"በኳስ ወቅታዊ አቋም እንጂ ታሪክ ብዙም ቦታ የለውም" ጋቶች ፓኖም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሐሙስ ሰኔ 02/2014 ዓ.ም. ዋሊያዎቹ በግሩም ብቃት ፈርዖኖቹን አንበረከኩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም እግር ኳስ ስሟ ከገነነው ግብፅ ለመግጠም ሲሰናዳ ብዙ ተባለ።
በርካቶች ሽንፈት ጠበቁ። "አቻ ብንወጣ በምን ዕድላችን" ሲሉ አንሾካሾኩ።
ዋሊያዎቹ ግን የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በባዳ ሜዳ ግብፅን ገጠሙ።
ብሩንዲያዊው የዕለቱ የመሃል ዳኛ ፊሽካቸውን ነፉ። ጨዋታው ተጀመረ።
ዋሊያዎቹ የግብፅን በር ያንኳኩ ጀመር።
ፈርዖኖቹ ኳስ መግፋት ከበዳቸው። አቡበከር ሲሸልል፣ ሽመልስ ሲያታልል፣ ጋቶች ሜዳውን ሲያካልል ቆመው ይመለከቱ ጀመር።
ጨዋታውን በስጋት የጀመረው ደጋፊ የልቡ ምት መለስ ይልለት ጀመር።
21ኛው ደቂቃ ደረሰ። ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግብፁ ግብ ጠባቂ ሞሐመድ አቡጋባል ገሰገሰ።
በዚህች ደቂቃ በኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ዘንድ ድቅድቅ ዝምታ ሰፈነ ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ኳሷ ተንከባላ መረቡን ስትነካ ምድር ተንቀጠቀጠ። ኢትዮጵያ 1 - ግብፅ 0።
ዋሊያዎቹ በአንድ ጎል ተማምነን ለዕረፍት ከሜዳ አንወጣም ያሉ ይመስላሉ።
የግብፅን የሜዳ አጋማሽ ፈነጩበት።
ተረኛው አምበሉ ሽመልስ በቀለ ነው። ለግብፁ ክለብ ኤል ጉና የሚጫወተው ሽመልስ የፈርዖኖቹን ነገር ለኔ ተዉት ያለ ይመስላል።
ከአማኑዔል ገብረሚካዔል የተሻገረለትን ኳስ በአቡጋባል አናት አሻግሮ የዋሊያዎቹን የጎል ድርሻ እጥፍ አደረገው።
የመሃል ሜዳው ሞተር
ፈርዖኖቹ ከወራት በፊት በተረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ ደርሰው በሴኔጋል ተረተው የአህጉሪቱ ሁለተኛ ኃያል ቡድን ለመሆን ችለዋል።
በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ሚዛን ግብፅ 32ኛ ናት። ኢትዮጵያ ደግሞ 140ኛ።
የእግር ኳስ ውጤት ተንታኞች ግብፅ ትረታለች ብለው ቢገምቱ አይገርምም።
ከውጤቱ በኋላም ኢትዮጵያ ረታች ሳይሆን፣ ግብፅ ተረታች ብለው ቢፅፉም በውጤቱ ደንግጠው መሆኑን እሙን ነው።
ግን ግን ዋሊያዎቹ ለጨዋታው የሰጡት ግምት ምን ነበር?
"ኧረ እኛ ምንም ዓይነት ፍራቻ አልነበረንም" ይላል ጋቶች።
"ማሸነፍ እንደምንችል ራሳችንን አሳምነን ነው የገባነው። በእግር ኳስ ወቅታዊ አቋም እንጂ ታሪክ ብዙ ቦታ የለውምና ዓላማችን የነበረው ማሸነፍ ነበር።"
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሚታወቁበት የ4-3-3 ፍልስፍና ፈቀቅ ብለው በአዲስ አሰላለፍ ነበር ግብፅን የገጠሟት።
ውበቱ በግብፁ ጨዋታ 4-2-3-1 በተሰኘው አጨዋወት ነው የተከሰቱት።
አቡበከር ናስር የፊቱን መስመሩን እንዲሾፍር፤ ጋቶችና አማኑዔል ዮሐንስ ተከላካዩንና አጥቂውን ክፍል እንዲያሳልጡ በማሰብ ያደረጉት ነበር።
የአሠልጣኙ ውበቱ ያደረጉት ለውጥ ግን ፍሬያማ ነበር።
"ከማላዊ ሽንፈት መልስ ነው ግብፅን የገጠምነው። ጨዋታው ቀላል እንደማይሆን እናውቃለን። ይኸው አሸንፈን እኛም ደስ ብሎን የኢትዮጵያም ሕዝብ ተደስቷል" ይላል ጋቶች ፈገግታ በሚነበብበት ድምፅ።
በአስገራሚ ብቃቱ መሃል ሜዳውን በብቸኝነት ሲሾፍር የነበረው ጋቶች ፓኖም፣ በቋሚ አሰላለፍ ኢትዮጵያን ከወከለ ሰንበትበት ብሏል።
በአፍሪካ ዋንጫ ጋቶችን ለማየት የቋመጡ ዓይኖች አልተሳካላቸውም።
ጋቶችን ግን ለታሪካዊው የግብፅ ፍልሚያ ደረሰ።
"እርግጥ ነው በአፍሪካ ዋንጫ አንድም ጨዋታ አልተጫወትኩም። ይህ የአሠልጣኙ ውሳኔ ነው። ነገር ግን እኔ ወደ ሜዳ ግባ ስባል ለመግባት ሁሌም ዝግጁ ነኝ።"
ጋቶች ይህን ይላል. . . "ወደ ሜዳ ግባ ስትባል ያለህን አቅም ነው ማሳየት ያለብህ።"
እነሆ በቃል ያለውን በግብፅ ጨዋታ ለብዙዎች አሳይቷል።
ለግብፅ ጨዋታ ባዳ አይደለንም
ከግብፅ 27 ክልሎች አንዱ የሆነው ሬድ ሲ ገቨርኔት የኤል ጉናን መቀመጫ ነው።
ኤል ጉናን ለኢትዮጵያዊያን እግር ኳሰኞች አዲስ አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችም ለግብፅ ሊግ ባዳ አይደሉም።
ጋቶች ፓኖም አንድ የእግር ኳስ ዘመን በኤል ጉናን አሳልፏል። ለሃራስ ኤል ሆዱድም ተሰልፎ ያውቃል።
ሽመልስ በቀለ ደግሞ የወቅቱ የኤል-ጉና የወቅቱ የቡድኑ አማካይ ነው።
ሌሎችም ስማቸው የከበደ ኢትዮጵያውያን ኳስ ተጫዋቾች የግብፅን ሊግ ያውቁታል።
ዋሊያዎቹ ግብፅን ለመርታታቸው ይሄ አንዱ ምክንያት ይሆን?
"አብዛኛዎቹ የግብፅ ተጫዋቾች ከአል-አህሊና ዛማሌክ የተመረጡ ናቸው። እዚያ ሳለሁ ተቃራኒ ሆኜ የተፋለምኳቸው ናቸው" ይላል ጋቶች።
"ይሄ ረድቶኛል ብዬ አስባለሁ።"
የግብፅ ድል ለቀጣይ ጨዋታዎች ጠንካራ መንፈስ እንደሚፈጥር ጋቶች ያምናል።
"በስኬትም በደረጃም ከእኛ ላቅ ያሉ ናቸው። ግብፅን መርታታችን ጠንከር ካልን ማንንም ማሸነፍ እንደምንችል ያሳየን ነው።"
ጨዋታው አገር ቤት ቢሆን. . . ?
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ፤ ኢትዮጵያ አህጉራዊ ጨዋታ ለማድረግ የሚችል ሜዳ የላትም ብሏል።
ይሄ ዜና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ደጋፊውን አንገት ያስደፋ ነበር።
ፌዴሬሽኑ የባሕር ዳር ስታድዬምን አድሻለሁ ቢልም ካፍ ተወካይ ልኮ ካስፈተሸ በኋላ መመዛኛዬን አላሟላችሁም የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ለዚህ ነው ዋሊያዎቹ በሜዳቸው ማድረግ የሚገባቸውን ጨዋታ በማላዊ ስታድዬም ሊያደርጉ የተገደዱት።
ቢሆንም በማላዊው ሊሎንግዌ ስታድዬም ለዋሊያዎቹ የነበረው ድጋፍ ደመቅ ያለ ነበር።
"እርግጥ ነው በሜዳችን ቢሆን የተሻለ የራስ መተማመን ይኖረን ነበር" ባይ ነው ጋቶች።
ነገር ግን ይላል የመሃል ሜዳው ሞተር "ነገር ግን በማላዊ የነበረው ድጋፍ ሜዳችን ላይ እየተጫወትን ያክል እንዲሰማን አድርጎናል።"
ጋቶች ጨዋታው ሲገባደድ ከስታድዬሙ ግዙፍ ድምፅ ማጉያ በሚወጣው ሙዚቃ ከደጋፊዎች ጋር ሲቦርቁ እንደነበር ያወሳል።
"እንግዲህ የእኛ ሜዳ ከደረሰ ቀጣዩን ጨዋታ [ኢትዮጵያ ከጊኒ] በደጋፊያችን ፊት እንደምናደርግ ተስፋ አደርጋለሁ" ይላል።
"ሳላህ ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም"
![ሞሐመድ ሳላህ [ግራ] አቡበከር ናስር [ቀኝ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/56c4/live/9b0b4580-ebc3-11ec-8935-4f1eb8b88d37.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈርዖኖቹ አለን የሚሉት ኮከብ ተጫዋቻቸውን በኢትዮጵያው ጨዋታ ማሰለፍ አልቻሉም።
የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በጉዳት ምክንያት ይህ ጨዋታ አምልጦታል።
ቁጥሩ አንዱ ግብ ጠባቂ ኤልሻናዊና ትሬዝጌም እንዲሁ አገራቸውን መወከል ሳይችሉ ቀርተዋል።
እውን የሞሐመድ ሳላህ አለመኖር ለዋሊያዎቹ መልካም አጋጣሚ ነበር?
"እርግጥ ነው ሞሐመድ ሳላህ ትልቅ ተጫዋች ነው" የጋቶች አስተያየት ነው።
"ነገር ግን ሳላህ ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም። ምክንያቱም እኛ በዕለቱ የተሻልን ነበርን። የሚገባንን ውጤት ነው ያገኘነው።"
አሠልጣኝ ውበቱ አባተም አገር ቤት ከገቡ በኋላ በሰጡት መግለጫ ያሉት ይሄንኑ ነው።
"እኛ በልጠን እንጂ ግብፅ ደክማ አይደለም" ብለዋል።
በግብፅ ሽንፈት የደነገጡ በርካታ ዓለም አቀፍ የኳስ አውታሮችም የዋሊያዎቹን ውጤት ከማድነቅ አልቦዘኑም።
የግብፅ መገናኛ ብዙኃን አዲሱን የፈርዖኖቹን አሠልጣኝ ኢሃብ ጋላልን የሚወቅስ ፅሑፍ አስነብበዋል።
ቀጣይ ጨዋታዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ማጣሪያ በሚቀጥለው ወር ደቡብ ሱዳንን ይገጥማል።
ቻን አገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሰለፉበት አህጉራዊ ውድድር ነው።
ይህም አሠልጣኝ ውበቱ አዳዲስ ተጫዋቾች እንዲሞክሩበት ዕድል የሚሰጣቸው ነው።
ከዚያ ቀጥሎ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይከተላሉ።
ዋሊያዎቹ በወርሃ መስከረም በደርሶ መልስ ጨዋታ ጊኒን ይገጥማሉ።
መጋቢት ደግሞ ሁለቱ ቀሪ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከማላዊና ከግብፅ ጋር ይደረጋሉ።
አሁን ኢትዮጵያ የምድብ 'መ' ቁንጮ ናት።
ምንም እንኳ ሁሉም የምድቡ ቡድኖች ተመሳሳይ 3 ነጥብ ቢያካብቱም ዋሊያዎቹ በአንድ ንፁህ ጎል ከምድቡ አናት ተቀምጠዋል።












