በፓሪስ ኦሊምፒክ የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ውድድር ምን ተፈጠረ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት ሰኞ ምሽት ሐምሌ 29/ 2016 ዓ.ም በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የፓሪስ ኦሊምፒክ የሴቶች የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር በድራማዎች የተሞላ ነበር።
ኬንያ በቢትሪስ ቼቤት አማካይነት ወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ኢትዮጵያ በርቀቱ ከዓመታት በኋላ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ሳትችል ቀርታለች።
በውድድሩ ሁለተኛ የወጣችው ሌላኛዋ ኬንያዊት ፌይዝ ኪፕዬጎን ስትሆን፣ የኔዘርላንዷ ሲፈን ሃሰን ደግሞ ሦስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
ቼቤት ውድድሩን 14 ደቂቃ 28.56 ሰከንድ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዳለች።
የዓለም ሻምፒዮናዋ ኪፕዬጎን በውድድሩ ላይ የጉዳፍ ፀጋይን መንገድ በመዝጋት በሚል ውጤቷ እንዲሰረዝ ተደርጎ ነበር።
በኋላ ላይ ኬንያ ይግባኝ በመጠየቋ አትሌቷ የተነጠቀችው የብር ሜዳሊያ እንዲመለስላት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተከሰተው ምንድን ነው?
የአምስት ሺህ ሜትር ውድድሩ እስከመጨረሻው ድረስ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ነበር።
ኪፕዬጎን ውድድሩ ሊጠናቀቅ አራት ዙሮች ሲቀሩት ወደፊት ቀድማ ወጣች።
ሁለት ዙሮች ሲቀሩት ጉዳፍ ወደፊት ለመውጣት ባደረገችው ሙከራ ከኬንያዊቷ ጋር ይጋጫሉ።
ከዚህ በኋላ ጉዳፍ ወደኋላ ስትቀር ሁለቱ ኬንያውያን ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ፉክክር ቼቤት ቀዳሚ ለመሆን ቻለች።
ሁለቱ ኬንያዊያን የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው በስታድ ደ ፍራንስ ከታደመው ሕዝብ ጋር ደስታቸውን ገለጹ።
በኋላ ላይ ግን የኪፕዬጎን ውጤቷ መሰረዙ እና የብር ሜዳሊያው ለሲፈን ሃሰን እንደሚሰጥ ተገለጸ።
ናዲያ ባቶክሌቲ ደግሞ የነሐሴ ሜዳሊያ አሸናፊ ተባለች።
ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረገችው ቼቤት ከውድድሩ ላይ ከጉዳፍ ጋር የተጋጨችው የአገሯ ልጅ ውጤቱ ሊመለስላት እንደሚችል ያላትን ተስፋ ገለጸች።
“የእሷ ጥፋት አይደለም። እኔ ከኋላቸው ነበርኩኝ። ፌይዝ የውስጠኛውን መስመር ይዛ ነበር የምትሮጠው። ጉዳፍ ደግሞ ወደ ፌይዝ መስመር ለመግባት ሞከረች” ብላለች ቼቤት።
“ፌይዝ እጆቿን ተጠቅማ ‘አትግፊኝ’ ስትል ለጉዳፍ ነገረቻት። ይሄ የፌይዝ ጥፋት አይደለም። ሚዛኗን ስታ ከመስመር ለላመውጣት ሞክራለች” ስትል አክላለች።
ከሁለት ሰዓታት በኋላ ግን ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ጉዳዩን ተመልክቶ ኬንያዊቷ ውጤቷ እንዲመለስላት በማለት የብር ሜዳሊያው ለኪፕዬጎን እንዲሰጥ ወሰነ።
አትሌቷ ውጤቱ ቢመለስላትም እስከ ውድድሩ ፍጻሜ ድረስ አብሯት የሚቆይ ቢጫ ካርድ እንዲሰጣት ፌደሬሽኑ ወስኗል።
በቀጣይ ቀናት በ10 ሺህ እና በማራቶን ለመወዳደር ጭምር የተዘጋጀችው ሲፈን ውሳኔውን መቀበሏን አስታውቃለች።
“ፌይዝ ውጤቷ ስለተመለሰላት ደስተኛ ነኝ። የብር ሜዳሊያው ይገባኛል ብዬ አላስብም። ያላሸነፍኩትን ሜዳሊያ መውሰድ አልፈልግም” ብላለች ሲፈን ከውሳኔው በኋላ።
“የነሐስ ሜዳሊያን እወደዋለሁ። ሚዛናዊነት እስካለ ድረስ ሜዳሊያ ሆነ ሌላ ውጤት ባስመዘግብ ችግር የለውም” ብላለች።
በውድድሩ ላይ እጅጋየሁ ታዬ 6ኛ፣ መዲና ኢሳ 7ኛ እንዲሁም ጉዳፍ ፀጋይ 9ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።
ፌይዝ ኪፕዬጎን ቀጣይ ትኩረቷን በ1500 ሜትር ሦስተኛውን ወርቅ ሜዳሊያዋን ለማግኘት ትወዳደራለች።












