አፍሪካውያን ሴቶች በቤተሰቦቻቸው የመገደል ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል - ተመድ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአፍሪካ ውስጥ ሴቶች እና ልጃገረዶች ከየትኛውም የዓለም ክፍል በበለጠ ሁኔታ በቅርብ አጋራቸው ወይም በሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ከፍተኛ የመገደል አደጋ እንደተጋረጠባቸው የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት ባወጡት ሪፖርት እንዳለመከተው አፍሪካ ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እጅግ ከፍተኛ ነው።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ዙሪያ 45,000 የሚሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች በቅርብ አጋራቸው ወይም በሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ተገድለዋል።
ይህም ማለት በየአንዳንዱ ሰዓት ከአምስት በላይ ሴቶች እና ልጃገረዶች የቤተሰባቸው አባል በሆኑ ግለሰቦች ግድያ ይፈጸምባቸዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የዕጽ እና የወንጀል መቆጣጠሪያ እንዲሁም የሴቶች ጽህፈት ቤቶች በጋራ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት፣ አሃዙ በእጅጉ አስደንጋጭ ከመሆኑ ባሻገር ትክክለኛው በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግድያ መጠን ከዚህ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል ብሏል።
ይህ በቅርብ አጋር ወይም በሌሎች የቤተሰብ አባላት በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግድያ በአህጉር ሲከፋፈል አፍሪካ በ17,200 ሁለተኛ ላይ ስትቀመጥ እስያ በ17,800 የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች። በአሜሪካ 7,500 እንዲሁም በአውሮፓ 2,500 ተመሳሳይ ወንጀሎች ተከስተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እነዚህን ግድያዎች ለመከላከል ለሴቶችን ሰብአዊ መብቶች ለሚከራከሩ እና ለሴቶች መብቶች ተቆርቋሪዎች ደኅንነት መጠበቅ ለቆሙ ወገኖች ጥበቃ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
“በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት እና አጋሮች ለሴቶች መብት መከበር ለሚሰሩ ድርጅቶች የገንዘብ እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ” ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት የሴቶች ጉዳይ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሲማ ባሁስ ተናግረዋል።
ይህ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ይፋ የተደረገው ከዛሬ አርብ ጀምሮ በመላው ዓለም ለ16 ቀናት የሚካሄደው ፀረ ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ በተጀመረበት ጊዜ ነው።












