የሱዳን ግጭት፡ በዋና ከተማዋ ካርቱም የሬሳዎች ዕጣ ፈንታ

የሱዳን መዲና ካርቱምን ለመያዝ ከተደረገ የሰባት ሳምንታት ግጭት በኋላ የከተማዋ ሰዎች ይገጥመናል ብለው አስበውት የማያውቁት ችግር ተደቅኖባቸዋል።
- ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ፅሑፍ አሰቃቂ የሚባሉ ቃለትን ያዘለ ነው።
“ሶስት ሰዎችን ቤታቸው ውስጥ ቀብሬያለሁ። የተቀሩትን ደግሞ እኔ ከምኖርበት መንገድ ፊት አድርጌያለሁ” ስሙ ለዚህ ፅሑፍ ሲባል የተቀየረው ኦማር።
“መቼም በር ከፍቶ ሬሳን ውሻ ሲበላው ከማየት ሳይሻል አይቀርም።”
እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ባይታወቅም ቁጥሩ ከ1000 እንደሚልቅ ግልጥ ነው። በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በተባባሪ ጥይት ሞተዋል።
መደበኛው ጦር እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ [አርኤስኤፍ] የተሰኘው ቡድን በተደጋጋሚ ተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈፅሙም ያን እየጣሱ እየተፋለሙ ይገኛሉ።
ሬሳ ለመቅበር ወደ መቃብር ሥፍራ መሄድ እጅግ አደገኛ ነው።
ኦማር ቢያንስ 20 ሰዎችን ቀብሯል።
“ጎረቤቴ ቤቱ ውስጥ ሳለ ተገደለ። ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ የሴራሚክ ወለሉን ነቃቅየ ቆፍሬ ቀበርሁት” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
“ሬሳዎች መንገድ ላይ ይበሰብሳሉ። አንዳንድ የካርቱም ሥፍራዎች አሁን የመቃብር ሥፍራ ሆነዋል።”
ባለፈው ወር ኦማር አል-ኢምታድ ከሚገኘው ቤቱ አቅራቢያ ካለ አንድ መንገድ ለአራት ሬሳዎች የሚሆን ጉድጓድ ቆፈረ።
እሱ እንደሚለው ሌሎችም ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ ዳር ጉዷጓድ እየቆፈሩ መቃብር እያበጁ ነው።
“አብዛኛዎቹ የተገደሉ ሰዎች ሬሳቸው ያረፈው ካርቱም ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ነው። ሌሎች ደግሞ መሐመድ ነጉብ መንገድ አካባቢ።”
ቤታቸው የተቀበሩ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ኦፊሴላዊ መረጃ ባይኖርም ኦማር “ቀላል አይደለም” ይላል።
ሌላኛው ለዚህ ፅሑፍ ሲባል ስሙ የተቀየረው ሃሚድም ቢሆን ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያለው።
ከመዲናዋ ወጣ ብላ በምትገኘው ሻምባት ሶስት የጦር ሠራዊት አባላትን መቅበሩን ለቢቢሲ የሚናገረው ሃሚድ የሞታቸው ምክንያት አንዲት ጄት ተከስክሳ ነው ይላል።
“በአጋጣሚ በሥፍራው ነበርኩ። ከሌሎች አምስት ሰዎች ጋር ሆነን የሰዎቹን ሬሳ ከስብርባሪው አራቅነው። አንድ መኖሪያ ሥፍራ ወስደን ቀበርናቸው።”
ቤት ንብረት የሚደልለው ሃሚድ ሬሳዎቹ የትም ይቀበሩ ዋናው ቁም-ነገር እሱ አይደለም ይላል።
“ዋናው መቅበራችን ነው። ፅድቅ ነው። ወደ መቃብር ሥፍራ መሄድ የሚታሰብ አይደለም፤ ቀናት ሊወስድ ይችላል። በዚያ ላይ አልሞ ተኳሾች በየቦታው አሉ።
ሕብረሰተቡን ከጤና ጠንቅ ለማዳን የምናደርገው ነገር ነው። ይህ ኃይማኖታዊና የሞራል ግዴታችን ነው።”

የፎቶው ባለመብት, Reuters
“እውነታን መቅበር”
ምንም እንኳ የካርቱም ነዋሪዎች ከቅን ልቦና ተነስተው ይህን ቢያደርጉም ይህ ግን የጦር ወንጀል ማስረጃን ማጥፋት ነው ይላሉ ዶክተር አቲያ አብዱላህ አቲያ።
እሳቸው እንደሚሉት ይህ ሬሳን አንስቶ የመቅበር ሂደት “እውነታውን ሊቀብር ይችላል” አልፎም ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ አይታወቅም።
ዶክተር አቲያ፤ ሬሳዎች ማንነታቸው ታውቆ ክብር ባለው መንገድ መቃብር ሥፍራ ማረፍ አለባቸው ይላሉ።
የከተማዋ ነዋሪዎች ሬሳዎችን አንስቶ የመቅበር ጉዳይን ለጤና ባለሥልጣናት፣ የቀይ መስቀልና ለሱዳን ቀይ ጨረቃ ማሕበር እንዲተዉ ዶክተሩ ያሳስባሉ።
“ሬሳዎችን በዚህ መልኩ መቅበር ተገቢ አይደለም። የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ሊካሄድ ይገባል። የሬሳ ምርመራ ባለሙያዎችና የቀይ መስቀል ሰዎች በተገኙበት ዘረ-መል መወሰድ አለበት።”
ሕግና ሥርዓት በሌለበት ሃገር እንዴት ሆኖ ይህ እውን ይሆናል ተብለው የተጠየቁት ዶክተሩ የውጭ ሃገራት ጣልቃ ሊገቡ ግድ ነው ይላሉ።
በጎ ፈቃደኞቹ ኦማር እና ሃሚድ ሬሳዎችን ከመቅበራቸው በፊት ፊትና ገላ የሚያሳይ ፎቶ አንስተው የሰዎችን ማንነት መለያ እንዲሆን በማስረጃ እንደሚያስቀምጡት ይናገራሉ።
ነገር ግን ዶክተር አቲያ ጥንቃቄ የጎደለው ቀብር በሽታን ሊያስፋፋ እንደሚችል ይገልጣሉ።
“ሬሳን በደንብ ሳይቆፍሩ መቅበር የመንገድ ዳር ውሾች ቆፍረው እንዲያወጡት ሊያደርግ ይችላል። ከሬሳው በለይ ክብደት ያለው ነገር አሊያም ጡብ ካልተቀመጠ ይጋለጣል” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
አሕመድ ስንል የምንጠራው የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ሬሳዎችን ከመንገድ በማንሳት ይተባበራል።
“የሬሳውን ፊት የተቀረ ገላ ፎቶ አነሳለሁ። የቆየና የበሰበሰ ነው ወይስ አዲስ ሬሳ ነው የሚለውን ለይቼ ቁጥር አደርገበታለሁ።”
ምንም እንኳ ዶክተሩ የቀብር ሂደቱን ቢወቅሱም አብዛኛዎቹ ሱዳናዊያን አሁን ከወደቀው የጤና መሠረተ-ልማት አንፃር ሌላ አማራጭ እንዳላቸው አያስቡም።
በፈረንጆቹ ግንቦት 11 አንድ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተሠራጭ ምስል ማጋዶሊን እና ማግዳ ዮሴፍ የተባሉ ሁለት ሴት ሱዳናዊያን ዶክተሮች ጓሯቸው ተቀብረው አሳየ።
ወንድማቸው በቪድዮ ጥሪ ለቢቢሲ ሲናገር ሁለቱን እህቶቹን ከመኖሪያ ቤታቸው ጓሮ መቅበር “ብቸኛው አማራጭ ነው” እንደሆነ ይገልጣል።
ወንድማቸው እንባ እየተናነቀው “ለ12 ቀናት ያክል ሳይቀበሩ ቆይተዋል” ይላል።
“ጎረቤቶቻቸው ከቤቱ አቅጣጫ ከባድ ሽታ እየመጣ መሆኑን ተመልክተው ከዚያ ተሰባስበው ጓሮ ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሯቸው።”
የሱዳን የጤና ባለሥልጣናት ከቀይ መስቀልና ከሱዳይ ቀይ ጨረቃ ጋር በመተባበር ሬሳዎችን ወደ መቃብር ሥፍራ ለመውሰድ እየሞከሩ ነው።
ነገር ግን በከተማዋ ያለው ጦርነት ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው እንዳይገቡ አድርጓል።
የእህትማማቾቹ ታሪክ የሱዳን ሕዝብ በዚህ ጦርነት ምክንያት እየተጋፈጠው ያለው የቀን ተቀን ታሪክ ሆኗል።
“እህቶቼ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ጓሮ ተቀብረዋል። መጨረሻቸው ይህ ይሆናል ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም።”












