አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ሊዞ በወሲባዊ ትንኮሳ እና ጤናማ ያልሆነ የስራ አካባቢን በመፍጠር ተከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ሊዞ በወሲባዊ ትንኮሳ እና ምቹ ያልሆነ የስራ አካባቢን በመፍጠር ሶስት የቀድሞ የዳንስ ባለሙያዎቿ ከሰዋታል።
ሶስቱ የቀድሞ ዳንሰኞች ያቀረቧቸው ክሶች ወሲባዊ ትንኮሳ፣ የሃይማኖት እና የዘር መድልዎ፣ ጥቃቶች እና ሃሰተኛ እስርን ያካትታሉ።
ሊዞ ወፍራም ዳንሰኛን በሰውነቷ እንድትሸማቀቅ በማድረግ እንዲሁም የአንዲት አርቲስትን ጡት እንድትነካም ጫና በማድረግ ክስ ቀርቦባታል።
ሊዞ እና ሌሎች አብረዋት ክስ የቀረበባቸው ግለሰቦች አስተያየት እንዲሰጡም በቢቢሲ ተጠይቀዋል።
ሙዚቀኛዋ ለቀረቡባት ክሶች እስካሁን በይፋ ምላሽ አልሰጠችም።
አሪያና ዴቪስ፣ ክሪስታል ዊልያምስ እና ኖኤል ሮድሪጌዝ የተባሉ የቀድሞ የዳንስ ባለሙያዎች በሙዚቀኛዋ እንዲሁም በዳንስ አስተባባሪዋ እንዲሁም በኩባንያዋ ቢግ ገርል ቢግ ቱሪንግ ላይ ክስ የመሰረቱት።
ማክሰኞ እለት በሎስ አንጀለስ የቀረበው ክስ የዳንስ ባለሙያዎቹ “ላልተገባ ወሲባዊ ባህርያት ተጋልጠዋል” እንዲሳተፉ ተደርገዋል እንዲሁም “በሚረብሹ ወሲባዊ ትዕይንቶችም ላይ እንዲሳተፉ ጫና ተደርጎባቸዋል” የሚል ነው።
የዳንስ ባለሙያዎቹ እነዚህ ጫናዎች ደርሰውብናል ያሉት ከጎሮጎሳውያኑ 2021- 2023 ድረስም ነው ተብሏል።
ሊዞ ወይም በትክክለኛ ስሟ መሊሳ ቪቪያን ጄፈርሰን ከቀረቡባት ክሶች መካከል አሪያና ዴቪስ የተባለችውን የዳንስ ባለሙያዋን በአምስተርዳም በአንድ ምሽት ክበብ ውስጥ የነበረችን አርቲስት ጡት እንድትነካ ጫና አድርጋለች የሚል ነው።
አሪያና መጀመሪያ ላይ እምቢታዋን ብትሰማም በመጨረሻም ከስራዋ ሊያባርራት ይችላል በሚልም እንደተስማማች ክሱ ላይ ቀርቧል።
ቀጭን ሰውነት በሚወደድበት ዓለም ውስጥ ያላትን ውፍረት በማክበር እና በመውደድ ታዋቂነትን ያተረፈችው ሊዞ አንድ የዳንስ ቅንብር ባለሙያዋንም ሰውነትን አሸማቀሻል የሚል ክስ ቀርቦባታል።
የዳንስ ቅንብር ባለሙያዋ ታኒሻ ስኮትን በአንድ የሙዚቃ ጉዞ ላይ በውፍረቷ አሸማቃታለች ተብሏል።
በተጨማሪም የሊዞ ኩባንያ ቢግ ገርል ቢግ ቱሪንግ አስተዳዳሪዎች የዘር መድልዎችን ይፈጽማሉ የሚሉ ክሶችም ቀርቦባቸዋል።
ጥቁር የዳንስ ባለሙያዎች ከሌሎች የቡድኑ አባላት በተለየ መልኩ መድልዎ እንደደረሰባቸውም በዚሁ ክስ ላይ ተተንትኗል።
“ሰነፎች፣ ሙያ የሌላቸው እንዲሁም መጥፎ ባህርይ” ያላቸው በሚልም ጥቁር የዳንስ ባለሙያዎች በኩባንያው አስተዳዳሪዎች እንደተፈረጁም ተጠቅሷል።












