ 35 ዓመት አልፎታል።
አሁንም ግን የወንድማማቾቹ ወንጀል ብዙዎችን፣ በተለይ ደግሞ በቲክቶክ ላይ ሰዎች ለሁለት ተከፍለው እንዲከራከሩ አድርጓል።
በቅርቡ ደግሞ የወንድማማቾቹን ወንጀል በተመለከተ በኔትፍሊክስ ላይ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ውይይቱን አጡዞታል።
ዘመኑ ስለ ወሲባዊ ጥቃት የተሻለ ግንዛቤ ያለበት በመሆኑ ወንድማማቾቹ ላይ የተሰጠው ፍርድ ፍትሃዊ አይደለም ሲል ተከራከረ።
ለሎስ አንጀለስ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት በርካታ ኢሜይሎች ተጻፉ፤ የስልክ ጥሪዎች ተደረጉ።
የቀድሞው ዐቃቤ ሕግ ኃላፊ ጆርጅ ጋስኮን የወንድማማቾቹን ጉዳይ ድጋሚ እንዲያዩት ጥያቄ ቀረበላቸው።
እርሳቸውም ጉዳያቸው እንዲታይ እና ውሳኔው እንዲከለስ ውሳኔ አስተላለፉ።
ጋስኮን ውሳኔውን ባስተላለፉበት ወቅት ወንድማማቾቹ "ለማኅበረሰቡ የሚገባቸውን ያህል ቅጣታቸውን ተቀብለዋል ብዬ አምናለሁ" ነበር ያሉት።
አክለውም ወንድማማቾቹ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እንደሚያምኑ እና በማረሚያ ቤት ውስጥ የወሰዱት የተሃድሶ ሥልጠና ቀለል ያለ ውሳኔ ይሰጣቸው ለሚለው ውሳኔያቸው ግብዓት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ ወንድማማቾች ዶሴ ዳግም ከችሎት መዝገብ ቤት አቧራውን አራግፎ ተነሳ።
የሕግ ባለሙያዎች ለሁለት ተከፍለው ተከራከሩ። ወንድማማቾቹ ቀለል ያለ ውሳኔ ሊሰጣቸው አይገባም የመጀመሪያው የዕድሜ ልክ እስር ውሳኔ የጸና ይሁን ያሉ ሲኖሩ አይ የቀድሞ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔን እንቀበላለን ጉዳያቸው ዳግም ይታይ እና ፍርዱ ይቅለልላቸው ባሉ መካከል ሙግት ተካሄደ።
በኋላም ቀለል ያለ ውሳኔ ይሰጥ የሚለው ወገን አሸንፎ ወንድማማቾቹ ፍርዳቸው ወደ 50 ዓመት ዝቅ አለ።
ከዚያ በተጨማሪም በይቅርታ ለመለቀቅ እንደሚችሉ ተወሰነ።
የካሊፎርኒያ ሕግ ዕድሜያቸው ከ26 ዓመት በታች ሆነው ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች በይቅርታ ነጻ የመውጣት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለሜኔንዴዝ ወንድማማቾች ትልቅ እፎይታን የሰጠ ነው።
ወንድማማቾቹ መጀመሪያ ከይቅርታ ቦርድ ይሁንታን ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህም ስድስት ወር እና ከዚያ በላይ ሊወስድ ይችላል።
ላይል "ዛሬ ከ35 ዓመት በኋላ የነበርኩትን መለስ ብዬ ሳስበው ያሳፍረኛል" ማለቱ ተዘግቧል።
ኤሪክ በተመሳሳይ የፈጸመውን ወንጀል አምኖ "ወላጆቼ ላይ አምስት ዙር ጥይት ተኩሼ ዳግም ጥይት ለመሙላት ተመልሻለሁ። ለቤተሰቦቼ ዋሽቻለሁ። በጣም ከልቤ አዝናለሁ" ብሏል።
ወንድማማቾቹ የገባቸው ፀፀት እና ያለፉበት የተሃድሶ ሥልጠና ተገቢውን ውጤት አምጥቶ እንደሆን የሚነግረን ከማረሚያ ቤት ነጻ ሆነው ከወጡ በኋላ የሚሆነው ነው።












