በኤርትራ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተባለ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመዘገበ

የመሬት መንቀጥቀጥ ያጋጠመ

የፎቶው ባለመብት, VOLCANO DISCOVERY

በማዕከላዊ ኤርትራ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች በሬክተር ስኬል 5.4 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተዘገበ።

የጀርመኑ የሥነ-ምድር ሳይንስ የጥናት ማዕከል በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. ምሽት 2፡15 ላይ የመሬት መንቀጥቀጡ አጋጥሟል ብሏል።

ረቡዕ ነጋት ላይ ደግሞ ከቀደመው ያነሰ መጠን ያለው 4.8 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ተመዝግቧል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል የመሬት መንቀጥቀጡ መከሰቱን አረጋግጠው የመሬት ነውጡ ማዕከል ከመዲናዋ አሥመራ 65 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ኢራፋአለ ነው ብለዋል።

በርዕደ መሬቱ በኤርትራ እና በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

የጀርመኑ የሥነ-ምድር ሳይንስ የጥናት ማዕከልም ምንም እንኳ 5.4 የተመዘገበውን የመሬት መንቀጥቀጥ ‘ከባድ’ ብሎ ቢገልጸውም ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሊያደርስ አይችልም ብሏል።

ከመደርደሪያዎች ላይ እቃ መውደቅ እና የመስታውት መስኮቶች ከመሰባበር የዘለለ የከፋ ጉዳት ላያደርስ ይችላል ብሏል ተቋሙ።

የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው በ10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ ሲሆን፣ ከመሬት በታች አንዳንድ ጉዳቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ግን ተጠቁሟል።

የጀርመኑ ተቋም በኤርትራ አዲ ቀይህ፣ ደቀማህረ፣ ከረን እና አሥመራ ከተሞች ውስጥ ርዕደ መሬቱ ተሰምቷል ያለ ሲሆን፣ በትግራይ ከተሞች ደግሞ አዲግራት እና መቀለን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም ንዝረቱ መሰማቱን አመልክቷል።

የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ በትግራይ በርካታ ከተሞች 5.5 ሬክተር ስኬል የተመዘገ የመሬት መንቀጥቀጥ ማጋጠሙን ዘግቧል።

ትግራይ ቴሌቪዥን በመቀለ፣ አክሱም፣ አዲግራት፣ ሽረ፣ አደዋ እና ውቅሮን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የመሬት መንቀጥቀጡ ተመዝግቧል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በኤርትራ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ሐምሌ መጀመሪያ ላይ እና ግንቦት አጋማሽ 2015 ዓ.ም. ላይ በእነዚህ አካባቢ አነስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሞ ነበር።

በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በተለያዩ አካባቢዎቻቸው ለርዕደ መሬት የተጋለጡ መሆናቸው ይነገራል።