በደቡብ ወሎ በኦፓል ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ሦስት ቀን ሆናቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ ሳሉ ዋሻ የተደረመሰባቸውን በርካታ ሰዎች ለማትረፍ የሚደረገው ጥረት ያለ ውጤት ለሦስተኛ ቀን መቀጠሉን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ምክንያት ቁፋሮ በተሽከርካሪ ማድረግ ባለመቻሉ በዚህ መስክ ልምድ እና መሳሪያ ያላቸው ለነፍስ አድን ጥረቱ ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት የኦፓል ማዕድን በቁፋሮ ለማውጣት ሲሞክሩ ነበር የተባሉ ማዕድን አውጭዎች ላይ ዋሻው ተንዶ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች የተቀበሩ ሲሆን፣ ስላሉበት ሁኔታ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የደቡብ ወሎ ዞን ኮሚዩኒኬሽን በገደላማ አካባቢ ያለው የማዕድን ማውጫ ዋሻ የተደረመሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ ነው ያለ ሲሆን፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን ትክክለኛው አሃዝ ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
የዋሻው መደርመስ አደጋ ያጋጠመው ባለፈው ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በኋላ እንደነበረ ለቢቢሲ የተናገሩት የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን፣ የሰዎቹን ሕይወት ለማትረፍ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ሌት እና ቀን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አደጋው የደረሰው በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው 018 አለኋት ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ቆቅ ውሃ በተባለ ስፍራ ላይ ነው።
ዋሻው ተደርምሶ የተቀበሩት ሰዎች በሌሊት ወደ ስፍራው መሄዳቸው ለአደጋው መከሰት እና ቁጥራቸውም በትክክል ላለመታወቁ ምክንያት መሆኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አሊ መኮንን ለቢቢሲ እንደገለጹት አካባቢው ገደላማ በመሆኑ እና ከዚህ ቀደም የኦፓል ማዕድን ለማውጣት የተቆፈሩት ዋሻዎች አደገኛ በመሆናቸው ለአካባቢው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ነበር።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አያሌው፤ አደጋው መከሰቱ ከታወቀ በኋላ የአካባቢው ነዋሪ በዋሻው ስር የተቀበሩትን ሰዎች ሕይወት ለማትረፍ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከስፍራው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪነት የተነሳ የሚፈለገውን ያልህ መንቀሳቀስ እንዳልተቻለ አመልክተዋል።
ባለፉት ቀናት ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች በነፍስ አድን ሥራው ላይ እገዛ ለማድረግ ወደ ስፍራው ቢያቀኑም ወደ ዋሸው ለማምራት የሚያስችለው መንገድ ጠባብ እና በአንድ ጊዜ ከአስር ሰዎች በላይ ማስገባት ባለመቻሉ ጥረታቸው አዝጋሚ ሆኗል።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በተደረጉ ቁፋሮዎች ምክንያት የአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ጠንካራ ባለመሆኑ የነፍስ አድን ጥረት በሚያደርጉት ሰዎች ላይ ጭምር አፈሩ ስለሚናድ ሌላ ስጋት መፍጠሩን አቶ አያሌው አመልክተዋል።
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን የቁፋሮ ሥራውን በማሽን ለማገዝ ፍላጎት ቢኖርም የአካባቢው ገደላማነት “እንኳን ቆፋሪ ተሽከርካሪን ቀርቶ ሰዎችን በበቂ ሁኔታ ለማስገባት አመቺ አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአደጋው መከሰት በኋላ ወደ ዋሻው በሌሊት አምርተዋል የተባሉ ሰዎች ቁጥር ግምት ከ10 በታች ሲሆን፣ ከነዋሪዎች በኩል የተለያዩ አሃዞች እንደሚወጡ የወረዳው አስተዳዳሪ ገልጸዋል።
በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች በተጨማሪ ከአጎራባች ቦታዎች የኦፓል ማዕድን ለማውጣት የመጡ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችል የታመነ ሲሆን፣ ቁጥሩን ግን ይህ ነው ብሎ ለመናገር አዳጋች መሆኑን አቶ አያሌው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሰዎች የጠፉባቸው ነዋሪዎች ምናልባት በዋሻ ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመገመት ወደ ስፍራው እንደሚመጡ አመልክተዋል።
የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ግን “ከ20 በላይ ወጣቶች” በዋሻው ውስጥ ተቀብረዋል ብሏል።
የተደረመሰው ዋሻ ከ750 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ውስጥ ሳሉ የተደረመሰባቸውን ሰዎች ለማውጣት ለዋሻው መግቢያ ቅርበት ባለው የውስጠኛ ክፍል በኩል ቁፋሮ እየተደረገ መሆኑን ሁለቱም የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, South Wollo Commu.
የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ከነዋሪዎች ጋር በመሆን ከሚንሸራተተው አፈር ጋር እየታገሉ አርብ እና ቅዳሜ በተደረጉ ቁፋሮዎች ወደ ዋሸው ውስጥ ብዙም ለመዝለቅ ባለመቻላቸው እስካሁን ውጤት እንዳላገኙ ተገልጿል።
የአካባቢው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን “ሰው ከመሬት በታች ከእነ ሕይወቱ ተቀብሮ ያለንበት ሁኔታ እጅግ አሳዛን ነው” በማለት ከመሬት በፍርስራሽ የተቀበሩ ሰዎችን በማውጣት ልምድ እና ቴክኖሎጂ ያላቸው ወገኖች በፍጥነት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ተማጽነዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ የሚገኘው የደላንታ ወረዳ ለጌጣጌጥ ሥራ ተፈላጊ የሆነው የኦፓል ማዕድን የሚገኝበት ስፍራ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ማዕድኑን በማውጣት ለገበያ ያቀርባሉ።
በዚህም አካባቢ የኦፓል ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ተደርምሶ በሰው ላይ ጉዳት ሲያደርስ የመጀመሪያው አለመሆኑን የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው አስታውሰው፣ ከዚህ በፊት በሕይወት እና በአካል ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
በአንድ ወቅም ዋሻ ተደርምሶበት ለሰባት ቀናት የቆየ ግለሰብ በቁፋሮ መውጣቱን በማንሳት አሁን አደጋው የደረሰበት አካባቢ ምንም እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያሉበት ቢሆንም፣ ሰዎቹ በሕይወት እንደሚተርፉ ተስፋ አድርገዋል።
ሦስተኛ ቀኑን የያዘው የነፍስ አድን ጥረት የሚፈለገውን ያህል እንዳልተፋጠነ በመጥቀስ ከነዋሪው ጋር በመሆን በቻሉት አቅም ሁሉ የተቀበሩትን ሰዎች ሕይወት ለማትረፍ ጥረታቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።












