ፖፕ ፍራንሲስ በፖርቹጋል በካቶሊክ ካህናት ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ጋር ተወያዩ

የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ በፖርቹጋል በካቶሊክ ካህናት ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ጋር ተወያዩ።

ፖፕ ፍራንሲስ በአገሪቷ ለአምስት ቀናት ባደረጉትም ጉብኝት የካቶሊክ ካህናት ጥቃት ሰለባዎችን እንዳደመጡም ቫቲካን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የፖፑና የጥቃት ሰለባዎቹ ውይይት ረቡዕ ዕለት እንደተካሄደም ተገልጿል።

በዚህ ዓመት በወጣ ሪፖርት መሰረት በፖርቹጋል ቢያንስ 4 ሺህ 815 ህጻናት ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ ቤተ ክርስቲያኗ ጥቃቶቹ ይፋ እንዳይሆንና ለመደበቅ “ስልታዊ በሆነ መንገድ” እንደንተቀንሳቀሰችም አክሏል።

በሊዝበን በተካሄደው የምሽት አገልግሎትም ላይ ፖፕ ፍራንሲስ ቤተ ክርስቲያን “የተጎጂዎችን አሳዛኝ ህመም” ልትሰማ ይገባታል ሲሉም ተደምጠዋል።

አክለውም ይህ ቅሌት “ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንድናይና በንስሃናና በንጽህና ህይወት እንድንኖር የሚጠይቅ ነው” ብለዋል።

የወሲብ ጥቃቶቹ ያስነሳው መጠነ ሰፊ ቁጣም ከካቶሊክ እምነት ለመራቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በፖርቹጋል በተካሄደው ውይይት 13 የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች የተካተቱበት ሲሆን ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀ መሆኑን ቫቲካን አስታውቋል።

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው የፖርቹጋል ቤተ ክርስቲያንም ባለስልጣናት በዚህ ውይይት ተሳታፊ ሆነዋል።

በየካቲት ወር በፖርቹጋል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመ ገለልተኛ ኮሚሽን በካቶሊክ ካህናት ወይም በሌሎች የቤተ ክርስቲያና ባለስልጣናት ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸውን 564 ህጻናት ያጋጠማቸውን በሪፖርቱ አትሟል።

በሌሎች አሜሪካና የአውሮፓ አገራት እንደተደረገውም ከጎሮጎሳውያኑ 1950 ጀምሮ የነበሩ ጥቃቶችን ወደኋላ ተመልክቷል።

በዚህ ሪፖርት እንደተካተተው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ በአጠቃላይም የጥቃቱ ሰለባዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት የህጻናት የስነ አዕምሮ ሐኪም ፔድሮ የተሰጠው አኃዝ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነና ሰለባዎቹ በጣም ከፍተኛ ቁጥር እንዳላቸው ተናግረዋል።