የአፕል የመጀመሪያው ትውልድ አይፎን በ63 ሺህ ዶላር በጨረታ ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, LCG AUCTIONS
ካረን ግሪን ከ15 ዓመታት ገደማ በፊት እአአ 2007 አይፎን ስልክ በስጦታ ካገኘች በኋላ ብዙዎች የሚያደርጉትን አላደረገችም፤ አልከፈተችውም።
ግሪን በስጦታ የተቀበለችውን ስልክ ሳትከፍተው አስቀመጠችው።
አፕል ለገበያ ካቀረባቸው የመጀሪያው ትውልድ አይፎን ስልኮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ስልክ በወቅቱ የተገዛው 599 የአሜሪካን ዶላር ነበር።
ከቀናት በፊት ግን ይህ ለዓመታት ሳይከፈት የተቀመጠው ስልክ በ63ሺህ 356 ዶላር (ከ3.3 ሚሊዮን ብር በላይ) ተሽጧል።
“ኦርጅናል የሆነ፣ በ2007 ለገበያ የቀረበ፣ ፋብሪካው እንዳሸገው ማግኘት በእውነት አስደናቂ ነገር ነው” ሲሉ አጫራቹ ማርክ ሞንቴሮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አጫራች ድርጅቱ የጨረታውን መነሻ 2ሺህ 500 ዶላር አድርጎ የነበረ ሲሆን 'ጥንታዊው' ስልክ እስከ 50ሺህ ዶላር ይሸጣል የሚል ግምት ተሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ሰዎች 28 ግዜ ከተጫረቱ በኋላ ስልኩ ከ63ሺህ ዶላር በላይ ተሽጧል። ስልኩን ማን እንደገዛው የተባለ ነገር የለም።
ካረን ግሪን አዲስ ሰራ ማግኘቷን በማስመልከት ነበር ጓደኞቿ እንኳን ደስ ያለሽ ለማለት ባለ 8 ጊጋ ባይት ስልክ በስጦታ መልክ የሰጧት። ይሁን እንጂ ግሪን ሌላ ስልክ ገዝታ ስለነበረ አይፎን ስልኩን ሳትከፍተው እንዳሰቀመጠችው በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግራለች።
“አይፎን ነው። ስለዚህ ግዜ ሊያልፍበት እንደሚችል አልገመትኩም” ስትል በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግራለች።
ለእርሷ መልካም ሆኖ ስልኩ ‘ግዜው አልፎበት’ ተፈላጊነቱ እንዲጨምር ምክንያት ሆኖላታል።
ግሪን አዲስ ለጀመረችው ንግድ ገንዝብ አስፈልጓት እንጂ ስልኩን ይዛው ብትቆይ የበለጠ ልታተርፍበት እንደምትችል ለቢዝነስ ኢንሳይደር ተናግራለች።
ለአፕል ምርት ፍቅር ያላቸው ግለሰቦች ለምርቶቹ ከፍ ያለ ገንዘብ ሲከፍሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከዚህ ቀደም ግሪን ከሸጠችው ስልክ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ያልተከፈቱ የመጀመሪያ ትውልድ አይፎን ስልኮች በ40ሺህ እና 35ሺህ ዶላር ተሽጠው ነበር።
ባለፈው ዓመት 1970ዎቹ ዲዛይን የተደረገ የአፕል ኮምፒዩተር ፕሮቶታይፕ ከ677ሺህ ዶላር በላይ ተሽጦ ነበር።












