ትራምፕ በንግድ ዙርያ ንግግር ለማድረግ ከፈለጉ የጣሉትን ታሪፍ እንዲያነሱ ቻይና አሳሰበች

ወደብ ላይ የሚገኝ ሸቀጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት ለማስቆም ቁርጠኛ መሆናቸውን ለማሳየት ወደ አገራቸው በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ እንዲሰርዙ ጠየቀች።

የትራምፕ አስተዳደር የንግድ ውይይት እየተካሄድ መሆኑን ቢገልጽም ይህ ከእውነት የራቀ መሆኑን አንድ የቻይና ባለስልጣን ተናግረዋል።

በሁለቱ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች መካከል ያለው የንግድ ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን በተጣለባት ታሪፍ ምክንያት ቻይና ከአሜሪካ ያዘዘችውን ቦይንግ አውሮፕላኖች አልፈልግም በማለት መልሳለች።

ትራምፕ በቻይና ላይ ያላቸውን አቋም መለዘብ የተያበት መሆኑ ሲገለጽ እስካሁን በቻይና ምርቶች ላይ የጣሉት ቀረጥ "በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል" ቢሉም "ዜሮ ግን አይሆንም" ብለዋል።

በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ጦርነት እየተፋፋመ ሲሆን ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ እስከ 145 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ሲጥሉ ቻይና ደግሞ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 125 በመቶ ቀረጥ ጥላለች።

ቻይና በታሪፍ ጦርነቱ ዙሪያ እስካሁን ከሰጠቻቸው በጣም ጠንካራው ነው በተባለለት መግለጫ የንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ሄ ያዶንግ ችግሩን ለመፍታት በቻይና ላይ የተጣለውን ሁሉንም "የአንድ ወገን ታሪፍ" አሜሪካ ማስወገድ አለባት ብለዋል።

"ታሪፉን የጣለው ሰው ይህንን መቀልበስ አለበት" ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን ደግሞ ቻይና እና አሜሪካ "ስምምነት ላይ መደረስ ይቅርና በታሪፍ ላይ ምክክርም ሆነ ድርድር አላደረጉም" ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ያሉ ዘገባዎች "ውሸት" መሆናቸውንም አክለዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገሮች መካከል ድርድር "እየተካሄደ" ነው ቢሉም፤ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት መንም ድርድር አልተጀመረም ሲሉ ተቃራኒ ሃሳብ አቅርበዋል።

ቤሴንት አክለውም በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና የንግድ ልውውጥ ላይ "ትልቅ ስምምነት" ለመፍጠር ዕድል አለ ብለዋል።

ከዚህ ቀደም "ዘላቂ ያልሆነው" የንግድ ጦርነት እንደሚለዝብ ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን አሁን ያለው ሁኔታ "ቀልድ አይደለም" ብለዋል።

ትራምፕ የንግድ ስምምነቱንን ለማሳካት ከቤጂንግ ጋር የሚያደርጉት ድርድር "በጣም ጥሩ" እንደሚሆን ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ቻይና በቅርቡ የወሰደችውን እርምጃ ተከትሎ ትሩዝ በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ቻእና በሚያምር ሁኔታ የተጠናቀቁትን አውሮፕላኖች ባለመውሰዷ ቦይንግ ሊቀጣት ይገባል" ብለዋል።

"ይህ ቻይና ለዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ያደረገችውን ትንሹ ማሳያ ነው" ከማለት ባለፈ ሰው ሰራሽ ኦፒዮይድ ፌንታሊን "ከቻይና በሜክሲኮ እና በካናዳ በኩል ወደ አገራችን መግባቱን በመቀጠሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን እየገደለ" ነው የሚለውን ውንጀላ ደግመዋል።

የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ከታሪፉ ጋር በተያያዘ ቻይና በወሰደችው የበቀል እርምጃ ከአሜሪካ ያዘዘችውን አውሮፕላኖች መልሳ እንደላከች ገልጿል።

በዚህ ሳምንት ሁለት አውሮፕላኖች መመለሳቸውን ኬሊ ኦርትበርግ ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት ተከትሎ ሌላ አውሮፕላንም ሊመለስ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከ80 የሚበልጡ የውጭ ኩባንያዎች የአሜሪካ ታሪፍ በቻይና ኢንቨስትመንታቸው ላይ እያሳደረ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ቻይና ረቡዕ ዕለት ውይይት ማድረጓን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የንግድ ምክትል ሚኒስትሩ ሊንግ ጂ "የውጭ ኩባንያዎች ፈተናዎችን ወደ እድሎች እንደሚቀይሩ ተስፋ ይደረጋል" ብለዋል።