በኢትዮጵያ ከተበራከቱት የኦንላይን ባንኪንግ አጭበርባሪዎች እንዴት እንጠበቅ?

ሞባይል የሚጠቀም ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ መዘመን ጋር ተያይዞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በበይነ መረብ (ኦንላይን) ባንኪንግ የሚጭበረበሩ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው።

በቅርቡም አንድ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ከ74 ሺህ የማያንሱ ሰዎች የኦንላይን ባንኪንግ የይለፍ ቃላቸውን መሰረቃቸውን ዘግቧል።

አጭበርባሪዎች እንደ የይለፍ ቃል (ፓስዎርድ) ያለ መሠረታዊ ግላዊ መረጃ እጃቸው ገባ ማለት ወደ ባንክ አካውንታችን በመግባት ከፍተኛ ኪሳራ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮችም የሞባይል ብንኪንግን በመጠቀም የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶች በመኖራቸው ደንበኞች እራሳቸውን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ ያሳስባሉ።

በአገሪቱ በቅርንጫፎች እና በደንበኞች ቁጥር ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከማጭበርበሪያ መንገዶች መካከል አንዱ ስልት በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት አማካኝነት የብድር አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚል የመረጃ ስርቆት መሆኑን ይገልጻል።

አጭበርባሪዎች ብድር የሚፈልጉ ደንበኞች በቅድም ተከትል በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት ኮድ እንዲያስገቡ ያዛሉ። በመጨረሻ ግን ተጠቃሚው ብድር ሳይሆን የሚያገኘው ገንዘብ ከሂሳቡ ተቀናሽ ይሆንበታል።

በአገሪቱ ካሉ የግል ባንኮች መካከል ቀዳሚ የሆነው አዋሽ ባንክም በተመሳሳይ በርካታ ደንበኞቹ በአጭበርባሪዎች እየተታለሉ መሆኑን ገልጿል።

ባንኩ አጭበርባሪዎች ከአዋሽ ባንክ የተደወለ በማስመሰል የሞባይል ባንኪንግ የአንድ ጊዜ መጠቀሚያ የምስጢር ቁጥር (የይለፍ ቃል) በማስላክ የተላከውን ቁጥር እየጠየቁ ደንበኞችን እያጨበረበሩ መሆናቸውን አመልክቷል።

spam

አጭበርባሪዎች የሚጠቀሙባቸው ስልቶች

ከላይ ከተጠቀሱት ምሳሌዎች አኳያ አንዱ ላይ በማተኮር የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እየገጠማቸው ያሉ እና በአሁኑ ወቅት በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ የማጭበርበሪያ መንገዶችን እንመልከት።

  • የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ልንሰጥዎ ነው በማለት ተጠቃሚዎች የሚነገራቸውን ኮድ ስልካቸው ላይ እንዲያስገቡ ማድረግ፤
  • በአገልግሎት ሰጪው ባንክ ተመዝግቦ ያለው የግል መረጃ ስህተት ስላለበት እንደ አዲስ እንመዝግብዎ በማለት የግል መረጃን መስረቅ፤
  • ሽልማት በማሸነፍዎ ሽልማቱን ለመቀበል ገንዘብ ይላኩ ማለት እንዲሁም
  • የሞባይል መተግበሪያ እናሻሽልዎ በለት የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ከተለመዱት ስልቶች መካከል ይገኙበታል።
spam

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አጭበርባሪዎች ሺህ ባሕሪያቸው ግን አንድ

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለምም አጭበርባሪዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የባንክ ማጭበርበር ወንጀሎች ሲፈጽሙ ኖረዋል።

አጭበርባሪዎች ቁጥራቸው ብዙ፤ የማጭበርበሪያ ዘዴዎቻቸው እልፍ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ አጭበርባሪዎች ተመሳሳይ የሆነ ባህሪ አላቸው።

ሕጋዊ መስሎ መቅረብ፡ የሚጠራውን ስልክ ሲያነሱ ከሚያውቁት ባንክ፣ ከመንግሥት ተቋም፣ ከሚታወቅ ድርጅት አንዳንዴም ከፖሊስ ጣቢያ መደወላቸውን ይገልጻሉ።

ያቻኩላሉ፡ አጭበርባሪዎች በማቻኮል ይታወቃሉ። የሚያጭበረብሯቸውን ሰዎች አእምሮ ለመቆጣጠር እያቻኮሉ ብዙ ትዕዛዝ ይሰጣሉ። እርስዎ ጊዜ ኖሮዎት እያደረጉ ያሉትን እንዳያሰላስሉ እያጣደፉ የፈለጉትን ይፈጽማሉ።

ወትዋች ናቸው፡ አጭበርባሪዎች የፈለጉት እስኪሳካ ድረስ ብዙ ይጥራሉ። ስልኮ ባይነሳ ደግመው ደጋግመው ይደውላሉ። የፈለጉትን ለማሳካት ረዥም ሰዓት መስመር ላይ ሊጠብቁ ይችላሉ።

መስጠንቀቂያ/ማስፈራሪያ፡ አጭብርባሪዎች ሌላው የሚለዩበት መንገድ ይህን ካላደረጉ ይህ ይከሰታል በሚለው ማስፈራሪያ አዘል ማስጠንቀቂያቸው ነው። ይህን ካላደረጉ በሕግ ይጠየቃሉ፣ የሚጠቀሙበትን መተግበሪያ ካላሻሻሉ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም. . . የሚሉ ማስጠንቀቂያ/ማስፈራሪያዎችን በማቅረብ የግል መረጃ ሊመነትፉ ይሞክራሉ።

ሐሰተኛ መና፡ እውነት ለማይመስል ነገር ቃል ይገባሉ። የ500 ሺህ ብር አሸናፊ ስለሆኑ ወደ ባንክ ሂሳብዎ ገንዘቡን ለማዘዋወር 50 ሺህ ብር ይክፈሉ የሚል በትህትና የተሞላ ጥያቄ ሊቀርብልዎ ይችላል።

በእነዚህ ሁኔታዎች በሞባይል አማካይነት የሚርቡልዎ ጥያቄዎች እና ስጦታዎች ግላዊ መረጃዎትን ወይም ገንዘብዎትም ለመውሰድ የሚደረጉ በመሆናቸው ፈጽሞ አይተባበሩ።

ሞባይል የሚጠቀም ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአጭበርባሪዎች እንዴት እራሳችንን እንጠብቅ?

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲህ ያሉ የማጭበርበር ሙከራዎች ሲደረግብዎ ሳይቻኮሉ ትኩረት በመስጠት እራስዎን ከአጭበርባሪዎች መታደግ ይቻላል ይላሉ።

መልዕክት ተላከልዎት? ወይስ ስልክ ተደወለ? እስቲ ረጋ ብለው ነገሩን ያጢኑ። ምንም አይነት እርምጃ ከመወሰድዎ በፊት ሁኔታውን ይመርምሩ፤ ከየት ተላከ/ተደወለ? ለምን? ይህ መልዕክት ለእኔ ሊላክ ይችላል? ለእኔ መደወል አለበት? ብለው ራስዎን ይጠይቁ።

የሚላኩልንን ሊንኮች (ማስፈንጠሪየዎች) በሙሉ ከመክፈት እና ለማየት ለመሞከር እንቆጠብ።

ከሚያውቁት ግለሰብ እንኳ አጠራጣሪ መልዕክት ከደረስዎ ያን ሰው በሌላ አማራጭ ለማግኘት ይሞክሩ፤ ምክንያቱም የዚያ ሰው ቴሌግራም ወይም ዋትስአፕ በአጭበርባሪዎች ተጠልፎ ይሆናልና።

በጽሑፍ መልክት ውስጥ አብሮ የሚመጣ ሊንክን ተከትለው መተግበሪያ ከማውረድ ይቆጠቡ። መተግበሪያ ማውረድ ከፈለጉ ይፋዊ የመተግበሪያ ማውረጃ ገጾችን በመጠቀም ያውርዱ።

አጠራጣሪ እና ከማጭበርባር የተያያዙ ጥያቄዎች ከቀረበልዎ እና ሙከራ ከተደረገብዎ ለሚለከተው አገለግሎት ሰጪ ተቋም እንዲሁም ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጉ።

አጭበርባሪዎች ብዙውን ጊዜ የሚያጨበረብሯቸውን ሰዎች የሚያጠምዱት በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ነው።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚመለከቱት ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል ነገርን ሁሌም በጥርጣሬ ቢመለከቱ እራሰዎን ይጠቅማሉ እንጂ አይጎዱም።

በተለይ ከባንክ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ሁልጊዜም ቢሆን ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶች መረጃ ማግኘት የሚኖርብዎ ወደ ባንኮች ቅርጫፎች በመሄድ፣ ባለ ሦስት ወይም አራት ዲጂት ስልክ ቁጥሮቻቸው ላይ በመደወል ወይም ወደ ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች እና ድረ-ገጾች በመሄድ ብቻ መሆን አለበት።