በደቡብ ወሎ በኦፓል ማዕድን ማውጫ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት የሚካሄደው ቁፋሮ መቋረጡ ተገለጸ

ከወሎ የተገኘ ኦፓል የተባለው ማዕድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ ሳሉ ዋሻ የተደረመሰባቸውን በርካታ ሰዎች ለማውጣት እየተደረገ የነበረው ጥረት በቁፋሮ ወቅት አፈሩ በመደርመሱ መቋረጡ ተገለጸ።

ስድስተኛ ቀናቸውን የያዙትን የኦፓል ማዕድን አውጪዎችን ከተቀበሩበት ለማውጣት የተጀመረው ቁፋሮ መቋረጡን የወገል ጤና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስምንት አባላቱ በናዳው ተይዘው እንደሚገኙ የገለጸው በአካባቢው የሚገኘው የወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር ተስፋዬ አጋዥ ቁፋሮው መቋረጡን አረጋግጠዋል።

አቶ ተስፋዬ የቁፋሮ ሥራው ረቡዕ የካቲት 6/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ እንደተቋረጠና ነገር ግን ሐሙስ ንጋት ላይ መልሶ እንደሚጀመር ቢናገሩም፣ አቶ ተስፋዬ አጋዥ ግን የቁፋሮ ሥራው ትላንት ማክሰኞ እንደተቋረጠ እና መልሶ እንደማይጀመር ተናግረዋል።

በመቶዎች ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ ውስጥ ተቀብረዋል የተባሉትን የኦፓል ማዕድን አውጪዎችን ለማውጣት የተጀመረው ጥረት ከ60 አስከ 70 ሜትር ገደማ ቁፋሮ ከተካሄደ በኋላ ነው የተቋረጠው።

ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት የኦፓል ማዕድን በቁፋሮ ለማውጣት ሲሞክሩ ነበር የተባሉ ማዕድን አውጪዎች ላይ ዋሻው ተንዶ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች የተቀበሩ ሲሆን፣ ስላሉበት ሁኔታ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የደቡብ ወሎ ዞን ኮሚዩኒኬሽን በገደላማ አካባቢ ያለው የማዕድን ማውጫ ዋሻ የተደረመሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ ነው ያለ ሲሆን፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን ትክክለኛው አሃዝ ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

ማዕድን አውጪዎቹን ከተጫናቸው አፈር ለማውጣት በሚሞከርበት ወቅት ከላይ ያለው ገደላማ መሬት እየተንሸራተተ በመምጣቱ ቁፋሮው መቆሙንም አቶ ተስፋዬ አጋዥ ተናግረዋል።

ቁፋሮው ከመቋረጡ በፊት ማክሰኞ ዕለት 55 ሰዎች ገደማ በቁፋሮው ሥራ ተሳትፈው የነበሩ ሲሆን፣ ከላይ ያለው አፈር መንሸራተት ሲጀምር በፍጥነት መውጣታቸውን ተናግረዋል።

“በፍጥነት ባንወጣ አደጋ ነበረው። የሚቆፍሩት ሰዎች ሕይወት ሊታጣ ሆነ” ሲሉም ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ገልጸዋል።

በዋሻው ውስጥ የሚገኙት የማዕድን ወጪዎቹ ቤተሰቦቻቸው በስፍራው የነበሩ ሲሆን፣ “ገደሉ ተንዶ ሌላ አደጋ ስለሚያደርስ አልቻልንም ብለው ተስፋ መቁረጣችንን ነግረናቸው እያለቀሱ ሄደዋል” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቁፋሮው ሥራም 60 ሜትር ደርሶ ትላንት ማክሰኞ ምሽት መቆሙን አቶ ተስፋዬ አጋዥ ገልጸው የተጫናቸው አፈር ሳይነሳ የሚወጡበት መንገድ እንደሌለ አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ በመቶ ሜትሮች ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው የሚገኙ ሲሆን፣ አሁን በተደረሰው ቁፋሮ ትንፋሽ እንዲያገኙ የሚያስችል ስፍራ ላይ መደረስ አልተቻለም ብለዋል።

ዋሻው የተረመሰበት አካባቢ ገደላማ በመሆኑ የነፍስ አድን ሥራ ለማካናወን አዳጋች መሆኑን የአካባቢው ባለሥልጣናት ይናገራሉ

የፎቶው ባለመብት, South Wollo Commu.

የምስሉ መግለጫ, ዋሻው የተደረመሰበት አካባቢ ገደላማ በመሆኑ የነፍስ አድን ሥራ ለማካናወን አዳጋች መሆኑን የአካባቢው ባለሥልጣናት ይናገራሉ

ረቡዕ ዕለት ቁፋሮው እንደቆመ የተናገሩት የወገል ጤና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ዓለምነው በበኩላቸው የላይኛው አፈር ተንዶ ቁፋሮው የሚቀጥልበትን መፍትሄም እያፈላለግን ነው ብለዋል።

ከስር ሲቆፈር ከላይ ያለው መሬት እየተናደ በመሆኑ ሁለተኛ ሌላ ጉዳት እንዳያደርስ ቁፋሮው ለጊዜው እንዲቆም መደረጉን ነው ከንቲባው የገለጹት።

አክለውም ከላይ ተንጠልጥሎ የሚገኘውን አፈር ለመናድ በድማሚት እና በሌሎች አማራጭ መሳሪያዎች መሞከሩ የበለጠ አስጊ ስለሚሆን በሰው ኃይል ከተናደ በኋላ እንደ አዲስ ቁፋሮ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

ዋሻው ውስጥ ተቀብረው የሚገኙትን ሰዎች ለማውጣት ሕዝቡን የማነቃነቅ እና የማስተባበር ሥራ አሁንም እየተከናወነ እንደሆነ በመጥቀስ መከላከያ፣ የፀጥታ ኃይሉን እና ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ሐሙስ ወደ ቁፋሮ እንደሚገባ እና ቁፋሮው አለመቆሙን አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።

አደጋው የደረሰው በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው 018 አለኋት ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ቆቅ ውሃ በተባለ ስፍራ ነው።

ዋሻው ተደርምሶ የተቀበሩት ሰዎች በሌሊት ወደ ስፍራው መሄዳቸው ለአደጋው መከሰት እና ቁጥራቸውም በትክክል ላለመታወቁ ምክንያት መሆኑን የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ደግሞ አካባቢው ገደላማ በመሆኑ እና ከዚህ ቀደም የኦፓል ማዕድን ለማውጣት የተቆፈሩት ዋሻዎች አደገኛ በመሆናቸው ለአካባቢው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም።