የሮማው ፖፕ ወደ ጋዛ መግባት ስለማይከለከሉ ሄደው ህጻናቱን እንዲያዩ ማዶና ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ሊዮ ወደ ጋዛ መግባት የማይከለከሉ ብቸኛው ሰው ስለሆኑ ወደ ጋዛ ሄደው ፍልስጤማውያኑን ህጻናት እንዲያዩ አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ማዶና ጠየቀች።
ማዶና "ጊዜው ሳይረፍድ" ፖፑ ወደ ጋዛ ሄደው ለህጻናቱ ተስፋ እንዲሆኗቸው በማሀበራዊ ሚዲያ ገጿ ተማጽናለች።
ማዶና ይህንን ያለችው ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጃፓን በጋዛ ያለውን ረሃብ አስመልክቶ ማሳሰቢያ ይህም ሁኔታ እንዲቀለበስ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
በተጨማሪም በጋዛ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያን አብዛኞቹ ህጻናት በረሃብ መሞታቸውን ሪፖርት መደረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል።
"ቅዱስ አባት ሆይ እባክዎ ወደ ጋዛ ሄደው ጊዜው ከመርፈዱ በፊት ለህጻናቱ ብርሃን ይሁኗቸው" ስትል ማዶና በኢንስታግራም ገጿ አጋርታለች።
አክላም "እንደ እናት ስቃያቸውን ማየት አልቻልኩም" ብላለች።
"የዓለም ልጆች በሙሉ የሁሉም ናቸው"
"ከእኛ ውስጥ መግባት የማይከለከሉት እርስዎ ብቻ ነዎት" ስትል በማህበራዊ ሚዲያ ገልጻለች።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ እየከፋ መሆኑን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች "የከፋ ረሃብ" ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
እስራኤል በጋዛ ረሃብ የለም በማለት የምትክድ ሲሆን የተበባሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እርዳታውን ከድንበር አካባቢዎች ወስደው አላሰራጩም ስትል ትከሳቸዋለች።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅት ወደ ጋዛ እየገባ ያለው እርዳታ "ከሚያስፈልገው በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን" ገልጿል።
እስራኤል ከምትቆጣጠራቸው የድንበር ስፍራዎች እርዳታዎቹን ለማምጣት እንቅፋት እየገጠመኝ እንደሆነም አክሏል።
ባለፈው ወር በጋዛ ከተማ በምትገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የነበሩ ሶስት ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ አዲሱ ፖፕ የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቅርበዋል።
"ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብዓዊ ህግ መከበሩን፣ ሲቪሎችን የመጠበቅ ግዴታ እንዲሁም የጅምላ ቅጣትን መከልከል፣ ሁሉንም ያልለየ የሃይል እርምጃ እና ዜጎች በአስገዳጅ ሁኔታ መፈናቀል አለመፈጸሙን ሊያዩ ይገባል" ሲሉ ፖፑ መናገራቸውን ፒኤ የተባለው ሚዲያ ዘግቧል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ላልቶ የነበረ ቢሆንም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት ማቋቋማቸው ይታወሳል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።















