ኤርትራ የሱዳን ዲፕሎማት ከአገሯ እንዲወጡ አዘዘች፤ ሱዳን ማብራሪያ ጠየቀች

የሱዳን መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና ኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የምስሉ መግለጫ, የሱዳን መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና ኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ኤርትራ የሱዳን ዲፕሎማት በሰባ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ከግዛቷ እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ ካርቱም ዲፕሎማቷን በተመለከተ ከአሥመራ ማብራሪያ ጠየቀች።

መንግሥታዊው የሱዳን ዜና አገልግሎት ሱና እንደዘገበው የሱዳን መንግሥት በጎረቤት አገር በኤርትራ የነበሩት ጉዳይ ፈጻሚው (ቻርጅ ዲ አፌር) ስለተባረሩበት ምክንያት “ማብራሪያ” ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ ነው።

የሱዳኑ ዲፕሎማት ከአሥመራ በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን በተመለከተ በኤርትራ በኩል በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም፤ ባለፈው ማክሰኞ የሳዑዲ አረቢያው ጋዜጣ “አል-አሽራቅ” በኤክስ ገጹ ላይ ዘግቦት ነበር።

“የኤርትራ መንግሥት የሱዳን ጉዳይ ፈጻሚ የነበሩት አምባሳደር ኻሊድ አባስ ከአገሩ ለቀው እንዲወጡ የ72 ሰዓታት ጊዜ በመስጠት” ማባረሩን ጋዜጣው አመልክቷል።

ሱዳን ዲፕሎማቷ በሦስት ቀናት ውስጥ ኤርትራን ለቀው እንዲወጡ ከተነገራቸው ከአንድ ቀን በኋላ ነው የኤርትራ መንግሥት ውሳኔውን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣት የጠየቀቸው።

የሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሁሴን አል-አሚን ውሳኔውን በተመለከተ መንግሥታቸው የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በመጥቀስ “ከኤርትራ መንግሥት በኩል ማብራሪያ እየጠበቅን ነው። አምባሳደሩ ወደ አገራቸው ሲመለሱም የሚሉትን እንሰማለን” ብለዋል።

በኤርትራ የሱዳን ጉዳይ ፈጻሚ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ኤርትራን ለቀው እንዲወጡ የተደረጉበት ምክንያትን በተመለከተ ከኤርትራ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

የሱዳን መንግሥት ተቀናቃኝ የሆነው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የመገናኛ ብዙኃን አባል የሆነው ዋድ አል-ቡሃየር እንዳለው፣ ኤርትራ ዲፕሎማቱን ለማባረር የወሰነችው ዲፕሎማቱ “በኤርትራ ያሉ ወጣቶችን ከሱዳን ሠራዊት ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ ሲመለምሉ ተግኝተው ነው” ብሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ “አል ታግህዬር” የተባለው የሱዳን የግል ጋዜጣ ስማቸውን ያልተገለጹ የኤርትራ ምንጮችን ጠቅሶ ለዲፕሎማቱ ከአሥመራ መባረር መክንያቱ “በምዕራብ ኤርትራ የሚገኝን የማሠልጣኛ ካምፕን በተመለከተ መረጃ እንዲሰበሰቡላቸው ሁለት ወጣቶችን በመመልመላቸው ነው” ብሏል።

ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው የሱዳን መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት መልካም ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ በጦርነቱ ወቅት የሱዳን ጦርን እና ደጋፊዎቹን በተለያዩ ጊዜያት ሲያሠለጥን ነበር ተብሎ ሲወቀስ ቆይቷል።

አሁን በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያበላሸው ይችላል የተባለውን አምባሳደሩን የማባረር ውሳኔ መነሻው ምን እንደሆነ በግምት ከሚነገረው ውጪ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።