በካሜሮን ዕድሜያቸውን ያጭበረበሩ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሊቀጡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካሜሮን ዕድሜያቸውን አጭበርብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ አርባ አራት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።
ተጫዋቾቹ ከዕድሜያቸው በተጨማሪ ማንነታቸውንም አጭበርብረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከአማተር ክለቦች የተውጣጡ ሲሆን ጥቂቶቹ ደግሞ የብሄራዊ ሊጎች ተጫዋቾች መሆናቸውን የካሜሮን እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፌካፉት አስታውቋል።
ተጫዋቾቹ በማጭበርበር ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ለስድስት ወር ያህል ከየትኛውም ጨዋታ የመታገድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የፌካፉት ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተጫዋቾቹ እድሜያቸውንና ማንነታቸውን ሲያጭበረብሩ ተባባሪ ናቸው ተብለው የተከሰሱ በርካታ የክለብ ፕሬዚዳንቶች ፌካፉት በሚያደርገው ማጣራት እንዲገኙ ተጠርተዋል።
ፌዴሬሽኑ ምርምሩንና መረጃዎችን የሚሰማው በዝግ ነው ተብሏል።
በካሜሮን የዕድሜ ማጭበርበር ክስ የተለመደ ነው። በአውሮፓውያኑ 2016፣ 14 የካሜሮን ተጫዋቾች በአመት ሁለት ጊዜ በሚደረገው የዩ 17 የአፍሪካ ዋንጫ ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት በፊት ታግደዋል።








