የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ከባለቤታቸው ሶፊ ጋር ተለያዩ

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ እና ባለቤታቸው ሶፊ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ እና ባለቤታቸው ሶፊ 18 ዓመታትን በትዳር አብረው ኖረዋል።

ነገር ግን የትዳር ጉዟቸው ከዚህ በላይ መቀጠል እንዳልቻለ ጥንዶቹ አስታውቀዋል።

“ትርጉም ካለው እና ከባድ ንግግር በኋላ” ወደዚህ ውሳኔ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በኢንስታግራም ገጽ ባጋሩት መረጃ፣ ጥንዶቹ የትዳር ጉዟቸውን ቢቋጩትም እጅግ የተቀራረበ ቤተሰባዊ ፍቅር እና አክብሮት ኖሯቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ሁለቱ ጥንዶች ትዳር የመሰረቱት በጎሮጎሳውያኑ 2005 ሲሆን በ18 ዓመት የትዳር ቆይታቸውም 3 ልጆችን አፍርተዋል።

የጀስቲን ትሩዶ ቢሮ እንደገለጸው ደግሞ ሁለቱ ጥንዶች የፍች ወረቀታቸውን ቢፈርሙም በትልልቅ ዝግጅቶች ላይ በአንድ ላይ መታየታቸውን ይቀጥላሉ ብሏል።

በቀጣይ ሳምንትም እንደቤተሰብ በጋራ ያሳልፋሉ ብሏል መግለጫው።

የ15፣ 14 እና የ9 ዓመት ልጆቻቸውን ሁኔታ በተመለከተ ከልጆቹ የግል መብት አንጻር ሚስጥራዊ ሆኖ እንዲቆይላቸው ጥንዶቹ ጠይቀዋል።

“እስካሁን በጋራ ያፈራነውን እና በቀጣይም የምናፈራውን ሁሉንም ነገር በትልቅ ቤተሰባዊ ፍቅር እና አክብሮት አብረን እናስቀጥላለን” ብለዋል የ51 ዓመቱ ትሩዶ እና የ48 ዓመቷ ሶፊ ትሩዶ።

ጥንዶቹ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙም አብረው አይታዩም ነበር።

በግንቦት ወር የንጎሥ ቻርለስ ሦስተኛን የንግሥና ሥነ ሥርዓት በጋራ የታደሙ ሲሆን በመጋቢት ወር ደግሞ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ተቀብለው በካናዳ በጋራ አስተናግደዋል።

ጀስቲን ትሩዶ በ2015 ለጠቅላይ ሚንስትርነት ሲመረጡ ሰለሁለቱ ጥንዶች በስፋት ተወርቶ ነበር።

በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ መመረጣቸውን ተከትሎ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ሶፊ የተናገሩት በብዙዎች ዘንድ የሚታወስ ነው። “ለመጀመሪያ ጊዜ የፍቅር ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ‘31 ዓመቴ ነው። 31 ዓመት ሙሉ ደግሞ አንቺን ስጠብቅ ነበር’ አለኝ” በማለት ሶፊ እና ትሩዶ የተዋወቁበትን ቅጽበት ተናግረው ነበር።

በ2022 የጋብቻ መታሰቢያ በዓላቸው ላይ ደግሞ ሶፊ “በጋራ በመሆን ጸሃያማና ነጎድጓዳማ ቀናትን በጋራ አሳልፈናል” ብለው ነበር።

ጄስቲን ትሩዶም በ2014 በጻፉት ግለ ማስታወሻ “ጋብቻችን ፍጹም አይደለም። ሶፊ ምርጥ ጓደኛዬ፣ የትዳር አጋሬ፣ እና ፍቅረኛዬ ሆና ብትቀጥልም ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈናል። በአስቸጋሪ ጊዜዎችም ቢሆን ግን ሁለታችንም ታማኞች ነን” ብለዋል።

ሁለቱ ጥንዶች ሶፊ የቴሌቪዥን አስተዋዋቂ በነበሩበት ወቅት በ2003 ነው ትውውቅ የጀመሩት። ሶፊ በአዕምሮ ሕመም ሥራ እና ከአመጋገብ ችግር ጋር የተገናኙ ሥራዎችን በመስራት ይታወቃሉ።

ጀስቲን ትሩዶ በስልጣን ላይ ሆነው የትዳር ፍቻቸውን ይፋ በማድረግ ሁለተኛው የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው።

የመጀመሪያው አባታቸው ፒዬር ኢሊዮት ትርዶ ናቸው። ከባለቤታቸው ማርጋሬት ትሩዶ ጋር ለስድስት ዓመታት በትዳር ከቆዩ በኋላ በ1977 መፋታታቸውን ለሕዝብ ይፋ አድርዋል።