የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረጋቸው ያሉት ተደራራቢ ግብሮች የደቀኑት ስጋት

ግብር

በሳምንቱ መጀመሪያ ማክሰኞ ጥር 6/2017 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአዲሱ የንብረት ታክስ ላይ አከራካሪ ውይይት አድርገው በአራት ተቃውሞ እና 10 ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቀውታል።

አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ከንብረት ታክስ ባለፈ አጠቃላይ በመንግሥት እየተጣሉ ያሉ ታክሶችን የሚተቹ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

የፌደራል መንግሥት በ2017 "የበለጠ የታክስ ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻል በማሰብ የተለጠጠ ዕቅድ" መያዙን የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ይፋ አድርጎ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ወራት በፊት ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ማብራሪያ መንግሥታቸው በ2017 በጀት ዓመት 1.5 ትሪሊዮን ብር ከታክስ ለመሰብሰብ ማቅዱን አስታውቀዋል።

መንግሥት ለ2017 ሥራ ላይ ለማዋል ካቀዳቸው የታክስ ሕጎች መካከል የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ማሻሻያ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ አረንጓዴ (የተሽከርካሪ ዝውውር ዓመታዊ) ታክስ እና የንብረት ታክስ ይጠቀሳሉ።

የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ከኢኮኖሚው ሊሰበሰብ የሚገባው ታክስ እንደማይሰበሰብ እና የታክስ መሠረትን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ ግን የመንግሥት ወጪ መብዛት "ከፍተኛ የገንዘብ ፍላጎት አስከትሏል" ይላሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግሥት የገቢ ምንጭ አድርጎ የተጠቀመው "የውጭ አገር ብድር እና የገንዘብ ህትመትን (ከብሔራዊ ባንክ መበደርን)" እንደነበር ያነሳሉ። ይህ በበከሉ የመንግሥት መዋቅርን እንዲሰፋ ማድረጉን ያክላሉ።

ባለሙያው "የመንግሥት ወጪ እየበዛ መምጣት እንዲሁም ከዚህ በፊት ዋነኛ የገቢ ምንጭ የነበሩትን ብድር እና የገንዘብ ህትመት መጠቀምን መቀነሱን ተከትሎ ሌላ የገቢ ምንጭ አስፈልጎታል" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

በመንግሥት በኩል የተስተዋለውን ይህን የገቢ እና ወጪ መዛባት ለማስተካከት "አንደኛ ወጪ መቀነስ ወይም ገቢ መጨመር አለበት" የሚሉት ዶ/ር አብዱልመናን፤ "ወጪ ለመቀነስ ግን ፍላጎት አላሳየም" ሲሉ ይገልጻሉ።

"ስለዚህ ገቢውን መጨመር አለበት፤ ገቢ ለመጨመር ደግሞ አለ የሚለውን ሕብረተሰቡን ታክስ የማድረጊያ ዘዴ መፈለግ አለበት" ሲሉ ዶ/ር አብዱልማንን ይናገራሉ።

አክለውም "በዚያ የተነሳ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት መንግሥት ታክስን እንደገቢ ምንጭ እንዲጠቀም ከፍተኛ ጫና አሳድረውበታል" ይላሉ።

መንግሥት ከዚህ በፊት ወጪውን ለመሸፈን ይጠቀምባቸው የነበሩት የገቢ ምንጮች እየተዘጉ መምጣታቸውን የጠቆሙት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው፤ "ታክስን እንደ ዋና የመንግሥትን ወጪ መሸፈኛ ዘዴ መጠቀም ካለበት ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ታክስ ማድረግ መቻል ይኖርበታል" በማለት ያስረዳሉ።

መንግሥት በ2017 ሥራ ላይ ይውላሉ ካላቸው የታክስ ዓይነቶች መካከል አንዱ የሆነው የንብረት ታክስ "ተደራራቢ ጫና ይፈጥራል" የሚል ተቃውሞ ገጥሞታል።

ግራፍ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ "አሁን አጠቃላይ ካለው የታክስ ጫና አንጻር ማኅበረሰቡ ላይ እና መንግሥት አሁን ከደረሰበት ግብር እና ታክስ የመሰብሰብ አቅም አንጻር አዲስ ታክስ ማስተዋወቅ አያስፈልግም" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

"አሁን ባለው የታክስ መሠረት መንግሥት ወጪዎችን ወደሚሸፍንበት ደረጃ እየደረሰ ነው" ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ "ይሄ ገንዘብ እየተሰበሰበ ያለው በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዋጋ እየከፈሉ ነው" ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

የፓርላማ አባሉ አክለውም "በዝቅተኛ ነጋዴዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች ትክሻ ላይ ሸክም በማብዛት ነው ይሄን ያህል የተደረስነው፤ እኔ የዚህ [የንብረት] ታክስ ፍትሃዊነቱ አይታየኝም" የሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሌላኛው የፓርላማ አባል አቶ ባርጠማ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ "ታክስ መሰብሰብ አለበት፤ ነገር ግን እንዴት መሰብሰብ አለበት? ዜጎች በተደራራቢ የታክስ ጫና ውስጥ ወድቀው ነው ወይ ታክስ መሰብሰብ ያለበት?" ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ተወካዩ አቶ ባርጠማ "በጥቅሉ ለታክስ ከፋዩ ተደራራቢ ጫና የሚያመጣ ነው፤ ይሄ አዋጅ መጽደቅ የለበትም" ሲሉ አዋጁን ተቃውመውታል።

ሌላኛው የአብን ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አበባው ደሳለውም በተመሳሳይ፤ "ደሃውን [ማኅበረሰብ] ለተደራራቢ ጫናዎች ይዳርጋል" የሚል ስጋታቸውን አስተጋብተዋል።

የምክር ቤት አባላት ይህን ቢሉም ግን በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ "ኢትዮጵያ ከጥቅል አገራዊ ምርት አኳያ [የምትሰበስበው ታክስ] ከሰሃራ በታች ትንሹ የሚባል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ታክስ የማንሰበስብባቸው ዘርፎች ብዙ ናቸው" ያሉት የመንግሥት ተጠሪው፤ "ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት ታክስ በአግባቡ እየተሰበሰበ አይደለም። ስለዚህ ታክስ በአግባቡ ለመሰብሰብ የታክስ መሠረቱ መስፋት አለበት" የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም "ከሰሃራ በታች አማካይ የታክስ እና አገራዊ ምርት ጥምርታ 16 በመቶ ነው፤ የእኛ ገና 7 በመቶ ነው" ብለዋል።

ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚያደርጉት የኢትዮጵያን የታክስ እና የአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጥምርታ ከሌሎች አገራት ጋር ማነጻጸር "አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን ይህን ሃሳባቸውን "የኢኮኖሚ መዋቅር ይወስነዋል። የኢትዮጵያ አብዛኛው ምርት አሁን አገልግሎት እየሰፋ መጣ እንጂ፣ ሰፊውን የሚይዘው ግብርና ነው። ግብርና ደግሞ ገበሬው አምርቶ ለፍጆታ የሚያውለው ነው። ግብርና ላይ ከተሰማራው ገበሬ ታክስ ማግኘት አይቻልም። ማነጻጸሪያው በደፈና የቀረበ ነው" ሲሉ ዝርዝር ሁኔታዎችን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን ያስረዳሉ።

የታክስ እና የአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጥምርታው (ratio) ያነሰው "በኢኮኖሚ መዋቅሩ ምክንያት ነው" የሚሉት ዶ/ር አብዱልመናን፤ ዘመናዊ የሆነ የሚያመርት ኢኮኖሚ ባለመሆኑ ኢመደበኛ ኢኮኖሚው በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ለታክስ አመቺ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

ባለሙያው አክለውም የታክስ መሠረቱ ያነሰው "ዜጎች ታክስ ሰለማይከፍሉ ሳይሆን፣ የመንግሥት የራሱ የታክስ ባለሥልጣን እና እዚያ አካባቢ ያሉ ሠራተኞች ብልሹ አሰራር ጭምርም ነው" ሲሉ ይገልጻሉ።

"መንግሥት ወጪውን ለመቀነስ ምንም ፈቃደኝነት አልታየበትም፤ ስለዚህ ወጪውን ለመሸፈን አለ የሚለውን ቀዳዳ ፈልጎ ታክስ መጣሉ አይቀርም" የሚሉት ዶ/ር አብዱልመናን "ከአምስት እና አስር ዓመት በኋላ በጣም ከበድ ያለ ጊዜ እንደሚኖር ነው የሚሰማኝ" ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።