በኢትዮጵያ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚካሄድ ተገለጸ

ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

አራተኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚካሄድ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገለጹ።

ቆጠራው ባለፉት ዓመታት ለተደጋጋሚ ጊዜ ሲራዘም የቆየ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ብዛትን የሚመለከት አስተማማኝ መረጃ የለም።

የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ባለፉት ዓመታት በዋነኛነት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በጦርነት ሳቢያ ሳይካሄድ መቅረቱን ሚኒስትሯ አክለዋል።

ከ2016 ዓ. ም. እስከ 2018 ዓ. ም. ድረስ የሚዘልቅ የሦስት ዓመት የኢንቨስትመንት ዕቅድ እየወጣ እንደሆነ ሚኒስትሯ ለቢቢሲ ገልጸው፣ በእዚህ ውስጥ ከተካተቱ ፕሮግራሞች የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከያዛቸው ዋና የጥናት ዓይነቶች አንዱ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ እንደሆነ ዶ/ር ፍጹም ተናግረዋል።

“የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ትክክለኛ በዚህ ቀን ነው የሚደረገው የሚለውን፣ ተጠሪነቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረገው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት አባል የሆኑበት የቆጠራ ኮሚሽን ቀርቦለት በዚህ ጊዜ ነው የሚለውን ከሦስት ዓመታቱ ውስጥ ይወስናል” ብለዋል።

የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ ከግምት ባስገባ ሁኔታ ቆጠራውን በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ዶ/ር ፍጹም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ታቅዷል፤ መደረግ አለበት። በዚያ ዘርፍ ልማት ከምናደርጋቸው አንዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ነው” ሲሉ አክለዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት ለሕዝብ እና ቤት ቆጠራው መዘግየት ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።

“ቆጠራ ቴክኒካል ነገሩ ይበልጣል። ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። አንደኛው፣ ሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ መድረስ መቻል ነው። የሰው ቁጥር ይሄን ያህል ነው ብሎ ለመወሰን፣ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አብላጫውን የአገሪቷን ክፍል በአንዳች ጊዜ መድረስ ነው” በማለት ዶ/ር ፍጹም የሕዝብ እና ቤት ቆጠራውን አካሄድን አስረድተዋል።

ሁሉንም አካባቢዎች መድረስ አንደኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ መሠረታዊ ነጥብ ከመሆኑ አንጻር፣ ባለፉት ዓመታት እንቅስቃሴ በመገታቱ ቆጠራውን ማካሄድ አለመቻሉንም መልክተዋል።

“አሁን መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ ስለሆነ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራው በዕቅድ ተካቷል” ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሕዝብ ብዛት ሳይቆጠር መቅረቱ ያሳደረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ፍጹም፤ የተሻለ እና ተጨባጭ መረጃ የሚባለው “ዛሬ ላይ ስንት ሰው አለ” የሚለውን ማወቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን ቆጠራ መካሄድ ባለበት ጊዜ ውስጥ ሳይካሄድ ሲቀር ሳይንስን የተመረኮዘ ትንበያ ማስቀመጫ (Projection) መንገዶችን በመጠቀም በየዓመቱ “የምንፈልገውን ከሕዝብ ቁጥር ጋር የተያያዘ መረጃ እናገኝ ነበር” ብለዋል።

ይህ መንገድ “ጉልህ የሚባል ስህተት” እንደማይኖረው ገልጸውም መረጃው ለፖሊሲ ግብዓት እየዋለ እንደነበር ተናግረዋል።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ በኢትዮጵያ

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው በ1976 ዓ.ም. ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በ1987 ዓ. ም. እንዲሁም ሦስተኛው ከ1999 ዓ. ም. እስከ 2000 ዓ. ም. ተካሂዷል።

ሦስተኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው በ1997 ዓ. ም. ሲሆን የተካሄደው ግን ሁለት ዓመት ዘግይቶ በ1999 ዓ. ም. ነው።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስከአሁን የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ የተከናወነው ሦስት ጊዜ ነው። አራተኛው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ከ2010 ዓ. ም. እስከ 2013 ዓ. ም. ባሉት ዓመታት አራት ጊዜ የተራዘመ ሲሆን፣ በ2014 ዓ. ም. ለአምስተኛ ጊዜ ተራዝሟል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ትንበያ የዓለማችንን ግማሽ ሕዝብ ይይዛሉ ካላቸው ስምንት አገራት መካከት ኢትዮጵያ ትገኝበታለች።

የዓለም ባንክ ቁጥር እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ60 ዓመታት በፊት ከነበረው በአምስት እጥፍ አድጓል።

እነዚህን ትንበያዎች መሠረት በማድረግ በስፋት እንደሚጠቀሰው በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከ110 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይገመታል።