አንድሬ ኦናና፡“ማንቸስተር ዩናይትድ የተሸነፈው በኔ ምክንያት ነው”

የማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ቡድኑ በባየር ሙኒክ የተሸነፈው “በኔ ምክንያት ነው” ሲል ኃላፊነት ወስዷል።

በብዙ ክስተቶች ታጅቦ በጀርመኗ መዲና ሙኒክ በተደረገው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ኦናና በፈፀመው ስህተት ምክንያት የመጀመሪያውን ጎል አስተናግዷል።

ባየር ሙኒክ በምድቡ የመጀመሪያ ፍልሚያ ማንቸስተር ዩናይትድን አስተናግዶ 4 - 3 ረትቷል።

ዩናይትድ ጨዋታውን የተሻለ ቅርፅ ይዘው ቢጀምሩትም አንድሬ ኦናና ያስተናገዳት ጎል የጨዋታውን መልክ ቀይራለች።

ቀያይ ሰይጣኖቹ የጀርመኑን ኃያል ቡድን ተፈታትነው ሶስት ጎል ቢያስቆጥሩም ከሽንፈት ሊታደጋቸው አልቻለም።

ለቲኤንቲ ስፖርት አስተያየቱን የሰጠው ኦናና “ይህ የግብ ጠባቂ ሕይወት ነው” ብሏል።

“በጣም ከባድ ነው። አጀማመራችን መልካም ነበር። ከኔ ስህተት በኋላ ግን ጨዋታው ተቀየረ። ሁኔታው ለኛ ከባድ ነው፤ በተለይ ደግሞ ለኔ። ቡድኔን የጎዳሁት እኔ ነኝ።

“[ተቀናቃኞቻችን] ብዙም ጥሩ አልነበሩም። የመጀመሪያውን ዒላማ የጠበቀ ኳስ ቢመቱ ተቆጠረብኝ። ቡድኑ ነጥብ ይዞ ያልወጣው በዚህ ስሕተት ምክንያት ነው።”

ኦናና አክሎ “ዛሬ ሽንፈት የቀመስነው በዚሁ ስሕተት ነው” ብሏል።

ቲኤንቲ ለተሰኘው ሚድያ ተንታኝ ሆኖ የቀረበው የቀድሞው የዩናይትድ ተጫዋች ሪዮ ፈርዲናንድ በኦናና ሐሳብ ይስማማል።

“ኳሱ ይህን ያህል ከባድ አልነበረም። ሊይዘው ይችል ነበር” ሲል በረኛውን ይወቅሳል።

ፈርዲናንድ እንደሚለው የትላንትናው ውጤት ዩናይትድ በያዝነው የውድድር ዘመን እያሳየ ያለው አቋምን የሚያሳይ ነው።

አንድሬ ባለፈው የዝውውር መስኮት ነበር ከኢንተር ሚላን ወደ ዩናይትድ በ47.2 ሚሊዮን ፓውንድ የመጣው።

ነገር ግን ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ በሁሉም ውድድሮች በስድስት ጨዋታ 14 ጎሎች አስተናግዷል።

የያዝነውን የውድድር ዘመን እየተንገዳገደ የጀመረው ማንቸስተር ዩናትይድ ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ምንም እንኳ ኦናና የጨዋታውን መልክ የቀየረች ስሕተት ቢሠራም ከባየርን ሙኒክ ተጫዋቾች የተቃጡ ሙከራዎችን ማክሸፍ ችሏል።

አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ግብ ጠባቂው ብቻውን ኃላፊነት ሊወስድ አይገባም ይህ የሁሉም ተጠያቂነት አለበት ብለዋል።

የቴን ሃግ ቡድን ሽንፈት ቢገጥመውም ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተደጋጋሚ ጎል በማስቆጠር ያሳየው ተጋድሎ አዎንታዊ ዕይታን አስችሮታል።

ይህም ሆኖ የተከላካይ መስመሩ መዳከም ለሽንፈት ዳርጎታል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በቻምፒዮንስ ሊግ ከባየርን ሙኒክ፣ ጋላታሳራይ እና ኮፐንሃቨን ተደልድሏል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ ቅዳሜ ምሽት በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከሜዳቸው ውጭ ከበርንሊ ይጫወታሉ።