የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው

አል ቡርሃን

የፎቶው ባለመብት, Sudan army

የምስሉ መግለጫ, በአል ቡርሃን ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ቅድመ ሁኔታ አቅረበው በሰላም ድርድር ላይ እንደሚሳተፉ ካሳወቁ በኋላ ነው

የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጸመ።

የጦሩ ቃል አቀባይ ነቢል አብደላህ በጄኔራል አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸመው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የሱዳን ጦር በጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔምቲ) ጋር ከሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ጦርነት ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የግድያ ሙከራው የተፈጸመው ጄኔራል አል-ቡርሃን በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በሠራዊት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመው በነበረበት ወቅት ነው ተብሏል።

ረቡዕ ጠዋት ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. የተካሄደውን የምረቃ ሥነ ሥርዓት የሚያሳይ እና በማኅበራዊ ሚዲያ በተጋራ ቪዲዮ ላይ የደንብ ልብስ የለበሱ ተመራቂዎች ተሰልፈው የሚታዩ ሲሆን፣ ተከትሎም የአየር ጥቃት ፍንዳታ ተሰምቷል።

“የሱዳን ሕዝብ ጠላት እና የሱዳንን ሕዝብ ዒላማ የሚያደርገው ብቸኛው ቡድን አማጺው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ነው” በማለት ቃል አቀባዩ ጄኔራል አብደላህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም ጄኔራል አል ቡርሃን እና “በስፍራው የነበሩ ሁሉም አዛዦች ደህና በመሆናቸው” ፈጣሪን አመስግነው፤ በጥቃቱ ብዙም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሉም ብዋል።

ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ማብቂያ ላይ በተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶች ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

በግድያ ሙከራው አል-ቡርሃን ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመው በድሮን ጥቃት መሆኑን የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው የአገሪቱ ጦር ዋና መቀመጫው ካደረጋት ፖርት ሱዳን 100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ጊቤት በተባለ የጦር ሰፍር ውስጥ ነው።

የግድያ ሙከራ የመፈጸሙ ዜና የተሰማው የሱዳን መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ከተስማማ በኋላ ነው።

የሱዳን መንግሥት የሰላም ንግግር ለማድረግ የተስማማው በአሜሪካ ጥያቄ በስዊትዘርላንድ በሚደረግ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ነው።

ይህ የሰላም ንግግር ለ15 ወራት ለዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋን አጭሮ የነበረ ቢሆንም በአል-ቡርሃን ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ የሰላም ተስፋውን ሊያጨልመው ይችላል የሚልስ ስጋት ፈጥሯል።

በሱዳን እየተካሄደ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው የእስር በርስ ጦርነት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ትልቁን ሰብአዊ ቀውስ የፈጠረ ሲሆን፣ ጦርነቱን ለማስቆም ተፋላሚ ወገኖች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለንግግር ቢቀመጡም የገቡትን ቃል ሳያከብሩ ቆይተዋል።

የሱዳን ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር በተያዘ ዕቅድ ላይ ባለመስማማታቸው ነበር ወደ ጦርነት የገቡት።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ በተቀሰቀሰው የእስር በርስ ጦርነት ምክንያት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ሲፈናቀሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል።