ሶማሊያ ቀርፋፋዋን የ100 ሜትር ሯጭ በማሰለፏ ይቅርታ ጠየቀች

ናስራ አቡበከር አሊን

የፎቶው ባለመብት, SNTV

የምስሉ መግለጫ, ናስራ አቡበከር አሊን

ቻይና ባዘጋጀችው የዓለም የዩኒቨርሲቲ ጨዋታዎች የ100 ሜትር ሩጫ ውድድር ልምድ አልባ አትሌት ያሰለፉ የሶማሊያ ባለሥልጣናት መንበራቸውን እንዲለቁ ጫና እየተደረገባቸው ነው።

የሃገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር 100 ሜትር ለመጨረስ ከተቀናቃኞቿ ሁለት እጥፍ ጊዜ የወሰደባት ናስራ አቡበከር አሊን በመምረጣቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።

ናስራ ከዚህ ቀደም ይህን በመሰለ ውድድር ተሰልፋ እንደማታውቅ ተዘግቧል።

ማሕበራዊ ሚድያን ባጥለቀለቀው ቪድዮ አትሌቷ አፈትልከው የወጡ ተቀናቃኞቹን ተከትላ ውድድሩን ካጠናቀቀች በኋላ ፈንጠዝ ስትል ይታያል።

ልምድ አልባዋ አትሌት ወድድሩን ለማጠናቀቅ 21.81 ሰከንድ ሲወስድባት አንደኛ ከወጣችው አትሌት 10 ሰከንድ ዘግይታ ነው የገባችው።

ስፖርትስ ሚኒስትር ሞሐመድ ባሬ ሞሐሙድ ክስተቱን አሳፋሪ ብለውታል።

“ዛሬ የተፈጠረው ነገር የሶማሊያ ሕዝብን የሚወክል አይደለም. . . ለሶማሊያ ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል።

አትሌቷ ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖራት ይህን በመሰለ ከፍተኛ የውድድር መድረክ እንዴት ልትገኝ መቻሏ እንዴት ተመረጠች የሚል ጥያቄ ጭሯል።

“እንዲህ ያለ ቀሽም መንግሥት ማየት ልብ ይሰብራል። እንዴት ነው ምንም ልምድ የሌላት ልጅ በሩጫ ሶማሊያን እንድትወክል የምትላከው” ኢልሃም ጋርድ የተሰኘች የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ሐሳቧን ሰጥታለች።

“ይህ በጣም አስደንጋጭ ነው። በዓለም አቀፉ መድረክም ሃገራችንን የሚያሳፍር ነው።”

በፌስቡ ገፁ መግለጫ የሰጠው የሶማሊያ ዩኒቨርሲቲዎች ማሕበር በውድድሩ እንዲሳተፉ አትሌቶችን አለመላኩን ገልጧል።

የሶማሊያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ናስራ አቡበከር አሊ እንዴት ልትመረጥ እንደቻለች ለማጣራት ምርመራ ከፍቷል።

ሶማሊያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲወክሏት በመረጠቻቸው አትሌቶች አማካይነት ስሟ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በፈረንጆቹ 2016 ማርያን ኑህ ሙሴ በ400 ሜትር ተሳትፋ 1 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ 14 ማይክሮ ሰከንድ ገብታለች።

በሪዮ ኦሊምፒክ በተካሄደው በዚህ ውድድር አማካይ ሰዓት የነበረው 48 ሰከንድ ነበር።

ነገር ግን ብዙዎች አትሌቷ የሶማሊያ ሴት አትሌቶች የሚያጋጥማቸውን ፈተና አልፋ በውድድሩ በመሳተፏ አድናቆታቸውን ገልጠውላታል።

በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ደግሞ ዘምዘም ሞሐመድ ፋራህ ከአሸናፊው 30 ዘግይታ 1፡20፡48 መግባቷ አይዘነጋም።

አትሌቷ በውድድሩ እየተሳተፈች ሳለ ሶማሊያ ከሚኖሩ ሴቶች በስፖርት ውድድሮች መሳተፍ የለባቸውም ከሚሉ ግለሰቦች የሞት ዛቻ ይደርስባት ነበር።