ህወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ‘ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጪ ነው’ በማለት ተቃወመ

የፎቶው ባለመብት, TPLF
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሕጋዊነቱ እና ንብረቶቹ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጪ ነው በማለት ተቃወመው።
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ህወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ መሰየሙ እና በምርጫ ቦርድም የነበረው እውቅና ተሰርዞ ሕገ ወጥ ተደርጎ ቆይቶ እንደነበር ይታወሳል።
ለሁለት ዓመት የቆየውን ጦርነት ለማብቃት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በቡድኑ ላይ ተጥሎ የነበረው የሽብርተኛነት ፍረጃ ተነስቶ ጊዜያዊ መስተዳደር ተቋቁሟል።
ህወሓት ለምርጫ ቦርድ የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ እና የፓርቲው ንብረት እገዳ እንደነሳለት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም ስምምነትን በመጥቀስ ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም ጥያቄ ቢያቀርብም ቦርዱ ሳይቀበለው በመቅረቱ ነው ተቃውሞውን የገለጸው።
ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ድንጋጌ ስለሌለ የቀረበለትን የሕጋዊ ሰውነት የማስመለስ ጥያቄ “በሕግ የተደገፈ ሆኖ ባለማግኘቱ” አንዳልተቀበለው ጠቅሶ፣ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመንቀሳቀስ የሚችለው በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑን አሳውቋል።
ነገር ግን ህወሓት በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው እና “በፕሪቶሪያ የተደረሰው ስምምነት እና ሕግን መሠረት ያላደረገ ነው” በማለት “እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነት ትግበራን ባለቤት አልባ የሚያደርግ” ነው በማለት ባወጣው መግለጫ ላይ አጥብቆ ተቃውሞታል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነው ህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።
ፓርቲው ጨምሮም ስምምነቱ በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በሌሎችም አካላት ስምምነቱ እውቅና እና ድጋፍ የሰጡት መሆኑን በመጥቀስ “በቦርዱ ውሳኔ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የማይቀበል ነው” ሲል ተችቶታል።
የቦርዱ ውሳኔ “የሰላም ሂደቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ያለው ህወሓት፣ ውሳኔውን እንደማይቀበለው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይበት በመግለጽ “የምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንደገና በማጤን የፕሪቶሪያን ስምምነት እና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያሳለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ” ጥያቄውን እንዲቀበል ጠይቋል።
የፌደራል መንግሥቱም የቦርዱ ውሳኔ እንደገና ታይቶ ከህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ጥያቄዎች አንጻር ያሉ “ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ አማራጮችን” ተጠቅሞ ፓርቲው ለከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት እንዲመለስ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተደደርም የቦርዱ ውሳኔ “የሰላም ስምምነቱን ባለቤት አልባ የሚያደርግ” እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተሳተፉ ያሉት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮችን “እውቅና በመንፈግ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ህልውና አደጋ ላይ ይሚጥል” ነው በማለት የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን በመሆኑ ቦርዱ ውሳኔውን መርምሮ እንዲያስተካክል ነው ጠይቋል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሹ ጦርነት በትግራይ ክልል ውስጥ ከተቀሰቀሰ ከወራት በኋላ ጥር 10/2013 ዓ.ም. ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሣተፉን” ማረጋገጡን በመግለጽ ሕጋዊ ሰውነቱን የሰረዘው።
በዚህ መሠረትም የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ውሳኔ ከማሳለፉ በተጨማሪ በህወሓት ስም የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረቶች ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሸፈኛ እንዲውል፤ ዕዳው ተሸፍኖ የሚተርፍ ንብረት ከተገኘ ቀሪው ገንዘብ እና ንብረት ለሥነ ዜጋ እና ለመራጮች ትምህርት እንዲውል ቦርዱ መወሰኑ ይታወሳል።
የሰላም ስምምነት ከተፈረመ እና ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ህወሓት ወደ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የተመለሰ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የሕጋዊ ሰውነት ዕውቅናው እና ንብረቶቹ እንዲመለሱለት ጥያቄ አቅርቦ በቦርዱ ተቀባይነት አላገኘም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለፓርቲው በሰጠው ምላሽ፣ የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1162/ 2011 እንደማይገኙ በማመልከት፣ ጥያቄው በሕግ የተደገፈ አይደለም በማለት ውድቅ አድርጎታል።
ጨምሮም ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመንቀሳቀስ የሚችለው በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑን ገልጿል።
የፓርቲው ንብረትን በተመለከተ የቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ፓርቲው ላይ የሰጠው የስረዛ ውሳኔ ውጤት በመሆኑ እንደ አዲስ ሊጠየቁ የሚችሉ ሆነው እንዳላገኘው በመግለጽ ሳይቀበለው መቅረቱን መግለጹ ይታወሳል።












