የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተመልሷል፡ ተጠባቂ ጨዋታዎች የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, UEFA
የአምናው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ማንቸስተር ሲቲ ማክሰኞ የዘንድሮውን የመጀመሪያ ጨዋታ ያደርጋል።
የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድንን ጨምሮ አርሰናል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኒውካስል በዚህ ተወዳጅ ውድድር የሚሳተፉ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቡድኖች ናቸው።
ኒውካስል በምድብ ኤፍ ከፓሪ ሳን ዠርማ፣ ኤሲ ሚላ እና ከቀድሞው የቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ቦሩሲያ ዶርትመንድ ተደልድሏል።
ይህ ምድብ ለኒውካስል ሊከብደው እንደሚችል እሙን ነው።
ማንቸስተር ሲቲ በተቃራኒው ቀላል የሚባል ምድብ ውስጥ የሚገኝ ቡድን ነው። በምድብ ጂ ሲቲን ጨምሮ አርቢ ሊፕዚግ፣ ሬድ ስታር ቤልግሬድ እና ያንግ ቦይስ ይገኛሉ።
የስኮትላንዱ ሴልቲክ ከፌይኖርድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ላዚዮ ተመድቧል።
ለማንቸስተር ዩናይትድ ከባድ እንደሚሆን የሚጠበቀው ጨዋታ ከጀርመኑ ጉምቱ ቡድን ባየርን ሙኒክ የሚያደርገው ነው።
በምድብ ኤ ዩናይትድ ከባየርን ይመደብ እንጂ ኤፍሲ ኮፐንሃገን እና ጋላታሳራይ በተነፃፃሪ ቀላል ሊሆኑለት እንደሚችሉ ይገመታል።
አርሰናል ደግሞ ከአውሮፓ ሊግ አሸናፊዎቹ ሲቪያ እንዲሁም ከፒኤስቪ አይንድሆቨን እና ላንስ በሚገኙበት ምድብ ተቀምጧል።
ቻምፒዮንስ ሊግ ያለሮናልዶና ሜሲ
ዘንድሮ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ክሪስቲያኖ ሮናልዶም ሆነ ሊዮኔል ሜሲ በአውሮፓ ግዙፉ ውድድር አይሳተፉም።
ሁለቱ ከዋክብት ይህን መድረክ ለረዥም ጊዜ ነግሰውበት ቆይተዋል።
ሮናልዶ አውሮፓ በቃኝ ብሎ ወደ ሳዑዲ በማምራት ለአል-ናስር ይጫወታል። ሜሲ ደግሞ ወደ አሜሪካ አቅንቶ የኢንተር ማያሚ ተጫዋች ሆኗል።
ሁለቱ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ብራዚላዊው ኔይማር እና ፈረንሳዊው ካሪም ቤንዜማም ዘንድሮ አናያቸውም። ሁለቱም ወደ ሳዑዲ ሄደው ለአል ሂላል እና ለአል-ኢቲሃድ በመጫወት ላይ ይገኛሉ።
ቢሆንም የፓሪ ሳን ዠርማው ፈረንሳዊው አጥቂ ኪሊያን ምባፔ እና የማንቸስተር ሲቲው ናርዌጂያን አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ዓይን ተጥሎባቸዋል።
የባርሴሎናው ተጫዋች ላሚን ያማል ኳስ ሲያንከባልል ማየትም ደስታ የሚያጎናፅፍ ነው። የ16 ዓመቱ ታዳጊ በባርሴሎና ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች ከመሆን አልፎ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን በትንሽ ዕድሜው በመሰለፍና ጎል በማስቆጠር ታሪክ ፅፏል።
ቻምፒዮንስ ለግ ከመች እስከ መች?
የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች፡ ከመስከረም 8-9
ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች፡ ከመስከረም 22-23
ሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች፡ ከጥቅምት 13-14
አራተኛ ዙር ጨዋታዎች፡ ከጥቅምት 27-28
አምስተኛ ዙር ጨዋታዎች፡ ከኅዳር 18-19
ስድስተኛ ዙር ጨዋታዎች፡ ከታኅሣሥ 2-3
የመጨረሻዎቹ 16 ክለቦች ጥሎ ማለፍ፡ ከየካቲት 5 - መጋቢት 4
ሩብ ፍፃሜ፡ ከሚያዚያ 1-9
ግማሽ ፍፃሜ፡ ከሚያዚያ 22-30
ፍፃሜ፡ ቅዳሜ ግንቦት 24/2016
የፍፃሜው ፍልሚያ በግዙፉ የእንግሊዝ ዌምብሊ ስታድየም ይካሄዳል።
የዘንድሮውን ዋንጫ ማን ሊያነሳው ይችላል?
ማንቸስተር ሲቲ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ድጋሚ ሊያነሱ እንሚችሉ ከፍተኛ ዕድል ተሰጥቶታል።
ዩሮ ክለብ ኢንዴክስ የተባለው ድርጅት ባወጣው ግምት መሠረት ሲቲ፤ ከሪያል ማድሪድ እና ባየርን ሙኒክ ከፍ ያለግ ግምት አግኝቷል።
ሲቲ 37 በመቶ የማሸነፍ ዕድል ሲሰጠው፤ ሪያል ማድሪድ 13 በመቶ፤ ባየርን ሙኒክ ደግሞ 11 በመቶ ዕድል አለው ተብሏል።
የቀረው 19 በመቶ ዕድል የተሰጠው ከሶስቱ ቡድኖች ውጭ የሆነ አዲስ ክለብ ያነሳዋል ለሚል ግምት ነው።
ሲቲ፣ ማድሪድ እና ባየርን ምድባቸውን አልፈው ወደ ጥሎ ማለፍ የመድረስ 90 በመቶ ግምት አግኝተዋል።
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሁን ባለው ቅርፅ የሚካሄደው ለመጨረሻ ጊዜ ነው።
አሁን ባለው ቅርፅ መሠረት 32 ቡድኖች በስምት ምድብ ተደልድለው ሁለቱ ከፍተኛ ነጥብ ያላቸው ቡድኖች ወደ ጥሎ ማለፍ ያልፋሉ።
ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን በኋላ ጀምሮ ይህ ይቀርና 36 ቡድኖች በውድድሩ የሚሳተፉ ይሆናል።












