በደቡብ ወሎ ከ13 ቀናት በፊት ዋሻ የተናደባቸው ማዕድን አውጪዎችን ለማዳን የተደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ዞን፣ ደላንታ ወረዳ በኦፓል ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ ሳሉ ዋሻው ተንዶባቸው የተቀበሩ ሰዎች ሁለት ሳምንት ሊሞላቸው ቢቃረብም እስካሁን ያሉበት ሁኔታ አልታወቀም።
ከ13 ቀናት በፊት ለጌጣጌጦች መሥሪያ የሚውለውን ውድ ማዕድን ለማውጣት ቁፋሮ ላይ እያሉ ዋሻ የተናደባቸውን ሰዎች ለማውጣት የሚያስችል መፍትሔ አሁንም ድረስ አለመገኘቱን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር እና የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ተናገሩ።
ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት በቁፋሮ ላይ ሳሉ ዋሻው ተንዶ መውጫ ያጡት ሰዎች ቁጥር አስካሁን በትክክል ባይታወቅም ለስምንት አስከ ሃያ ሊደርሱ እንደሚችሉ የአካባቢው ምንጮች አሳውቀዋል።
ሰዎቹ ከውስጥ እያሉ ዋሻው እንደተደረመሰባቸው ከታወቀበት ዕለት አንስቶ የአካባቢው ነዋሪዎች እና አስተዳዳሪዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ በሰው ኃይል ለቀናት ቁፋሮ ቢያደርጉም፣ ውጤት ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ነፍስ ለማዳን በሚሞክሩት ላይ አደጋ ሊደርስ ይችላል በሚል ቁፋሮው ለቀናት ቆሞ ነበር።
የማዕድን ማውጫው ያለበት ገደላማ ስፍራ የቁፋሮ ማሽን ማስገባት ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎችን ለቁፋሮ ለማሰማራት አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በዋሻው አናት የተንጠለጠለ አለት በቁፋሮው ሂደት ሊደረመስ እና አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው ቁፋሮው የተቋረጠው።
ይህንንም አለት ለማስወገድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. በአካባቢው በመገኘት የዋሻውን የላይኛው ክፍል ለማፍረስ ፈንጂ ቢጠቀምም፤ ሙከራው አለመሳካቱን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በደላንታ ወረዳ 018 አለኋት ቀበሌ ቆቅ ውሃ በተባለው አካባቢ በሚገኘው የኦፓል ማዕድን ማውጫ ዋሻ ውስጥ ምሽት ላይ አደጋው ከደረሰ በኋላ ስምንት አባላቱ ሰዎች በዋሻው ውስጥ እንደነበሩ መረጋገጡን የአካባቢው የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አጋዥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በዋሰው ውስጥ በማዕድን ፍለጋ ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል በመግለጽ ቁጥሩን አስከ 20 ከፍ ያደርጉታል።
የዋሻው መናድ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢው ነዋሪዎች የተቀበሩትን ሰዎች ለማውጣት ቁፋሮ ሲያካሂዱ የነበረ ሲሆን 80 ሜትር ጥልቀት ያለው አፈር ከተቆፈረ በኋላ ጥረቱ ተቋርጧል።
አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት ቁፋሮው እንዲቋረጥ የተደረገው የዋሻው የላይኛው ክፍል ላይ የሚገኘው አፈር ከስር ቁፋሮ የሚያካሂዱት ሰዎች ላይ ተንዶ ተጨማሪ ሰዎች በተመሳሳይ “መውጫ ያጣሉ” የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን እንደሚናገሩት፤ ሰዎቹን ከዋሻው የማውጣት ጥረቱን አስቸጋሪ ያደረገው ዋነኛው ጉዳይ ዋሻው የሚገኝበት አካባቢ መልካ ምድር አስቸጋሪነት ነው።

የፎቶው ባለመብት, SOUTH WOLLO COMMUNICATION
“[ዋሻው የሚገኘው] ገደል ውስጥ ስለሆነ ሌሎች ማሽነሪዎችን መጠቀም በፍጹም የሚቻልበት ቦታ አይደለም” የሚሉት አቶ አሊ፤ በዚህም ምክንያት የዞኑ አስተዳደር ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመነጋገር የሠራዊቱ መሃንዲሶዎች ቦታውን እንዲመለከቱት መደረጉን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት መሃንዲሶች በአካባቢው ላይ የተሰማሩት የማዕድን አውጪዎች ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የወረዳው አስተዳደር ፈቃድ ከተገኘ በኋላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዋሻው የሚገኝበትን ቦታ የተመለከቱት የመከላከያ መሀንዲሶችም “ፈንጂ እና ድማሚት” በመጠቀም የዋሻው የላይኛው ክፍል ለማፍረስ ሀሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ዋና አስተዳዳሪው፤ “የመከላከያ መሃንዲሶች [ያቀረቡት ሀሳብ] የተንጠለጠውን ገደል ለመናድ ‘በፈንጂ እና በድማሚት እንሞክር’ የሚል ነበር። ሰኞ ዕለት ተሞከረ እሱም የሚቻል አልሆነም” ሲሉ ሙከራው አለመሳካቱን ገልጸዋል።
አቶ አሊ እንደሚያስረዱት ጥቅም ላይ የዋለው ፈንጂ ቢፈነዳም የአካባቢው ነዋሪዎች ቁፋሮ ሲያከናውኑ እንዳይናድባቸው ስጋት የፈጠረውን የዋሻውን ክፍል ማስወገድ ግን አልተቻለም።
ይህ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ እንዲወገድ የሚፈለገውን የዋሻ ክፍል “በታንክ የመምታት” ሃሳብ ከመሃንዲሶቹ በኩል መቅረቡን የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
“ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፤ ያቺ ቦታ ብትመታ ሰዎቹን ቆፍሮ የማውጣት ዕድል ይኖር ነበር” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህ ስፍራ ከተናደ በኋላ ነዋሪዎች ቁፋሯቸውን ቀጥለው ማዕድን አውጪዎቹን ማዳን ይችላሉ የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና “በታንክ መምታት” የሚለው ሃሳብን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ጠቅሰዋል።
ተመሳሳይ ሃሳብ የሚያነሱት ዋና አስተዳዳሪው አቶ አሊ በበኩላቸው፤ “መፍትሄ መስጠት የሚቻለው ባለሙያዎች አይተውት፤ የተሰነጠቀውን ነገር ሊያወርድ የሚችል ‘ምን አይነት ቴክኖሎጂ እንጠቀም?’ የሚለው እንደገና ተፈትሾ ነው። [በታንክ ቢመታ] የሚል ሀሳብ አለ ግን ‘ሊያወርደው ይችላል ወይ?” የሚለው መረጋገጥ አለበት” ሲሉ የዚህ መፍትሄ አዋጭነት መረጋገጥ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በዋሻው ውስጥ የተቀበሩትን የማዕድን ቆፋሪዎች ለማውጣት አሁንም በአካባቢው እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ አሊ፤ “በመንግሥት በኩል ሊወሰድ የሚችል ማንኛውንም አማራጭ ወስዶ የልጆቹን ሕይወት ለማዳን ወደ ኋላ የሚባል ነገር የለም” ብለዋል።
በዋሻው ውስጥ መውጫ ካጡ 13ኛ ቀን ያስቆጠሩት የማዕድን አውጪዎች ያለ ምግብ “እስካሁን መቆየት ይችላሉ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ፤ አሁንም ተስፋ እንዳላቸው ነው ተናግረዋል።
“[ያለ ምግብ] ይኖራሉ። እስከ 15 ቀን ድረስ የመቆየት ዕድል አላቸው። [ዋሻው] ውስጥ ውሃ ስላለ፤ አፈር በሉ ምንም አሉ ዞሮ ዞሮ የመቆየት ዕድላቸው አለ” ሲሉ ግለሰቦቹ በሕይወት ይገኛሉ የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።
ውድ ጌጣጌጦችን ለማምረት የሚውለው ኦፓል በደቡብ ወሎ ዞን በደላንታ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህንኑ ማዕድን በማውጣት ላይ የተሰማሩ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች አሉ።
በዚህ ሂደትም እንዲህ ያለው አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት የሚናገሩ ሲሆን፣ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በማዕድን ቁፋሮ ወቅት በሚያጋጥም የናዳ አደጋ ቢያንስ 50 ሰዎች መሞታቸውን የማዕድን አውጪዎቹ ማኅበር ሊቀመንበር ለቢቢሲ ገልጿል።















