የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ከኢራን ጥቃት ግምገማ በኋላ የስለላ ኃላፊውን አባረረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግዝ ዋይት ሐውስ አሜሪካ በኢራን ላይ የፈፀመችው ጥቃት ግምገማ ላይ ማስተባበያ ከሰጠ ከሳምንታት በኋላ የፔንታጎን የስለላ ኃላፊን ከሥልጣናቸው አባረሩ።
ፔንታጎን በመግለጫው ሌተናል ጄኔራል ጄፍሪ ክሩስ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ መረጃ ኤጀንሲ (DIA) ኃላፊ ሆነው አያገለግሉም ሲል ገልጿል። ሌሎች ሁለት ከፍተኛ የጦር አዛዦችም በፔንታጎን ከስልጣናቸው ተነስተዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ስለ ተባረሩበት ምክንያት ማብራሪያ አልሰጠም።
በሰኔ ወር ላይ አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን እንዳላወደመ የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ አሳይቶ ነበር።
ቅድመ ግምገማው ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ነው ያሳየው።
በወቅቱ ዋይት ሃውስ በበኩሉ "ይህ ፍጹም የተሳሳተ" ግምገማ" በማይረባ የደህንንት ማህበረሰብ ሾልኮ የወጣ ነው" ሲል ውድቅ አድርጎታል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል በማለት አጽንኦት ሰጥተው፤ "በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች መካከል አንዱ የሆነውን ለማዋረድ" በሚዲያዎች የሚደረግ ሙከራ ሲሉ ከሰዋል።
በወቅቱ በኔቶ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ሄግዝ ሪፖርቱ የተዘጋጀው "ዝቅተኛ የደህንነት መረጃ" ላይ ተመስርቶ መሆኑን እና ኤፍቢአይ ሾልኮ የወጣውን መረጃ እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክሩስ መባረር በመጀመሪያ የተዘገበው በዋሽንግተን ፖስት ነው።
የመከከላከያ የደህንነት ኤጀንሲ የፔንታጎን አንዱ አካል ሲሆን የተለያዩ ሥራዎችን ለመደገፍ በወታደራዊ መረጃ ላይ አተኩሮ ይሰራል።
ኤጀንሲው ከፍተኛ መጠን ያለው የቴክኒክ መረጃዎች የሚሰበስብ ቢሆንም እንደ ሲአይኤ ካሉ ሌሎች የስለላ እና የደህንነት ኤጀንሲዎች ግን የተለየ ነው።
ሄግዝ የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል ተጠባባቂ ዋና አዛዥ እና የባሕር ኃይል ልዩ የጦር አዛዥ አዛዥን ከስልጣን እንዲነሱ ማዘዛቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጭ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር ማርክ ዋርነር በሰጡት መግለጫ የክሩስ መባረር ትራምፕ "የደህንነት መስሪያ ቤቱን ለአገራችን ጥበቃ ከማዋል ይልቅ እንደ ታማኝነት መፈተኛ የመመልከት አደገኛ ባህሪ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ ከእርሳቸው ጋር የማይጣጣም ሃሳብ ያላቸውን በርካታ ባለሥልጣናት ከሥልጣናቸው አንስተዋል።
በሐምሌ ወር ትራምፕ የስራ እድገት መቀዛቀዙን ካሳወቀ በኋላ ቡድናቸውን የሠራተኞች ስታስቲክስ ኮሚሽነር ኤሪካ ማክታርፈርን "ወዲያውኑ" እንዲሰናብቱ ማዘዛቸው ተናግሯል።
በሚያዝያ ወር የብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ በአገሪቱ የሥራ እድገት መቀዛቀዙን ይፋ ካደረገ በኋላ ዳይሬክተሩን ጄኔራል ቲሞቲ ሃውንን እንዲሁም በርካታ የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ሠራተኞችን አሰናበተዋል።
ሄግዝ በፔንታጎን በርካታ ወታደራዊ ባለስልጣናትን አባርረዋል።
በየካቲት ወር የአየር ኃይል ጄኔራሉን ሲኬ ብራውንን ከአምስት አድሚራሎች እና ጄኔራሎች ጋር ከኃላፊነታቸው አሰናብተዋል።















