95 ለ 0 እና 91 ለ 1 የተጠናቀቁ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሴራ ሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን 95 ለ 0 እና 91 ለ 1 በተጠናቀቁ ሁለት የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።
የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በሁለት ጨዋታዎች ሊታመን የማይችል 187 ጎሎች መቆጠራቸውን ‘አሳፋሪ’ ብሎታል።
በሴራ ሊዮን በሁለተኛ ደረጃ የእግር ኳስ ሊግ በተደረጉት ግጥሚያዎች ካሁንላ ሬንጀርስ እና ገልፍ ኮኖ ክለቦች ተጋጣሚዎቻቸውን በከፍተኛ የጎል ብልጫ አሸንፈዋል።
ካሁንላ ክለብ ሉምቤቡ ዩናይትድ የተሰኘውን ቡድን 95 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን፤ ገልፍ ኮኖ ደግሞ ኮኪየም ሌበናን 91 ለ 1 አሸንፏል።
በእነዚህ ጨዋታዎች የተመዘገቡት የጎል ብዛቶች በሴራ ሊዮን ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ሲሆን፣ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ውጤቱን ሰርዞታል።
ሁለቱ ቡድኖች ከፍተኛ ወደሆነው የአገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ ተጋጣሚዎቻቸውን ማመን በማይቻል ውጤት ቢያሸንፉም የሁለቱም ጨዋታ ውጤቶች ተሰርዘዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ አሸናፊዎቹ ተጋጣሚዎቻቸውን 2 ለ 0 እና 7 ለ 1 ብቻ እየመሩ ነበር። ከእረፍት መልስ ግን በሁለቱም ጨዋታዎች ከፍተኛ ጎሎች መቆጠራቸው ሆነ ተብሎ ጎሎች እንዲቆጠሩ ሳይደረግ አይቀርም የሚል ጥርጣሬን ፈጥሯል።
“ይህን መሰል አሳፋሪ ተግባር ሲፈጸም ዝም ብለን አንመለከትም፤ ተገቢው ቅጣት ይተላለፋል” ሲሉ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ቶማስ ብሪማ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል።
“አስቸኳይ የሆነ ምርመራ በመክፈት ለዚህ ተጠያቂ የሆኑትን እንለያለን። . . .ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙት በሴራ ሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ይቀጣሉ፤ ለአገሪቱ ፀረ-ሙስና ኮሚሸንም ተላልፈው ይሰጣሉ” ብለዋል የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት።
ተጋጣሚያቸውን በሰፊ የጎል ልዩነት ያሸነፉት የሁንላ ሬንጀርስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ “ስፖርታዊ ጨዋነትን ያልጠበቀ” ያሉትን ባህሪ አጥብቀው እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።
በዚሁ ክለብ በከፍተኛ ውጤት የተሸነፈው ሉምቤቡ ዩናይትድ ክለብ አሰልጣኝ በበኩላቸው ሆነ ተብሎ የጨዋታ ውጤት ለማስቀየር የተደረገ ጥረት ስለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።
አሰልጣኝ ሞሐመድ ጃን ጃሎህ የሚያሰለጥኑት ቡድን 95 ለ 0 ከመሸነፉም በላይ ሦስት ተጫዋቾቻቸው ከሜዳ ተወግደዋል።
“የጨዋታ ውጤት ለማስቀየር ሆነ ተብሎ የተደረገ ነገር ስለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም። ስለ ሌሎች ግን መናገር አልችልም” ሲሉ እራሳቸውን ተከላክለዋል።
“በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ጎሎች ተቆጥረውብናል። በጣም ተበሳጭቼ ነበር. . . ምን ያክል ጎሎች እንደተቆጠሩብን እንኳ ማወቅ አልቻልኩም ነበር” ብለዋል።
የሴራ ሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአራቱንም ክለቦች ተጫዋቾች እና አስተዳዳሪዎች፣ ጨዋታውን የመሩ ዳኞችን እና የአካባቢውን እግር ኳስ ማኅበር አባላት ላይ ምርመራ አደርጋለሁ ብሏል።
















