ሕንድን ያስደነገጠው ሰዎችን የመሰዋት ወንጀል

በደቡባዊ ሕንድ ኬራላ ግዛት ፖሊስ ሁለት ሴቶችን “በመስዋዕትነት” ገድለዋል ያላቸውን ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሏል።
በወራት ልዩነት ተገድለዋል የተባሉት የእነዚህ ሴቶች ቀሪ የሰውነት ክፍል ማክሰኞ ጥቅምት 01/2015 ዓ.ም. ተገኝቷል።
ተከሳሾቹ ባልና ሚስት እና ሌላ አንድ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ሴቶቹን ከመግደላቸው በፊት “ክፉኛ እንዳሰቃዩዋቸው” ፖሊስ ተናግሯል።
ተከሳሾቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያሉ በመሆናቸው ስለ ክሱ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ መረጃዎችን ይዟል።
በሕንድ ተራማጅ ግዛቶች ከሆኑት አንዷ በሆነችው ኬራላ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ በአገሪቱ ሚዲያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተዘገበ ሲሆን በርካቶችንም አስደንግጧል።
ተከሳቾቹ ፈዋሽ እንደሆነ የተነገረለት ባጋቫል ሲንግ እና ባለቤቱ ለይላ እና የአስማተኛ ነኝ የሚለው መሐመድ ሻፊ እንደሆኑ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ረቡዕ ዕለት በኮቺን ከተማ የሚገኝ ፍርድ ቤት ለሦስት ሳምንታት ያህል በፍርድ ቤት ቁጥጥር እንዲቆዩ ብያኔ አስተላልፏል።
የኮቺን ፖሊስ ኮሚሽነር ሲኤች ናጋራጁ ግድያው የተፈጸመው ከአራት ወራት በፊት እንደሆነና “ገንዘብና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች” ለማግኘት በተደረገ የአምልኮ ሥርዓት እንደሆነም ተጠርጥሯል ብለዋል።
ከግድያው ጀርባ ያለው ምክንያት ግምት እንደሆነ እና የእምነት ክህደት ቃላቸውንም በመስማት ምርመራ እየተደረገባቸውም መሆኑንም አክለዋል።
በሕንድ ውስጥ ሀብትን ለማግኘት፣ ሴቶች ልጆች እንዲወልዱ፣ የተለያዩ ህመሞችን ለመፈወስ እና አልፎ ተርፎም ዝናብ እንዲመጣ በሚል ጥንቆላ እና አንዳንድ የአምልኮ ሥርዓቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ።

የተገደሉት ግለሰቦች በኮቺን የሎተሪ ቲኬት በመሸጥ የሚተዳደሩ ሲሆን ገንዘብ እንሰጣችኋለን በሚልም ተከሳሾቹን እንዳተለሏቸው ፖሊስ ተናግሯል።
ግለሰቦቹን ከወሰዷቸው በኋላ አንገታቸውን በመቅላት ከገደሏቸው በኋላ አካላቸውንም ቆራርጠውታል።
የሴቶቹ ቀሪ አፅምም መሆኑ የተጠረጠረም ማክሰኞ እለት በፓታናምቲታ ግዛት በሚገኘው ባጋቫል መኖሪያ አቅራቢያ ተቆፍሮ ወጥቷል።
የተቆራረጠውን የሴቶቹን አፅም ቤተሶቦቾቻቸው መለየት ባለመቻላቸው ናሙናቸው ለዲኤንኤ ምርመራ ተልኳል።
የሃገሪቱ ዋና ሚኒስትር ፒናራይ ቪጃያን ወንጀሉ “የሰውን ህሊና የሚፈትን” እንደሆነ ገልጸው በአጉል እምነት ምክንያት ሰዎችን ማፈን እና መግደል አንደ ኬራላ ባሉ ግዛት “ከሰው ልጅ ሃሳብ በላይ የሆነ ወንጀል” ነው ብለዋል።
የተገደሉት ግለሰቦች እነማን ናቸው?
ፖሊስ የተገደሉት ግለሰቦች ፓድማም እና ሮዚሊ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው ብሏል።
የ57 ዓመቷ ፓድማም ዳርማፑራም ከተባለ ግዛት መጥታ በኮቺን ከተማ ትኖር የነበረ ሲሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ የ49 ዓመቷ ሮዚሊ ከትሪስሱር ግዛት መጥታ ካላዲ በተባለች ስፍራ ነዋሪ ነበረች።
የፓድማም ልጅ እናቱ እንደጠፋች ለፖሊስ መስከረም ወር ላይ ጥቆማውን አቅርቧል።
ፓድማ ከየካቲት ወር ጀምሮ በኮቺን በአንድ ክፍል መኖሪያ ቤት ውስጥ ተከራይታ ትኖር ነበር። “ብቻዋን ነበር የምትኖረው። እናም ሁልጊዜ ማታ ትደውልልኝ ነበር” ስትል እህቷ ፓላኒያማ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ፓላኒያማ ለእህቷ በተደጋጋሚ ብትደውልም ለቀናት ያህል ምላሽ ባለማግኘቷ ሁኔታውን ለማጣራት ወደ እህቷ ቤት አመራች።
ነገር ግን ቤቷ ተቆልፎ እንዳገኘችውና የእህቷም ስልክ እንደጠፋ ታስረዳለች።
ፖሊስም የፓድማን የተንቀሳቃሽ ስልክ ሲከታተልም ከኮቺን 113 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፓታናምቲታ አገኘው።
ከአንደኛው ተከሳሽ ሻፊም በርካታ የስልክ ጥሪም እንደረሳት አረጋግጠዋል።
የሻፊም ስልክ ጥሪ በሚመረመርበትም ወቅት ከሌላኛው ተከሳሽ እና እዚያው አካባቢ ከሚኖረው ሲንግ ጋር ተደዋውሎ እንደነበር ፖሊስ መረዳት ቻለ። ፖሊስ ሲንግን በሚጠይቅበት ወቅት ወንጀሉን አምኗል።
ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ባደረገበት ወቅት ሲንግ፣ ባለቤቱ እና በሻፊ እርዳታ ሰኔ ወር ላይ ሮዚሊ የተባለች ግለሰብን መግደላቸውን ደረሰበት።
“በጣም እንግዳ የሆነ የግድያ ወንጀል ነው። ግድያዎቹ በትክክል መቼ እንደተፈጸሙና ሌሎች ግድያዎችም ተፈፅመው ከሆነ ለማጣራት እየሞከርን ነው” ነው በማለት ኢንስፔክተር ፒ ፕራካሽ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።













