ዲግሪውን ለዩኒቨርስቲው ለመመለስ የወሰነው የምህንድስና ምሩቅ

አሰፋ አለሙ

የፎቶው ባለመብት, Asefa Alemu

በተማረበት ሙያ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ የቀን ሠራተኛ የሆነው የምህንድስና የማዕረግ ተመራቂ የትምህርት ማስረጃውን ላስተማረው ዩኒቨርሲቲ ለመመለስ መወሰኑ ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።

አሰፋ አለሙ ከሦስት ዓመታት በፊት ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና በማዕረግ ቢመረቅም በተማረበት ዘርፍ ተቀጥሮም ይሁን በግሉ ለመሥራት ያደረገው ጥረት ፍሬ ባለማፍራቱ የትምህርት ማስረጃውን ለመመለስ ምክንያት እንደሆነው ለቢቢሲ ተናግሯል።

በሲቪል ምህንድስና በማዕረግ መመረቄ “በሕይወቴ ለውጥ አላመጣም” የሚለው አሰፋ፤ አሁን ላይ በቀን ሠራተኝነት በሚያገኘው ገቢ እና ከእናቱ የእርሻ መሬት ከሚገኘው ገቢ ሕይወትን ለመግፋት መገደዱን ይገልጻል።

በአሁኑ ወቅት ኑሮውን በትውልድ አካባቢው ደብረ ማርቆስ ያደረገው አሰፋ፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ የሲቪል ምህንድስና ለማጥናት አሶሳ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀሉን ያስታውሳል።

አባቱን በሞት ለተነጠቀው እንዲሁም ወላጅ እናቱ መነኩሴ ለሆኑት ተማሪ አሰፋ፤ የዩኒቨርሲቲ ቆይታው ቀላል አልነበረም።

“በጓደኞቼ [በሌሎች ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች] ድጋፍ ነው ትምህርቴን ተከታትዬ የጨረስኩት” ይላል።

አሰፋ የሲቪል ምህንድስና ድግሪውን ያጠናቀቀው 3.45 አጠቃላይ ነጥብ በማስመዝገብ ነበር።

ከዩኒቨርሲቲ ሲወጣ በግል የኮንስትራክሽን ዘርፍ በመሰማራት ስኬታማ የመሆን ህልም እንደነበረው የሚናገረው አሰፋ፤ እንኳንስ ያሰበውን ማሳካት ቀርቶ ሥራ አጥ መባል አሳቆት ወደ ትውልድ ቀዬው እንኳ መመለስ እንደሚያሳፍረው ይናገራል።

አሰፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ፣ ቆላ አይሹ ተብላ በምትጠራ ገጠራማ ቦታ ነው።

“ከአንድ ሰዓት በላይ በእግር እየተጓዝኩ ነው የተማርኩት። በትምህርቴ የደረጃ ተማሪ ነበርኩ። ከ3ኛ እስከ 5ኛ ያለ ደረጃን ይዤ ነው ዩኒቨርሲቲ የገባሁት።” ይላል።

አሰፋ ሥራ አጥ መሆኑ ከእርሱ በተጨማሪ ለሚያውቁት የመንደሩ ሰዎች ሞራል የሚጎዳ ይሆናል ሲልም የችግሩን ግዝፈት ያስረዳል።

“አሁን ያለሁት ደብረ ማርቆስ ነው። ወደተወለድኩበት የገጠር ቀበሌ አልሄድም። የማልሄድበት ምክንያት ለአካባቢው አርዓያ የምባል ተማሪ ነበርኩ። አሁን ‘እነ አሰፋ ተመርቀው ሥራ አልያዙም’ እየተባለ ስለሆነ

ልጆች ትምህርት የሚጠሉበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ወደ ተወለድኩባት ቦታ ከዩኒቨርሲቲ ከተመርቅኩ ጊዜ ጀምሮ አልሄድኩም” በማለት ጉዳቱ የእሱ ብቻ እንዳልሆነ ይናገራል።

አሰፋ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ከትውልድ አካባቢው በተጨማሪ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎች ሥራ ፍለጋ ብዙ መንከራተቱን፤ ብዙ የሥራ ማመልከቻ ማስገባቱን እና የሥራ ቅጥር ፈተና ላይ ቢቀመጥም በመንግሥትም ሆነ በየግል ድርጅት ውስጥ ሥራ ማግኘት አለመቻሉን ይናገራል።

የ29 ዓመቱ አሰፋ የሥራ ማመልከቻ ከማስገባት አልፎ ሥራ የማግኘት ዕድልን ሊፈጥር ይችላል በሚል በበጎ ፍቃደኝነት ወደ ኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ሄዶ ለወራት ማገልገሉን ይገልጻል።

ከጎጃም እስከ አዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ጅግጅጋ በትምህርት ቤቶች ጭምር በመምህርነት ለመቀጠር ያደረገው ጥረት አለመሳካቱንም ያስረዳል።

“ከትምህር ቤቶች እስከ የግል ድርጅቶች አልፎም የመንግሥት ተቋም ድረስ ማመልከቻ ያላስገባሁበት ቦታ የለም” የሚለው አሰፋ፣ ከአንድ ተቋም ውጪ ለፈተና እንኳ የጠራው ቀጣሪ እንደሌለ ይናገራል።

ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎት እና አቅም እንዳለው ለሚያምነው አሰፋ፤ ተወዳድሮ ሥራ እንዳያገኝ ያደረገው ምክንያት ብልሹ አሰራር መሆኑን ያምናል።

“ወይ ገንዘብ ወይም ዘመድ ከሌላ ሥራ ማግኘት አይቻልም” በማለት የቅጥር ሂደቶች ፍትሃዊ ባለመሆናቸው የሥራ ዕድል ማግኘት አለመቻሉን ይገልጻል።

በዚህም አሰፋ ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ የተሰጠውን ዲግሪ ምንም አልጠቀመኝም በማለት ለዩኒቨርስቲው ሊመልስ መሆኑን ተናግሯል።

አሰፋ አለሙ

የፎቶው ባለመብት, Asefa Alemu

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ከአማራ ክልል ወደ አሶሳ የሚወስደው መንገድ ዝግ ስለሆነ መሄድ አልቻልኩም። በአውሮፕላን እንዳልሄድ ገንዘብ የለኝም። መሄድ ስችል እመልሰዋለሁ” ይላል የትምህርት ማስረጃውን።

“ቅጥር ፈልጌ አልተሳካም። በግል የሆነ ነገር ፈጥሬ ለመስራት ስለከበደኝ የትምህርት ማስረጃዬ ጥቅም እንደሌለው ማሳየት እፈልጋለሁ።”

አሰፋ ዲግሪውን ለዩኒቨርሲቲው መመለስ የፈለገው “የተንሰራፋውን ሙስና በገሃድ እንዲያሳይልኝ ነው” በማለት እሱና እሱን የመሳሰሉ ምሩቃን ያሉበት ሁኔታ ትኩረት እንዲያገኝ ፈልጎ ነው።

“31ሺህ ብር አካባቢ የወጪ መጋራት ዕዳ አለብኝ። አሁን 40 ምናምን ሺህ ሊደርስ ይችላል [ከወለድ ጋር]። የትምህርት ማስረጃውን መመለሴም መንግሥት ‘ዕዳ ይከፍላል’ ብሎ እንዳይጠበቅ እና የመክፈል አቅም እንደሌለኝ የማሳውቅበት አጋጣሚም ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የትምህርት ማስረጃ መመለስ የሚል ይፋዊ አሰራር እንደሌለ ቢረዳም “ሕግ የለም ብዬ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም” የሚለው አሰፋ፤ የትምህርት ማስረጃውን ለመመለስ ሲሄድ ከዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን ምላሽ “በጋራ የምናየው ይሆናል” ብሏል።

አሰፋ በ2011 ዓ.ም. ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ ቢመረቅም ያለፉትን አራት ዓመታት ሥራ በመፈለግ አሳልፏል።

ወደ አርባ ከሚጠጉ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በተለያየ ዘርፍ ያስመርቃሉ። በዚህም በርካቶቹ ከተመረቁባቸው መስኮች ውጪ በተለያዩ ሥራዎች ሕይወትን እየመሩ መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት ተሰምቷል።

የአሰፋ ለየት የሚለው በማዕረግ በተመረቀበት የምህንድስና ሙያ ለአራት ዓመታት መሥራት ባለመቻሉ “አልጠቀመኝም በሚል” የትምህርት ማስረጃውን ለመመለስ መወሰኑ ነው።