ኢራን በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈር ስላደረሰችው ጥቃት ምን እናውቃለን?

የፎቶው ባለመብት, USAF
ኢራን በሳምንቱ መገባደጃ በኒውክሌር ጣቢያዎቿ በአሜሪካ ለተፈፀመባት ጥቃት በኳታር የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የሚሳዔል ጥቃት ፈፅማለች።
የዓይን እማኞች በዶሃ ሰማይ ላይ ከባድ የፍንዳታ ድምፅ መስማታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ በተንቀሳቃሽ ምስሎች የአየር መከላከያ ስርዓቶች ሚሳኤሎችን ለማክሸፍ ሲሞክሩ በሰማይ የብርሃን ብልጭታ ታይቷል።
ጥቃቱ በኢራን፣ እስራኤል እና አሜሪካ መካከል ግጭቱ መካረሩን ያሳየ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረቶች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩን ጠቋሚ ነው።
ኢራን ምን ላይ ነው ያነጣጠረችው? ለምን?
የኢራን ሚሳዔሎች በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፉ የአሜሪካ ጦር ሰፈር በሆነው አል ኡዲድ ያነጣጠሩ ሲሆን፤ ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ ሦስት የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎችን መደብደቧን ተከትሎ የተሰጠ አፀፋዊ እርምጃ ነው ተብሏል።
አል ኡዲድ በቀጣናው የአሜሪካ ጦር የሁሉም የአየር ተልዕኮ ዋና ጣቢያ ነው።
አንዳንድ የብሪታኒያ ወታደሮችም ተራ በተራ በጣቢያው ይሰራሉ።
ጥቃቱ መፈፀሙ መጀመሪያ በኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ከዚያም በጦሩ በኩል ታውጇል።
የኢራን ጦር ፈርጣማ ቅርንጫፍ የሆነው እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ "ኢራን በሉዓላዊነቷ ላይ የተቃጡ ማንኛውንም ጥቃቶች ምላሽ ሳትሰጥ አትቀመጥም" ብሏል።
"በቀጣናው የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ጥንካሬ ሳይሆኑ ድክመቶች ናቸው" በማለትም አክሏል።
አሜሪካ በኒውክሌር ጣቢያዎቿ ላይ ለፈፀመችው ጥቃት ኢራን የአፀፋ እርምጃ እንዳትወስድ አስጠንቅቃ የነበረ ሲሆን፤ በቴህራን የሚገኙ መሪዎች በቀጣናው ያለውን ግጭት ለመቋጨት ወደ ዲፕሎማሲ እንዲመጡ ጥሪ አቅርባለች።
በኳታር ምን ያህል ሚሳኤሎች እንደተተኮሱ የተለያዩዩ ዘገባዎች አሉ። ኢራን ስድስት ሚሳዔሎችን ተኮስኩ ስትል አሜሪካ በበኩሏ 14፤ ኳታር ደግሞ 19 በማለት ሁሉም መክሸፋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስካሁን በጥቃቱ የተገደለ ወይንም የቆሰለ ሰው የለም ተብሏል።
ከጥቃቱ ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ዜጎቻቸው ወደ መጠለያ እንዲገቡ ምክር ሰጥተዋል።
8 ሺህ የሚሆኑ የአሜሪካ ዜጎች በኳታር እንደሚኖሩ አገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ የሚጠቁም ሲሆን፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ የብሪታኒያ ዜጎችም ይኖራሉ።
ከጥቃቱ በኋላ ምን ተባለ?
ኢራን የሚሳዔል ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀች መሆኑን ማስጠንቀቋ ከጥቃቱ በኋላ ግልፅ ሆኗል።
ሦስት የኢራን ሹማምንት ለኒዮርክ ታይምስ ቴህራን የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ፍላጎቷን ለዶሃ አስቀድማ ማሳወቋ ተናግረዋል።
ከጥቃቱ በኋላ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን "አስቀድማ በማሳወቋ" ያመሰገኑ ሲሆን፤ ይህም የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እና ጉዳት እንዳይደርስ አድርጓል ብለዋል።
"በጣም ደካማ" ሲሉ ጥቃቱን የገለፁት ትራምፕ፤ አንድም አሜሪካዊ አለመጎዳቱን እና ያደረሰው አጠቃላይ ጉዳት አነስተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
"ለሰላም ምንም እድል የለም" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥቃቱን "ድንገተኛ" እና "በሉዓላዊነት ላይ ግልፅ ጥሰት" ብለውታል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "በቀጣናው የእስራኤልን የግስጋሴን አደገኛነት በመጀመሪያ ያስጠነቀቀችው ኳታር ናት" ብለዋል።
የኢራን ታላቅ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ኢራን በጥቃቱ ማንንም እንዳልጎዳች ነገር ግን አገራቸው "ለማንኛውም ጥቃት አትንበረከክም" ብለዋል።
"ማንንም አላጠቃንም፤ እናም በየትኛውም ስንጠቃ በምንም ሁኔታ አንቀበልም። ለየትኛውም ጥቃት እጅ አንሰጥም፤ ይህ የኢራን አመንክዮ ነው" ሲሉ በኤክስ ገፃቸው አስፍረዋል።
ጥቃቱ የማይቀር ለመሆኑ ምልክቶች ምን ነበሩ?
ሰኞ ዕለት አሜሪካ ኢራን በኳታር የሚሳዔል ጥቃት ለመፈፀም እተዘጋጀት ነው የሚል ጥርጣሬ ነበራት።
ጥቃቱ ከመፈፀሙ ከሰዓታት በፊት ኳታር የአየር ክልሏን በጊዜያዊነት እንደምትዘጋ አስታወቀች። ይህንም ያሳወቀችው የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ዜጎች እንዲጠለሉ ከተነገረ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነው።
እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ጥቃቱ የማይቀር ስለመሆኑ ግልፅ ምልክት አልሰጡም።
አሜሪካ ትዕዛዙን የሰጠችው "ለጥንቃቄ" ሲባል እንደሆነ ስትገልፅ፤ ብሪታኒያ ደግሞ የአሜሪካን መሪነት በመከተል ነው ብላለች።
ነገር ግን ከጥቃቱ ከሰዓታት በፊት ቢቢሲ በጦር ሰፈሩ "ተጨባጭ ስጋት" መደቀኑን መረዳት ችሏል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በስም ያልጠቀሷቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሰው የኢራን ሚሳዔሎች በኳታር ጥቃት ለማድረስ ፊታቸውን አዙረው መደቀናቸውን ዘግዋል።
የበረራ መከታተያ ድረ ገፆች በጥቃቱ በፊት አውሮፕላኖች ማረፊያቸውን መቀየራቸውን አሳይተዋል።
'ፍላይትራዳር24 የተባለ የበረራ መከታተያ ከሚሳዔል ጥቃቱ በፊት ወደ ዶሃ እየተጓዙ የነበሩ 100 በረራዎች ነበሩ ብሏል።
ሀማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የዓለማችን 10 በመንገደኞች የተጨናነቀ አየር ማረፊያ ውስጥ ቀዳሚ ሲሆን፤ በየቀኑ 140 ሺህ መንገደኞችን ያስተናግዳል።
በቀጣናው ባሕሬን እና ኩዌትን ጨምሮ ሌሎች አገራት ለአጭር ጊዜም ቢሆን የአየር ክልላቸውን ዘግተው ነበር።
እዚህ የደረስነው እንዴት ነው?
ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒወክሌር ጣቢያዎች ግዙፍ የተባለ ጥቃት አድርሳለች።
ይህም በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት አሜሪካ ልትቀላቀል ትችላለች የሚለውን የበርካታ ቀናት ውዝግብ የፈታ ሆኗል።
እስራኤል በየቀኑ በኢራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ጣቢያዎች የሚሳዔል ጥቃት እየፈፀመች ሲሆን፤ የእስራኤል መንግሥት የኢራንን አይቀሬ የኒውክሌር መሳሪያ ግንባታ ለመከላከል አስፈላጊ ነው ይላል።
ተከታታይ የእስራኤል እና የአሜሪካ መንግሥታት ኢራን ኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ለመከላከል ፍላጎት አላቸው።
ኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ እንደሚውል በተደጋጋሚ ትገልፃለች።
አሜሪካ በፈፀመችው ድብደባ የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሷን ብትገልጽም እስካሁን የጥቃቱ ሙሉ ተፅዕኖ ምን ያህል ነው የሚለው በግልፅ አይታወቅም።
በእስራኤል እና ኢራን መካከል ጥቃቶች ከእሁድ እስከ ሰኞ ድረስ ቀጥሏል።















