ከ30 ዓመታት በላይ በማቀዝቀዣ ውስጥ ከነበረ ሽል መንታ ልጆች ተወለዱ

መንትዮቹ ሊዲያ እና ቲሞቲ

የፎቶው ባለመብት, NATIONAL EMBRYO DONATION CENTER

የምስሉ መግለጫ, ሊዲያ እና ቲሞቲ የተወለዱት እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 31፣ 2022 ነው።

በአሜሪካዋ ግዛት ቴኒሲ ከ30 ዓመታት በላይ በማቀዝቀዣ ውስጥ ከቆዩ ሽሎች መንታ ልጆች መወለዳቸው ተነገረ።

ይህም ለረጅም ጊዜ በማቀዝቀዣ የቆየ ሽል ስኬታማ ሆኖ ሲወለድ አዲስ ክብረ ወሰን ነው ተብሎ ይታመናል።

ሽሎቹ ከዜሮ በታች 128 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚጠጋ ቅዝቃዜ ባለው የናይትሮጂን ፈሳሽ ውስጥ የተቀመጡት እንደ አውሮፓውያኑ ሚያዝያ 22/1992 ነበር።

የኦሪገን ነዋሪዋና የአራት ልጆች እናት የሆነችው ራቸል ሪጂወይ፣ መንታ ልጆቹን የወለደችው ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ነው።

አባት ፊሊፕ ሪጂወይ ሁኔታውን “ተአምር” ብሎታል።

እስካሁን ከተለገሱ ሽሎች ከ1 ሺህ 200 ህጻናት በላይ እንዲወለዱ ካደረገው የግል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ድርጅት የሆነው ብሔራዊ የሽል ልገሳ ማዕከል እንደሚለው እነዚህ መንትዮች በዘርፉ አዲስ ክብረ ወሰን ሳያስመዘግቡ አልቀረም።

ድርጅቱ ቀደም ብሎ የመዘገበው ክብረ ወሰን የተያዘው እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በተወለደው ሞሊይ ጊብሰን ሲሆን የተወለደው ለ27 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ማቀዝቀሻ ውስጥ ከቆየ ሽል ነበር።

ሽሎቹን ወደ ማህጸን ያሸጋገሩት ዶ/ር ጆን ዴቪድ ጎርዶን “እነዚህን ሽሎችን ለመቀበል የተደረሰው ውሳኔ ከ5፣ ከ10 እና ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጠሩ ሽሎችን ለመውሰድ የሚፈልግ ይኖሩ ይሆን? በሚል ለሚያስቡ ምላሽ የሰጠ ነው” ብለዋል።

መንታ ሽሎቹ የተፈጠሩት ስማቸው ካልተገለጸ ጥንዶች በአይቪኤፍ (በቤተ ሙከራ ብልቃጥ) አማካኝነት ነበር።

ወንዱ በ50ዎቹ የእድሜ ክልል ላይ የነበረ ሲሆን፣ ከ34 ዓመት እድሜ ያላት ሴት ከለገሰችው እንቁላል ጋር የተገናኘ ነው።

አይቪኤፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና ሲሆን፣ ይህ የሕክምና ዘዴ ከሴቷ እንቁላል ከወንዱ ደግሞ የዘረ ፈሳሽ በመውሰድ በቤተ ሙከራ እንዲገናኙ ተደርጎ ፅንስ ከተፈጠረ በኋላ ያ ፅንስ ተመልሶ ማህፀን ውስጥ እንዲገባ የማድረግ ሒደት ነው።

ጥንዶቹ ሌላ ባልና ሚስት እንዲጠቀሙባቸው በኖክስቪል፣ ቴኒሲ ለሚገኘው የሽል ልገሳ ማዕከል በስጦታ እስከሰጡበት 2007 ድረስ በአሜሪካ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ በሚገኘው በሽል ማሳደጊያ ቤተ ሙከራ ውስጥ ተቀምጦ ቆይቷል።

ከዚያም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የድርጅቱ አጋር በሆነውና በደቡብ ምሥራቅ በሚገኘው ክሊኒክ ውስጥ የሚሰሩ የጽንስ ባለሙያዎች ሽሉን ወደ ማህጸን አዘዋውረውታል።

ድርጅቱ በመግለጫው እንዳለው ዜናው የሽል ልገሳ ያስገኘውን በረከት ሌሎችም እንዲሞክሩት የሚያበረታታ ነው ብሏል።

እነዚህ መንታ ህጻናት፣ ለወለዷቸው ወላጆቻቸው በአይቪኤፍ አማካይነት ያገኟቸው የመጀመሪያ ልጆች ናቸው። ጥንዶቹ ሌሎች እድሜያቸው ከ1 እስከ 8 የሚደርስ አራት ልጆች አሏቸው።

አባት ፊሊፕ ሪጂወይ ለሲኤንኤን ከቤቱ ሆኖ በሰጠው ቃለ ምልልስ “ፈጣሪ ለሊዲያ እና ቲሞቲ ሕይወት ሲሰጥ እኔ የ5 ዓመት ልጅ ነበርኩ።ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ይህን ሕይወት ጠብቆ አቆይቷል” ብሏል።

“እነዚህ መንታ ልጆች ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆኑም በእድሜ ትልቆቹ ልጆቻችን ናቸው። ይህም የሚያስገርም ነው” ብሏል ፊሊፕ።