የናይጄሪያን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቦላ ቲኑቡ ማሸነፋቸው ታወጀ

ቦላ ቲኑቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የናይጄሪያን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ እጩ ቦላ ቲኑቡ አሸናፊ መሆናቸው ታወጀ።

የ70 ዓመቱ አዛውንት ከተሰጡት ድምጾች 36 በመቶ የሚሆነውን ማግኘታቸውን ይፋዊ የምርጫ ውጤቶች አሳይተዋል።

ዋነኛ ተቀናቃኞቻቸው አቲኩ አቡበከር 29 በመቶ እንዲሁም የሌበር ፓርቲ እጩ ፒተር ኦቢ 25 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከመደረጉ በፊት ሦስት ፓርቲዎች ምርጫው የተጨበረበረ ነው በማለት ዳግም ምርጫ ይካሄድ ሲሉ ከምርጫው እራሳቸውን አግልለዋል።

ዋነኛ ተቃዋሚዎቹ ፒፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ፒዲፒ) እና ሌበር ፓርቲ አዲሱ የኤሌክትሮኒክ የመራጮች ሥርዓት ላይ ግልጽነት የጎደለው ሁኔታ አይተናል ካሉ በኋላ የምርጫ ውጤት ከሚነገርበት አዳራሽ ለቅቀው ወጥተው ነበር።

በናይጄሪያ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ የመራጮችን ማንነት ለመለየት ጥቅም ላይ ሲውል ይህ የመጀመሪያው ነው።

የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን ግን የእነዚህን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል።

ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ቲኑቡ ናይጄሪያ ካፈራቻቸው ባለጸጋ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ የሌጎስ ግዛት አስተዳዳሪም ነበሩ።

ቲኑቡ የትውልድ አካባቢያቸው በሆነው ደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኙ ግዛቶች አሸናፊ ሆነዋል።

ቲኑቡ ለሁለት የስልጣን ዘመናት አገሪቱን ሲመሩ ከቆዩት ፕሬዝዳንት ሞሐመዱ ቡሃሪ የሚረከቧት የምጣኔ ሃብት እድገት የተቀዛቀዘባት፣ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር የጨመረባት እና የጸጥታ ችግር ያለባትን ናይጄሪያ ነው።

ይህ ምርጫ በናይጄሪያ ወታደራዊ አገዛዝ እአአ 1999 ካበቃ በኋላ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል ተብሏል።