ቲክቶክ በመጪው እሁድ በአሜሪካ አገልግሎቱን እንደሚያቆም አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቲክቶክ የተጣለበት እገዳ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት መንግሥት ጣልቃ ካልገባ በስተቀር ከመጪው እሁድ ጀምሮ መተግበሪያውን በአሜሪካ ቀጥ ለማድረግ እንደሚገደድ አስታወቀ።
ኩባንያው አርብ አመሻሽ፣ ጥር 9/ 2017 ዓ.ም ላይ በሰጠው መግለጫ ዋይት ሃውስ እና የፍትህ ዲፓርትመንት "ቲክቶክ በቀጣይነት እንዲቀጥል ለማህበራዊ ሚዲያው መሰረታዊ የሚባሉ ግልጽነት እና ማረጋገጫ መስጠት ተስኗቸዋል" ብሏል።
መንግሥት በአስቸኳይ አጫጭር ቪዲዮዎች ማጋሪያ የሆነውን ማህበራዊ ሚዲያ የተጣለበትን እገዳ በመጣሱ እንደማይቀጣ ጣልቃ ገብቶ ማረጋገጫ ካልሰጠው በስተቀር እሁድ፣ ጥር 11/ 2017 ዓ.ም "መተግበሪያውን ለማጨለም እገደዳለሁ" ብሏል።
በቻይና መቀመጫውን ያደረገው ወላጅ ኩባንያው ባይትዳንስ ቲክቶክን እስከ መጪው እሁድ ካልሸጠ በስተቀር ማህበራዊ ሚዲያው በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዳይውል የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አርብ ዕለት መወሰኑን ተከትሎ ነው ኩባንያው ይህንን መግለጫ ያወጣው።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ባይትዳንስ የተጣለውን እገዳ ለማስቀረት የአሜሪካውን ቲክቶክ ለገለልተኛ አካል መሸጥ እንዳለበት የሚበይን አንድ ሕግ ጸድቋል።
ቲክቶክ በበኩሉ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ 170 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹን ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ሕጉን አጥብቆ ተቃውሟል።
ነገር ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ የአሜሪካው ቲክቶክ በሚቀጥሉት ቀናት እስካልተሸጠ ድረስ ማህበራዊ ሚዲያው ከተንቀሳቃሽ ስልኮች መተግበሪያዎች እንዲወርዱ ይደረጋል ተብሏል።
እገዳው አስቀድሞ በስልካቸው ላይ ቲክቶክን የጫኑ ተጠቃሚዎችን አይጎዳም የሚል እሳቤ ነበር። ነገር ግን እገዳው ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የመተግበሪያው ማሻሻያዎች የማይገኙ ከመሆናቸው አንጻር የማህበራዊ ሚዲያው በጊዜ ሂደት ከጥቅም ውጭ ይሆናል ተብሎ ነበር።
ሆኖም ቲክቶክ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ለነባር ተጠቃሚዎችም ሆነ መተግበሪያውን አውርደው መጫን ለሚፈልጉ አዳዲስ ተጠቃሚዎች በአስቸኳይ አገልግሎቱን እንደሚያቆም ጠቁሟል።
የማህበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እገዳው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የስንብት ቪዲዮዎቻቸውን ለተከታታዮቻቸው ሲለጥፉ ቆይተዋል።
የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ዘመን በመጪው ሰኞ ማብቃቱን ተከትሎ ይህንን እገዳ የማስከበር ኃላፊነት በተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚወድቅ ዋይት ሃውስ ከዚህ ቀደም አስታውቋል።
በመጀመሪያ እርምጃውን ደግፈውት የነበሩት ትራምፕ እገዳውን እንደሚቃወሙ ጠቁመዋል።
"በቲክቶክ ላይ ያለኝን ውሳኔ በቅርብ ይፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ሁኔታውን ለመገምገም ጊዜ ያስፈልገኛል" ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።
ትራምፕ አክለውም ከቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ቲክቶክን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ አገሪቱ ባደረገችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወጣት መራጮችን ለመድረስ ቲክቶክ እንደረዳቸው ገልጸዋል። ትራምፕ የሰጡት ይህ አስተያየት በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ቲክቶክን ለማገድ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ካወጡበት አቋማቸው በእጅጉ የራቀ ነው ተብሏል።
ባይትዳንስ ቲክቶክን ላለመሸጥ ቃል ገብቶ በአሜሪካ ያለውን አገልግሎት ከእሁድ ጀምሮ እዘጋዋለሁ ብሏል።
የዲሞክራት እና የሪፐብሊካን ሕግ አውጭዎች ቲክቶክ ከቻይና መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ስጋት ላይ ጥሎናል በሚል መተግበሪያውን የሚያግድ ድምጽ ሰጥተዋል። ቲክቶክ በበኩሉ ከቻይና መንግሥት ጋር ምንም አይነት መረጃ እንዳማያጋራ በተደጋጋሚ አስታውቋል።












