የመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያን ጥያቄ እንዳይቀበል የመብት ተሟጋቾች ጠየቁ

የተመድ ስብሰባ

የፎቶው ባለመብት, UN

ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶች ላይ የሚደረገውን ምርመራ እንዲቋረጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረትን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት እንዳይቀበሉት ጥሪ አቀረቡ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋችን ጨምሮ ሌሎችም ከስድሳ በላይ የሚሆኑት ተቋማት ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ በተመድ የሚከናወነው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ እንዲቋረጥ ለማድረግ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ማቀዷ አሳስቦናል ብለዋል።

ይህ የሲቪል ማኅበራቱ እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ጥሪ የተሰማው የተባበሩት መንግሥታtእ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጄኔቭ ለአምስት ሳምንታት በሚያካሂደው ስብሰባው ስለሰሜን ኢትዮጵያው ጉዳይ እንደሚወያይ ከተገለጸ በኋላ ነው።

ሮይተርስ የዜና ወኪልም እንዲሁ ኢትዮጵያ በድርጅቱ የተሰየመው ኮሚሽን ሥራ እንዲቋረጥ ለምታቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ድጋፍ እያሰባሰበች ስለመሆኑ አምስት ዲፕሎማቶች ነገረውኛል ሲል ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ተፈጽሟል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተሰየመውን የተባባሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን ከምሥረታው ጀምሮ ስትቃወም ቆይታለች።

ኢትዮጵያ የባለሙያዎቹ አሰያየም ፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ነው በማለት ኮሚሽኑ በጀት እንዳያገኝም ጥረት አድርጋ ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አገራቸው ኢትዮጵያ ‘ትክክለኛ ውክልና’ የለውም የምትለው ኮሚሽን እንዲበተን የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ለኅብረቱ አባላት ጥሪ አቅርበው ነበር።

ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ ያቀረቡት ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት እና የመብት ተሟጋች ግን የኢትዮጵያ ጥረት ‘ያልተጠበቀ’ እና ዓለም አቀፍ ምርመራን ለማስቀረት የሚደረግ ጥረት ነው ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎችም ባወጧቸው ሪፖርቶች ማሳወቃቸው ይታወሳል።

የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም እና ሌሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዚህ ጦርነት የተፈጸሙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ጥሰቶች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ነበር።

ሦስት አባላት ያሉት ኮሚሽን ምርመራውን ከጀመረ በኋላ በጦርነቱ የተሳተፉ ተዋጊዎች የጦር ወንጀል እና ሌሎች የመብት ጥሰቶችን ስለመፈጸማቸው የሚያሳምኑ መረጃዎችን ማግኘቱን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በመላው ዓለም የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት ያለባቸው የ47 አገራት ስብስብ ነው።