ፖል ፖግባ አበረታች መድኃኒት በመውሰድ ተጠርጥሮ ከእግር ኳስ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጁቬንቱስ አማካይ ፖል ፖግባ አበረታች መድኃኒት በመውሰድ ተጠርጥሮ ለጊዜው ከእግር ኳስ መታገዱ ተሰምቷል።
የጣሊያን ፀረ-አበረታች መድኃኒት ችሎት በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 20 ጁቬንቱስ ዩዲኒዜን 3-0 ሲረታ ፖግባ ‘ቴስቴስትሮን’ ከፍ የሚያደርግ መድኃኒት ወስዷል ብሏል።
ፈረንሳዊው የ30 ዓመት አማካይ በዚህ ጨዋታ ባይሰለፍም ከግጥሚያው በኋኃ በነብስ ወከፍ ተመርጠው ከተመረመሩ ተጫዋቾች መካከል ነበር።
ፖግባ አበረታች መድኃኒት መውሰዱ ከተረጋገጠ ከሁለት እስከ አራት ዓመት ከእግር ኳስ ሊታገድ ይችላል።
ጁቬንቱስ በለቀቀው መግለጫ “ፖል ላቢሌ ፖግባ ነሐሴ 20 በተደረገው ምርመራ ውጤት መሠት፤ ዛሬ ጳጉሜ መስከረም 11/2023 ከፀረ-አበረታች መድኃኒት ችሎት ለጊዜው ከእግር ኳስ ታግዷል” ብሏል።
“ክለባችን ቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለበት ይመክራል” ይላል መግለጫው አክሎ።
በቅፅል ስሙ ናዶ የሚባለው ችሎት እንዳለው ፖግባ የፀረ-አበረታች መድኃኒት ሕጉን የጣሰው ‘ቴስቴስትሮን’ የተባለውን ሆርሞን ከፍ የሚያደርግ መድኃኒት ወስዶ በመገኘቱ ነው ብሏል።
ቴስቴስትሮን የአትሌቶችን ጥንካሬ ከፍ የሚያደርግ የሆርሞን ዓይነት ነው።
ፖግባ በሶስት ቀናት ውስጥ የችሎቱን ውጤት ውድቅ የሚያደርግ ዝርዝር መረጃ ይዞ መቅረብ አለበት።
ፖግባ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያለውን ውል ካጠናቀቀ በኋላ ሐምሌ 2022 ነው ወደ ቀድሞ ክለቡ በነፃ የተዘዋወረው።
ነገር ግን ወደ ጣሊያን ከተመለሰ በኋላ በተደጋጋሚ ጉዳት ስለሚያጋጥመው በጥቂት ጨዋታዎች ብቻ ነው መሰለፍ የቻለው።
አልፎም በካታር በተደረገው የዓለም ዋንጫ በጉዳት ምክንያት ለሃገሩ ፈረንሳይ መጫወት አልቻለም።
ፖግባ በያዝነው የውድድር ዓመት ጁቬንቱስ ከቦሎኛ እና ከኢምፖሊ ሲጋጠም ተቀይሮ ገብቶ በድምሩ 51 ደቂቃ ተጫውቷል።
ባለፈው የውድድር ዘመን ደግሞ በስድስት የሴሪ አ ጨዋታዎች ተቀይሮ የገባ ሲሆን 162 ደቂቃዎች ብቻ ነው ሜዳ ላይ ያሳለፈው።
በተደጋጋሚ ጉዳት የሚያጋጥመው ፖግባ በቅርቡ ባጋጠመው የጀርባ ሕመም ምክንያት ከሜዳ መራቁን የጁቬንቱሱ አሠልጣኝ ማሲሞ አሌግሪ ገልጠዋል።












