የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በመርዓዊ የተፈጸመውን ግድያ ሊመረምር ነው

የመርዓዊ ከተማ በከፊል

የፎቶው ባለመብት, MERAWI COMMUNICATIONS

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመርማሪ ቦርድ በሰሜን ጎጃም በመርዓዊ ከተማ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተፈጽሟል የተባለውን የሰላማዊ ዜጎች ግድያ ሊመረምር መሆኑን አስታወቀ።

መርማሪ ቦርዱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ ምርመራ ሊያደርግ መሆኑን ምክትል ሰብሳቢዋ ዶ/ር ነጃት ግርማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ ሪፖርቱን ተከትሎ ቦርዱ ባደረገው ስብሰባ ወደ መርዓዊ ከተማ አቅንቶ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ ጉዟቸው መቼ እንደሚሆን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ኢሰመኮ “ማንነታቸውን አረጋግጬያለሁ” ያላቸው ቢያንስ 45 ሰዎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ጥር 20/2016 ዓ.ም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ መገደላቸውን ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር ከዚህ ከፍ እንደሚል እና ግድያው ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ እና መንገድ ላይ በተገኙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በተተኮሰባት ጥይት ሆስፒታል ከገባች በኋላ ሕይወቷ ማለፉንም ከህክምና ባለሙያዎች ቢቢሲ ሰምቷል።

መንግሥት እስካሁን ስለክስተቱ ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የመንግሥት ኃይሎች በመርዓዊ ታጣቂዎችን እንጂ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አላደረጉም በማለት ክሱን አስተባብለዋል።

ግድያው ከተፈጸመ ሁለት ሳምንት ማለፉን እና በርካታ ሚዲያዎች መዘገባቸውን አስመልክቶ ለምርመራ አልዘገያችሁም? ተብለው ምክትል ሰብሳቢዋ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሚዲያ ዘገባዎች እንደማይወሰኑ እና “ጥቆማዎችን እንዲሁም ይፋዊ የሆኑ ሪፖርቶችንም እንጠብቃለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የቦርዱ የሥራ ጊዜ በቅርቡ መራዘሙን ገልጸው ምርመራዎችን ማካሄድ ቢፈልጉም መሬት ላይ ወርደው ለመመርመር ግን በፀጥታው ሁኔታ እንደሚወሰን ምላሽ ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ለስድስት ወራት የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር 28/2016 ዓ.ም. ከማብቃቱ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በማድረግ የመርማሪ ቦርዱ የሥራ ጊዜን አራዝሟል።

በአማራ ክልል በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች ከሚደረገው ግጭት ጋር ተያይዞም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳሳቢነቱ መቀጠሉን የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ ኢሰመኮ ባወጣውም ሪፖርት በክልሉ በሚገኙት ሦስት የጎጃም ዞኖች በጥር ወር ከ65 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ መገደላቸውን አስፍሯል።

በክልሉ ባለው የፀጥታ ሁኔታ መርማሪዎቻቸው ጥሰቶች ተፈጽመዋል በተባሉ ሌሎች አካባቢዎች ተጉዘው ለመመርመር እንደተቸገሩም ዶክተር ነጃት አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምክትል ሰብሳቢዋ እንደገለጹት መርማሪዎቻቸው መሄድ የቻሉባቸው ስፍራዎች ጥቂቶች እንደሆኑ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት መጓዝ ያልቻሉባቸው ስፍራዎች በርካታ በመሆናቸው በቀጥታ መረጃ ከማግኘት አንጻር ችግር እንደሆነባቸው አመልክተዋል።

በመርዓዊ የተፈጸመውን ግድያን አስመልክቶ ምርመራ ካካሄዱ በኋላ የደረሱበትን ግኝት ለሕዝብ እንደሚያሳውቁ ምክትል ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

በመርዓዊ ከተማ ግድያው የተፈጸመው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣዊዎች ለሰዓታት ውጊያ አድርገው የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ መሆኑን ነዋሪዎች መግለጻቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ ጥቃቱን ተከትሎ ያናገራቸው የህክምና ባለሙያን ጨምሮ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎች የተመለከቷቸውን አስከሬኖች መሠረት በማድረግ “ከስድስት ዓመት ህጻን እስከ 75 ዓመት አዛውንት” ድረስ ያሉባቸው ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንዶችም የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ የአሜሪካ መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረት ድርጊቱን በማውገዝ ክስተቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ እና በግድያው ላይ ገለልተኛ ምርመራ ተደርጎም አጥፊዎች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው በሪፖርቶቻቸው አሳስበዋል።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የካቲት 6/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች ቢያንስ 1 ሺህ 606 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን፣ 824 ሰላማዊ ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም ቢያንስ 210 ሴቶች ላይ መደፈራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ማኅበሩ ባወጣው በዚህ መግለጫው በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ከ10 ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆች መታሰራቸውንም ገልጿል።

በአካባቢው የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡ ለሚያካሂደው ምርመራ እንቅፋት ሆኗል ያለው ማኅበሩ፣ የተገለጸው የተጎጂዎች አሃዝ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችልም አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ሰዎችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሺዎች የሚቆጠሩ እንደተፈቱ እና አሁንም በቁጥጥር ስር ያሉት በመቶዎች እንደሆኑ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።