ራሱን 200 ጊዜ በእባብ ያስነደፈው ግለሰብ ደም ለእባብ መርዝ መድኃኒት እንደሚሆን ተገለጸ

እባብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው ቲም ፍሬዲ ራሱን ከ200 ጊዜ በላይ ለእባብ መርዝ ሲያጋልጥ ወደ 20 ዓመታት ገደማ ቆይቷል።

በደሙ ላይ በተሠራ ጥናት መሠረት ደሙ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ለተለያዩ ዓይነት የእባብ መርዞች መድኃኒት እንደሚሆን ማወቅ ተችሏል።

ለእባብ መርዝ አንድ ዓለም አቀፍ መድኃኒት ለማግኘት የቲም የ18 ዓመታት ምርምር ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች ተናግረዋል።

በየዓመቱ 14,000 ሰዎች እባብ ነድፏቸው ይሞታሉ፣ አካላቸውም የሚጎድል በርካቶች ናቸው።

ቲም ከ200 ጊዜ በላይ ራሱን በእባብ ሲያስነድፍ ከ700 በላይ የእባብ መርዝም ወደ ሰውነቱ አስገብቷል።

አደገኛ ከሆኑት ማምባ፣ ኮብራ፣ ታይፓን እና ክራት እባቦች የተገኙ መርዞች በሰውነቱ ገብተዋል።

ግለሰቡ እራሱን ከእባብ መርዝ ለመከላከል ሲል ሰውነቱ የእባብ መርዝ የመከላከል አቅም እንዲያዳብር ነበር በእባብ ሲያስነድፍ የነበረው።

ኮብራ ነድፎች ኮማ ውስጥ ገብቶም ያውቃል።

"መሞት ወይም አካሌን ማጣት አልፈልግም። ሥራዬን ማጣትም አልፈልግም ነበር" ይላል።

"እባብ ነድፏቸው የሚሞቱ ሰዎችን ለማዳን ምርምሬን ቀጠልኩ" ሲልም ተናግሯል።

የእባብ መርዝ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ መርዙን በትንሹ ወደ ሰውነት ዳግመኛ በማስገባት የተነደፉ ሰዎችን ለማዳን ይሞከራል።

ሰውነት በተፈጥሮ ከተለያዩ ነገሮች ራሱን ለመከላከል የሚሞክረውም በዚህ ሂደት ነው።

በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እባቦች መርዛቸው በሌሎች አካባቢ ከሚኖሩ እባቦች የተለየ ስለሆነ ወጥ የሆነ የእባብ መርዝ ማርከሻ መድኃኒት ለማግኘት ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።

የእባብ መርዞችን የተለያዩ የሚያደርጉ ይዘቶችን በመተው የሚያመሳስላቸው ይዘት ላይ በማተኮር ሳይንቲስቶች ጥናታቸውን ቀጥለዋል።

በባዮቴክ ተቋሙ ሴንቲቫክስ የሚሠሩት ዶ/ር ጃኮብ ግላንቪል እና ቲም የተገናኙትም በዚህ ምርምር ወቅት ነው።

"የእሱን ያህል ሰውነቱ የእባብ መርዝ መከላከያ ያመረተ ሰው የለም። ደውዬለት ከደምህ ናሙና ልውሰድ አልኩት እና ተስማማ" ይላሉ ዶ/ር ጃኮብ።

ምርምር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥናቱ ያተኮረው የማምባ፣ ኮብራ፣ ታይፓን እና ክራት እባቦች መርዞች ላይ ነው።

መርዛቸው ሰውነት መንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎ የአተነፋፈስ ሥርዓትን ያስቆማል።

የዓለም ጤና ድርጅት የለያቸው 19 የአደገኛ እባቦች መርዞች ላይ የቲም ደም ሙከራ ተደርጎበታል።

አይጦች ላይ ሙከራ ተደርጎ ከ19 የእባብ መርዞች 13 ዓይነቱን መቋቋም ተችሏል።

"ይህም በጣም ብዙ የእባብ መርዝ አይነቶችን ይሸፍናል" ይላሉ ባለሙያው።

ሌላው ጥናት የተደረገበት የእባብ መርዝ ዓይነት ቫይፐር ሲሆን፣ የደም ዝውውርን የሚገታ መርዝ ነው።

"በቀጣይ 10 ወይም 15 ዓመታት ውጤታማ መድኃኒት ይገኛል። የቲም ደም በጣም አስደናቂ ነው። ሰውነቱ የእበባ መርዝ የመከላከል አቅሙን አዳብሯል" ሲሉ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የምርምር ቡድኑ ባልደረባ ፕሮፌሰር ፒተር ኮንግ ይናገራሉ።

ለየትኛውም የእባብ መርዝ ዓይነት አንድ መድኃኒት ማግኘት ነው የሳይንቲስቶቹ ግብ።

የእባብ መርዝ ላይ ጥናት የሚሠሩት ፕሮፌሰር ኒክ ካስዌል እንደሚሉት ይህንን መድኃኒት ማግኘት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል።

ሆኖም ግን ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው።

ቲም ደሙ ለዚህ ምርምር መዋሉ "በጣም ጥሩ ስሜት ይሰጠኛል" ይላል።

"ለሰው ልጆች ጥሩ ነገር እያደረግኩ ነው። ይሄን ማድረግ ለእኔ ትልቅ ዋጋ ነው ያለው። በጣም ኩራት ይሰማኛል" ሲልም ያክላል።