የተባበሩት መንግሥታት ዳኛ ኡጋንዳዊት ሴትን በባርነት በመያዛቸው እስራት ተፈረደባቸው

የተባበሩት መንግሥታት ዳኛ

የፎቶው ባለመብት, Thames Valley Police

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት ዳኛ እና በኡጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሊድያ

የተባበሩት መንግሥታት ዳኛ በቤታቸው አንዲት ሠራተኛን በባርነት በመያዛቸው የስድስት ዓመት ከአራት ወር እስራት ተፈረደባቸው።

የ50 ዓመቷ ሊድያ ሙጋምቤ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፒኤችዲ እየተማሩ ሲሆን፣ ወጣት ኡጋንዳዊት ሴትን ሳይከፍሏት ሠራተኛ እና ሞግዚት እንዳደረጓት ፖሊስ ደርሶበታል።

በኡጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሊዲያ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በኋላ በኦክስፎርድ ታስረዋል።

ፍርዱን ያስተላለፉት ዳኛ ዴቪድ ፎክስተን ተከሳሿ "ምንም ፀፀት አላሳዩም" ብለዋል። እንዲያውም ተበዳዩዋን ጥፋተኛ ማድረጋቸውን ዳኛው ተናግረዋል።

ወጣቷ ከኡጋንዳ እንድትወጣ ቪዛ የተመቻቸላት በቀድሞው የኡጋንዳ ከፍተኛ አምባሳደር ቤት እንደምትቀጠር ተገልጾላት ነበር።

በለንደን የቀድሞው የኡጋንዳ አምባሳደር ጆን ሙጋምቤ ቪዛውን ለወጣቷ ያመቻቹት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከሄደች በኋላ በሊዲያ ሙጋምቤ ቤት በሠራተኛነት እንደምትሠራ እያወቁ ነው።

ሊዲያ ሙጋምቤ ለዚህ በምላሹ ጆን ሙጋምቤ በኡጋንዳ በነበራቸው ክስ ትብብር አድርገዋል።

በኦክስፎርድ በባርነት እየሠራች የነበረችውን ወጣት ጉዳይ የተመለከቱት ዳኛ "በጣም አሳዛኝ ነው" ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ ካሮላይን ሀግሊ በፍርድ ቤት ባነበቡት የወጣቷ ምስክርነት ላይ ወጣቷ "ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ነበርኩ። በተለይ ደግሞ ሊዲያ በኡጋንዳ ያላትን ቦታ ስለማውቅ ፈርቼ ነበር" ብላለች።

የ50 ዓመቷ ሊድያ ሙጋምቤ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፒኤችዲ እየተማሩ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Thames Valley Police

የምስሉ መግለጫ, የ50 ዓመቷ ሊድያ ሙጋምቤ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፒኤችዲ እየተማሩ ነበር

ወደ ኡጋንዳ ከተመለሰች ምን ሊደርስባት እንደሚችል በመፍራት ወደ አገሯ መሄድም አልቻለችም። እናቷን እስከመጨረሻው እንደማታይ ይሰማትም ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም ያለውን የሠራተኞች ሕግ ባለማወቋና ሊዲያ ሙጋምቤ ኃያል ሴት በመሆናቸው ምክንያት ወጣቷ እንደተበዘበዘች ተገልጿል።

ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንድትሄድ ያደረጉት ጆን ሙጋምቤ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ለብዝበዛ በመመሳጠር መከሰስ እንዳለባቸው ፍርድ ቤት አስታውቋል። እስካሁን የኡጋንዳ መንግሥት ያለመከሰስ መብታቸውን አላነሳም።

ሊዲያ ሙጋምቤ ወጣቷን እንድትሠራ እንዳላስገደዱ እና "በፍቅር" እንደያዙዋት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዳኛው ግን "ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ነበረች። ወንጀል ነው። ወጣቷ የደረሰባትን በድፍረት መናገሯ ሌሎችን ተጎጂዎችም ያበረታታል" ብለዋል።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲም የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል።