አሳሳቢ የሆነው በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ዝርፊያ እና የባንኮች ኃላፊነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አቶ እንዳለ ገ/መድኅን ከሚሰሩበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት የቁጠባ አገልግሎት በብድር ያገኙትን 200 ሺህ ብር ለጋራ መኖሪያ ቤት ቅድሚያ ክፍያ ለመክፈል በማሰብ በባንክ አስቀምጠው በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
ነገር ግን ምንም አይነካብኝም ብለው ያሰቡት ሁለት መቶ ሺህ ሊሞላ 5 ሺህ ብር የጎደለው ገንዘባቸው፣ ባልጠበቁት መንገድ በዘራፊዎች ከአካውንታቸው ተመንትፎ ለዘርፈ ብዙ ቀውስ መዳረጋቸውን ይናገራሉ።
አንድ ዕለት “ከባንክ ነው የምንደውለው” ያሉት ግለሰቦች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚያካሂደው “ይቆጥቡ ይሸለሙ” መርሃ ግብር የሞተር ሳይክል ሽልማት እንደደረሳቸው ተነገራቸው።
ቀጥሎም በወቅቱ ሞተር ሳይክሉን ሊሰጧቸው እንደማይችሉ ነገር ግን ገንዘቡን ሊያስገቡ እንደፈለጉ በመናገር የተለያዩ መረጃዎችን ጠየቋቸው። ይህንንም ተከትሎ አቶ እንዳለ የተጠየቁን ቁጥር ሁሉ ተናግረው በመጨረሻም በአቢሲኒያ እና በንግድ ባንክ አካውንቶቻቸው ውስጥ የነበረው 195 ሺህ ብር ተወስዶባቸዋል።
ይህ የአቶ እንዳለ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎች የገጠማቸው የማጭበርበር ድርጊት ነው። ዝርፊያው በተለይም የሞባይል ባንኪንግ አገልገሎት የሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ በርካቶች በተለያየ ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ እሮሮ ሲያሰሙ የከረሙበትም ጉዳይ ነው።
የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዚህ የማጭበርበር ድርጊት ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲሁም ክስ የተጀመረባቸው መዝገቦችን በተመለከተ ባደረገው ጥናት በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ ምዝበራዎች መበራከታቸውን አመልክቷል።
የሞባይል ባንኪንግን ጨምሮ በመዝገብ የተያዙት ወንጀሎች በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 1.9 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ማድረሳቸውን ጥናቱ አትቷል። በዝርዝሩም ከፍተኛ ዝርፊያ ያጋጠመው በንግድ ባንክ ሲሆን አቢሲኒያ ባንክ እና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ይከተላሉ።
በቼክ የሚፈጸሙ፣ በቁጠባ ሂሳብ ላይ፣ በሃዋላ በሚላክ ገንዘብ ላይ፣ የይለፍ ቃል ምንተፋ ብሎም በሌሎች መንገዶች ስርቆቱ እንደሚፈጸም ጥናቱ ያሳያል።
በሞባይል ባንኪንግ የሚፈጸመው ስርቆት በርካታ ስልቶች ያሉት ሲሆን ከተዋናዮቹ መካከል የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች እና ሌሎች የባንክ ሠራተኞች ጭምር እንደሚሳተፉበት ይገልጻል። ሠራተኞቹ ከደንበኞች አካውንት ጋር የራሳቸውን ወይም የዘመዶቻቸውን ብሎም የጓደኞቻቸውን ቁጥር በማያያዝ እና ሐሰተኛ ቅጽ በመሙላት ስርቆቱን እንደሚፈጽሙ ጥናቱ አመልክቷል።
በማሳያነት የተጠቀሰው መዝገብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፒኮክ መናፈሻ ቅርንጫፍ ሠራተኛ የሆነ አንድ ግለሰብ በባንኩ ደንበኛ ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀስ የቆየውን አካውንት በማንቀሳቀስ ስርቆት መፈጸሙን ያሳያል። ለዚህም ግለሰቡ ካስገቡት የሞባይል ባንኪንግ ቁጥር ውጪ ሌላ በማስገባት በአጠቃላይ 2.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ከግለሰቡ ሂሳብ ወስዷል ሲል ጥናቱ ያሳያል።
አክሎም የስርቆቱ ዋና ተዋናዮች የባንክ ኃላፊዎች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ነገር ግን መደበኛ የባንኩ ሠራተኞች አይሳተፉበትም ብሎ ለመደምደም ግን አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የባንክ ሠራተኞች ምን ይላሉ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ለዓመታት በባንክ ሥራ ላይ የቆዩ አንድ ግለሰብ እንደሚሉት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የባንክ ሠራተኞች ለእስር እየተዳረጉ ነው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በባንኮች ውስጥ ሆነው ወንጀሉን የሚፈጽሙ ሰዎች እንደማይያዙ ያክላሉ።
በባንኮች መካከል የቅልጥፍና ውድድር በመኖሩ ምክንያት የባንክ ሠራተኞች ሁልጊዜ የባንኩን የአሰራር ሥነ ሥርዓት እንደማይከተሉ የሚናገሩት እኚሁ ግለሰብ፤ በምሳሌነትም በሥርዓቱ መሰረት ያለ ባንክ ደብተር ገንዘብ መክፈል ባይቻልም በአብዛኛው የባንክ ደንበኞችን ለመያዝ በሚደረገው ፉክክር ያለ ደብተር ክፍያ መፈጸም እጅግ የተለመደ ነው ይላሉ።
በዚህም ሳቢያ አንድ ሰው ያለደብተር በመቅረብ አጭበርብሮ ገንዘብ ቢዘርፍ ከፋዩ ባለሙያ በኋላ ላይ ሲጣራ ተጠያቂ ሲሆን ባንኩም “ባስከመጥኩለት ሥርዓት መሰረት አልሰራም” በሚል አሳልፎ ይሰጠዋል ሲሉ ያስረዳል።
ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራ የሚካሄድበትን የቼክ ማጭበርበር ወንጀልንም ይመለከታል። ዝርፊያው ከተፈጸመ በኋላ ከፋዩ ወይም የቅርብ አለቃው ለእስር ይዳረጉ እንጂ፣ ዋነኛዎቹ አጥፊዎች ሌሎች እንደሚሆኑ ይናገራሉ።
“ባንኮች ትልልቅ ደንበኞቻቸውን ለመያዝ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ” የሚሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት የባንክ ባለሙያ፣ ቼክ ለመክፈል የሚያስፈልጉ ሂደቶችን በሙሉ ማሟላት ካስፈለገ አንድ ቀን ሙሉ ሊወስድ እንደሚችል በመጥቀስ “ይህ ደግሞ ትልልቅ ደንበኞችን ያርቃል” ይላሉ።
ታዲያ አንድ ግለሰብ ቼክ ፈርሞ ለተከፋይ ሲልክ ለባንኩ ቀድሞ ደውሎ ገንዘቡ እንዲዘጋጅ ካዘዘ በኋላ ገንዘብ የሚወስደው ግለሰብ ገንዘቡን ተቀብሎ ይሄዳል። ቼኩ ማለፍ ያለበት ሂደትን ግለሰቡ ገንዘቡን ይዞ ከሄደ በኋላ የሚከናወን ይሆናል። በአሰራሩ መሰረት ግን ቼኩን የተቀበለው የመጀመሪያው ሠራተኛ ወደ ደንበኛው በመደወል ካረገገጠ በኋላ በመፈረም ለቀጣይ አለቃው ያስፈርማል።
ቀጥሎም መስኮት ላይ ያለው ከፋይ በድጋሚ ፊርማዎቹን አረጋግጦ ይከፍላል። ነገር ግን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ባለው ፉክክር፣ በቅርብ አለቆቻቸው ዝርዝር ሂደትን እንዳይከተሉ የሚበረታቱት ከፋዮች መጨረሻ ወንጀል መፈጸሙ ሲታወቅ ግን ሂደቱን አልተከተሉም ተብለው ለእስር እንደሚዳረጉ እኚሁ በባንክ ሥራ የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው ግለሰብ ይናገራሉ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው የሞባይል ባንኪንግን መሰረት ያደረገ ዘረፋ ግን በርግጥም በባንኮች የአሰራር ግድፈት ጭምር የታገዘ መሆኑን ይናገራሉ።
“የስማርት ስልክ የሌለው፣ እንኳን ስልኩን አንብቦ አገልግሎቱን መፈጸም ቀርቶ ፊርማ እንኳን በአሻራ የሚፈርሙ ሰዎች የሞባይል ባንኪንግ አግልገሎት እንዲጠቀሙ እና እንዲመዘገቡ መደረጉ ለከፍተኛ ዝርፊያ ይዳርጋል” ሲሉም ይናገራሉ።
ቀጥሎም ገንዘብ ያለው እና የሌለው ሰውን እንዲሁም የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቱን የሚጠቀመውን እና የማየጠቀመውን በመለየት ለሦስተኛ ሰው አሳልፈው የሚሰጡት ራሳቸው በባንኮች ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ሰዎች እንደሆኑም ያስረዳሉ።
አሁን አሁን ከአካውንት ወደ ቴሌ ብር በማስላክ ዝርፊያውን ቀላል እንዳደረገውም ግለሰቡ ተናግረዋል። በዚህ ሂደት ሐሰተኛ መታወቂያ ከሚያወጡ የቀበሌ ሠራተኞች እስከ የባንክ ኃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸውም አልቀረም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞባይል ገንዘብ
የባንክ ግልጋሎቶች በዘመኑባቸው አገራት እንዲህ አይነት በባንክ አካውንት ላይ ብሎም የሞባይል ክፍያ አገልግሎቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ባንኮች ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ይሰራሉ። ከእነዚህም መካከል ከአንድ በላይ የሆነ የደንበኛውን ማንነት የማረጋጥ ሂደት ይጠቀሳል።
ከዚያ በመለስ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ሳይታክቱ ያስተምራሉ። የኢትዮጵያ ባንኮች ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን ኋላ ላይ የምንመለስበት ቢሆንም ለምን ይህንን ማደረግ አይፈልጉም ስንል ግን የባንክ ሠራተኛ የሆኑ ምንጫችንን ጠይቀናቸዋል።
“ገበያ ያርቅብናል ብለው ስለሚያስቡ ነው” ይላሉ። ይህም በተለይም እንደ ሞባይል ባንኪንግ ያሉ አገልግሎቶች ገና እየተለመዱ ያሉ ሲሆኑ ደንበኞች እንደዚህ አይነት ችግር ካለው ይቅርብን ብለው እንዳይተዉት በመስጋት መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ ዘላቂ እና አዋጭ መንገድ ነው ወይ ስንል የባንክ እና የኢኮኖሚ ባለሞያውን አብዱልመናን መሐመድን ጠይቀናቸዋል። ባንኮች ደንበኞቻቸውን ማስተማር እንደሚገባቸው እንዲሁም ይህ የማስተማር ሂደት በተገቢው የመገናኛ ዘዴ ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይም በዲጂታል ባንኪንግ ሥርዓት ወቅት ደንበኞችን ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ማጭበርበሮች ማስተማር ከፍተኛ ትርጉም አለው ይላሉ።

ባንኮች ኃላፊነት
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ያጠናው ጥናት በራሱ የባንኮችን ኃላፊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
“እነዚህ በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚያመሳስላቸው ነገር በአብዛኛው ከባንክ አሰራር ጋር ግንኙነት ያላቸው “የውስጥ ሠራተኞች’’ ሳይሳተፉባቸው የማይፈጸሙ ናቸው። የትኛውም ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አካውንቱ ላይ ገንዘብ ያለውን ከሌለው መለየት ያስፈልጋል” ሲል በግልጽ የባንኮች ተሳትፎን ያሳያል።
እንዲሁም እነዚህን መረጃዎች በዚህ ጥልቀት እና ስፋት ከአንዳንድ የባንክ ሠራተኞች ትብብር ውጪ ማግኘት የማይቻል መሆኑንም ጥናቱ ያትታል።
አብዱልመናን እንደሚሉት ባንኮች የደንበኞቻቸውን የግል መረጃዎች የመጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ በአብዛኛውም ይህንን እንደሚፈጽሙ ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ እምነት የማይጣስበት አጋጣሚ የለም ማለት እንዳልሆነ ያክላሉ። ጨምረውም ይህንን ለመፍታትም ባንኮች በሚጠቀሙባቸው ሥርዓቶች ውስጥ ሠራተኞቻቸው ለመጥፎ አላማ ሊያውሏቸው የሚችሉ ክፍተቶችን የመሙላት አስፈላጊነትን አጽንኦት ይሰጣሉ።
እንዲሁም መንግሥት ሕጎቹን በመከለስ በባንኮች ውስጥ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ያለ አግባብ እንዳይመዘብሩ ማድረግ ይገባዋል፤ እንደ ባለሙያው ገለጻ። ይህ ካልሆነ ግን ከደንበኞች ባሻገር እንዲህ ያሉ ተግባራት ባንኮች ላይ የሚጣለውን አመኔታ በመሸርሸር ለበለጠ ችግር ሊዳርጋቸው እንደሚችልም ይናገራሉ። ይህ በጥቅሉ ኢኮኖሚውን በመጉዳት ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።
ነገር ግን እነዚህ ችግሮች እስከሚፈቱ ድረስ ደንበኞች በአጭበርባሪዎች መበደላቸው ብሎም ክስ ከመመስረት ውጪ ገንዘባቸውን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
በምሳሌነትም አቶ እንዳለ ለፖሊስ ያላቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ይዘው ቢያመለክቱም፣ እስካሁን የተያዘ ተጠርጣሪ ያለመኖሩ ያሳስባቸዋል። ነገር ግን አሁንም በብድር ያገኙትን ገንዘባቸውን የሚያስመልስላቸው ፍትህ እየተጠባበቁ ነው።
ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተደራርቦ ይህን ያህል ገንዘብ ማጣታቸው ከባድ ቀውስጥ ውስጥ እንደከተታቸው የሚገልጹት አቶ እንዳለ፣ ባዶ እጃቸውን ቢቀሩም “ያው እዳ ስለሆነ ከደመወዜ እየተቆረጠ መክፈል መች ይቀርልኛል?” ሲሉ በተስፋ መቁረጥ ይናገራሉ።












