ሄርሞሶን የሳሙት የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ሩቢያሌስ ሥልጣናቸውን ለቀቁ

ሉዊስ ሩቢያሌስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ስታነሳ የተጫዋቿ ጄኒ ሄርሞሶን ከንፈር ሲስሙ በቴሌቪዝኝ መስኮት የታዩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ሉዊስ ሩቢያሌስ ሥልጣናቸውን ለቀቁ።

የ33 ዓመቷ ሄርሞሶ ሩቢያሌስ ያለፈቃዷ እንደሳሟት ገልጣ ባለፈው ማክሰኞ ክስ መመሥረቷ ይታወሳል።

ሩቢያሌስ ለጊዜያዊው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ፔድሮ ሮቻ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ይፋ አድርገዋል።

“ሥራዬን ልቀጥል አልችልም” ሲሉ ፒርስ ሞርጋን ለተሰኘው እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ ተናግረዋል።

የ46 ዓመቱ ግለሰብ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ራሳቸውን አግልለዋል።

ሩቢያሌስ ተጫዋቿኝ በመሳማቸው ታላቅ ነቀፌታ የገጠማቸው ሲሆን በተደጋጋሚ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ሲጠየቁ አሻፈረኝ በማለታቸው መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

ሄርሞሶ ያለፈቃዴ ስመውኛል ማለቷን ተከትሎ ባለፈው አርብ በስፔን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሩቢያሌስን በወሲባዊ ጥቃትና ጫና ማሳደር ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል ታውቋል።

ሩቢያሌስ “በፈቃድና በመግባባት ነው” የሳምኳት ቢሉም ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ላልተወሰነ ጊዜ ከሥልጣናቸው አግዷቸው ነበር።

“ፊፋ ባደረገው ቅፅበታዊ ውሳኔ እንዲሁም በሌሎች የተመሠረቱብኝ ክሶች ምክንያት ወደ ሥልጣኔ የማልመለስ ይሆናል” ይላል ሩቢያሌስ ያሰራጩት መግለጫ።

“ሥልጣን ላይ ለመቆየት መወሰኔ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ጎን የለውም፤ ለፌዴሬሽኑም ይሁን ለስፔን እግር ኳስ።”

ከሥልጣን መልቀቃቸው በአውሮፓዊያኑ 2030 ከፖርቹጋል እና ሞሮኮ ጋር የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ላቀደችው ስፔን መልካም ዜና ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጠዋል።

“ሴት ልጆቼና ቤተሰቤ እንዲሁም የሚወዱኝ ሰዎች እኔ ላይ በደረሰው ምክንያት ተንገላተዋል። መጠን አልባ ፍርድና ሐሰተኛ ክስ ቢቀርብብኝም ቀን ተቀን እውነት መጋለጧ አይቀርም” ብለዋል።

የዓለም ዋንጫ ያነሱት 23 ተጫዋቾችን ጨምሮ 81 የስፔን እግር ኳሰኞች ሩቢያሌስ ሥልጣን ላይ ሳለ ለብሔራዊ ቡድኑ አንጫወትም ብለው ነበር።

የሩቢያሌስ ቀኝ እጅ ናቸው የሚባሉት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኙ ሆርጌ ቪልዳ ተባረው በምትካቸው ሞንትሴ ቶሜ ተሹመዋል።

ፖለቲከኞች፣ እግር ኳስ ተጫዋቾችና ታዋቂ ሰዎች ሩቢያሌስን በይፋ ወቅሰዋል። ባለፈው ወር የሕግ ሰዎች በፌዴሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው ሰውዬው ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል።

በስተመጨረሻ ከሥልጣን ለምን ለመውረድ እንደወሰኑ ፒርስ ሞርጋን ሲጠይቃቸው ከቤተሰብና ከጓደኞቻቸው በተሰጣቸው ምክር ምክንያት እንደሆነ ሩቢያሌስ ተናግረዋል።

“አባቴ፣ ሴት ልጆቼ አናገሩኝ። ጉዳዩ ስለኔ አይደለም። የቅርብ ጓደኞች «ስለክብርህ እና ስለወደፊት ሕይወትህ ልታስብ ይገባል፤ የምትወዳቸውን ሰዎች ሕይወት ልታበላሽ ነው» አሉኝ” ብለዋል።

የስፔን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡትን ማስረጃዎች አሰባስቦ ሩቢያሌስ ላይ ክስ ይመሰርታል ተብሎ ይጠበቃል።

ወሲባዊ ጥቃት በስፔን ሕግ መሠረት ከገንዘብ ቅጣት እስከ አራት ዓመት እስር ሊዳርግ ይችላል።