ዴንማርክ የመከላከያ በጀቷን ለመደጎም ሃይማኖታዊ የበዓል ቀንን ሰረዘች

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
የዴንማርክ ፓርላማ ወጪን በመቆጠብ የአገሪቱን ወታደራዊ በጀት ለማጠናከር ለዘመናት ሲከበር የነበረን ሃይማኖታዊ በዓል እንዲቀር ወሰነ።
የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በፀደይ ወቅት የሚከበረውንና “ታላቁ የጸሎት ቀን” ተብሎ የሚታወቀውን ሃይማኖታዊ ብሔራዊ በዓል እንዲቀር በድምጽ ብልጫ ወስነዋል።
የዴንማርክ ምክር ቤት እንደራሴዎች የበዓሉ መቅረት ወጪን ይቀንሳል በሚል የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ 95 ለ 68 በሆነ ድምጽ ተቀብለውታል።
የበዓሉ መሰረዝ ሦስት ቢሊዮን ክሮነር (የዴንምርክ ገንዘብ) ወይም 427 ሚሊዮን ዶላር ወጪን የሚያስቀር ሲሆን፣ ይህም ወደ አገሪቱ የመከላከያ በጀት ገቢ እንደሚደረግ መንግሥት አስታውቋል።
የውሳኔ ሐሳቡ ለፓርላማው በቀረበበት ጊዜ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ከሠራተኞች ማኅበራት እና ከሃይማኖት መሪዎች በኩል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
በተጨማሪም ይህንን የመንግሥትን ዕቅድ እና ውሳኔን በመቃወም 50,000 የሚሆኑ ሰዎች በአገሪቱ ምክር ቤት ደጃፍ ላይ ተገኝተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ማክሰኞ ዕለት ክርክር በተካሄደበት ጊዜ ካርስተን ሆንጌ የተባሉት የሶሻሊስት ፒፕልስ ፓርቲ አባል “ሌባውን አስቁሙ” ሲሉ ተቃውሟቸውን እንዳሰሙ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ጨምረውም በዚህ ውሳኔ “ሕዝቡ ተጨማሪ አንድ ቀን እንዲሰራ መንግሥት እያዘዘ ነው” ብለዋል።
ቢሆንም ግን በውሳኔው ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የሚያስችል በቂ ተቃውሞ ባለመቅረቡ ለዘመናት በብሔራዊ ደረጃ ሲከበር የነበረው በዓል እንዲሰረዝ በቀጥታ በምክር ቤቱ ተወስኗል።
ምንም እንኳን ተቃውሞ ቢቀርብበትም የዴንማርክ መንግሥት የሚገኘውን ተጨማሪ ገንዘብ ለመከላከያ በማዋል ኔቶ ካስቀመጠው ግብ ላይ በቶሎ ለመድረስ አልሟል።
ኔቶ ዴንማርክ ለመከላከያ የምታውለው በጀት አውሮፓውያኑ 2033 ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርቷ 2 በመቶውን እንዲይዝ ግብ አስቀምጧል።
ነገር ግን መንግሥት ብሔራዊ በዓልን በማስቀረት በሚያገኘው ተጨማሪ ገቢ ከሦስት ዓመታት ቀደም ብሎ በ2030 ግቡ ላይ ለመድረስ አቅዷል።
የዴንምርክ መንግሥተ እንዳለው ይህ የዕቅድ ለውጥ የመጣው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዴንምርክ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በየዓመቱ አስከ 11 የሚደርሱ የብሔራዊ በዓላት እረፍት ቀናት አሏቸው።
“በዓመት ውስጥ አንድ ተጨማሪ ቀን መሥራት ችግር አለው ብዬ አላስብም” በማለት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ውሳኔውን ደግፈውታል።












