91 ለ 1 በማሸነፍ የታገደው የአፍሪካ እግር ኳስ ክለብ ወደ ውድድር እንዲገባ ተፈቀደለት

የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሴራሊዮን የሚገኘው የሁለተኛ ደረጃ የእግር ኳስ ክለብ፣ ገልፍ ኮኖ 91 ለ 1 በሆነ ውጤት በተጠናቀቀው የእግር ኳስ ጨዋታ የማጭበርበር ወንጀል ምርመራ እየተደረገበት ቢሆንም ወደ አገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ በሚደረገው ውድድር እንዲሳተፍ ተፈቀደለት።

ገልፍ ኮኖ የተሰኘው ክለብ ኮኪማ ሌባኖን በማሸነፍ ወደ ሱፐር 10 የፕሪሚየር ሊግ ምዕራፍ ማለፉን ሲያረጋግጥ የቅርብ ተፎካካሪው ካሁንላ ሬንጀርስ እሁድ በተደረገው የመልስ ጨዋታ በሉምቤቡ ዩናይትድ 1 ለ 0 ተሸንፏል።

ባለፈው ወር ካሁንላ ሌንጀርስ ሉምቤቤ ዩናይትድን 95 ለ0 በማሸነፍ ገልፍ ኮኖ ደግሞ ኮኪማ ሌባኖንን 91 ለ 1 በማሸነፍ አለም አቀፍ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

በነዚህ ሁለት ጨዋታዎች 187 ጎሎች በመቆጠራቸው የሴራሊዮን እግር ኳስ ማህበር በጨዋታ ማጭበርበር ክስ ሰርዟቸዋል እንዲሁም ምርመራም ተከፍቷባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከፍተኛ ወደሆነው የአገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ ተጋጣሚዎቻቸውን ማመን በማይቻል ውጤት ቢያሸንፉም የሁለቱም ጨዋታ ውጤቶች ተሰርዘዋል።

በነዚህ ጨዋታዎች የተሳተፉት አራት ቡድኖች በጨዋታዎቹ አዘጋጆች አካላት ታግደው ነበር።

ይሁንና እገዳው የጨዋታው አዘጋጅ የሆነውና የሴራሊዮን እግር ኳስ ማህበር አካል የሆነው የምስራቃዊ ክልል የእግር ኳስ ማህበር ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተነሳ ሲሆን ይህም የዲሲፒሊን ኮሚቴው ያደረገው ጥናት ተከትሎ ነው። ጥናቱ እስካሁን ለህዝብ ይፋ አልሆነም።

“ከምስራቃዊ ክልል የእግር ኳስ ማህበር ባገኘነው ሪፖርት መሰረት የፕሪሚየር ሊጉን የጊዜ ሰሌዳ እንዳያልፍ ግጥሚያዎቹ እንዲደገሙ ፈቅደናል” ሲሉ የሴራሊዮን እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ቶማስ ዳዲ ብሪማ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።

“ነገር ግን ይህ ማለት ምርመራውን ዘግተነዋል ማለት አይደለም። ፊፋ እና ካፍ (የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን) እንዲመለከቱት እና በዚያም መሰረት እንዲመክሩበት ልከናል” ብለዋል።

“ ገልፍ በሱፐር 10 ውስጥ እንዲሳተፍ መፈቀዱን አረጋግጣለሁ” ብለዋል

ሆኖም ማህበሩ የቀደመ ውጤቱን በተግባር የማይቻል እንደሆነም በዚህ ወቅት አስምሯል።

“ማንም ሰው ቢሆን ይህንን ውጤት ከቁም ነገር አይወስደውም። በማንኛውም መስፈርት በ90 ደቂቃ ውስጥ 90 ግቦች ሊቆጠሩ አይችሉም ብሏል።

ማህበሩ ከአራቱም ክለቦች የተውጣጡ ተጫዎቾችን እንዲሁም ኃላፊዎችን እንደሚመረምሩ ተናግረዋል።

ሆኖም ገልፍ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በምዕራብ አፍሪካ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ለመግባት ቅዳሜ በሱፐር 10 የመጀመሪያ ግጥሚያው ላምቦይን ይገጥማል።