የሲአይኤ ዳይሬክተር የኢራን የኒውክሌር ተቋማት "ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል" አሉ

የኢራንን ተራሮች የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሲአይኤ ዳይሬክተር አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር ተቋሞች ላይ የፈጸመችው ጥቃት "ከፍተኛ ጉዳት" አድርሶ በዓመታትን ወደኋላ እንዲመለሱ እንዳደረጋቸው በመግለጽ ሾልኮ ከወጣው እና ፕሬዚደንት ትራምፕን ካስቆጣው የደህንነት መረጃ የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል።

የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ቁልፍ ቦታዎች ወድመዋል ያሉ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ተወግደዋል ከማለት ግን ተቆጥበዋል።

የስለላ ተቋሙ ኃላፊ አስተያየት የተሰማው የፔንታጎን የደህንነት ኤጀንሲ የመጀመርያ ደረጃ ግምገማ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን አላወደመም የሚል ሪፖርት ሾልኮ ከወጣ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር ተቋማትን "ደምስሷል" ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "የሐሰተኛ ዜና" ሚዲያዎች "ዋሽተዋል፤ እንዲሁም አንዳቸውም የሌላቸውን እውነታ ሙሉ በሙሉ አዛንፈው አቅርበዋል" ሲሉ ለጥፈው ነበር።

የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግዝ እና ሌሎች ወታደራዊ ባለስልጣናት ሐሙስ ዕለት በፔንታጎን "የታላላቅ አሜሪካውያን አብራሪዎች ክብር ለመጠበቅ" "አስደናቂ እና ሊካድ የማይችል" ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል ።

ትራምፕ በኢራን እና በእስራኤል መካከል ለ12 ቀናት የተካሄደው የተኩስ ልውውጥ እንዲቆም ያደረጉት ጥረት እየሰመረ በሚመስልበት በዚህ ጊዜ ነው መረጃው ሾልኮ የወጣው።

ረቡዕ በኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ትራምፕ ስለ ጥቃቶቹ "በጣም ከባድ ነበር፤ መደምሰስ ነበር" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረገው ውይይትም ምናልባት ከኢራን የኒውክሌር ግንባታዋን ለማቆም ቁርጠኝነቷን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ኢራን ድርድር እንደሚካሄድ ምንም ዓይነት እውቅና አልሰጠችም።

ነገር ግን የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት በአገሮቹ መካከል ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እየተካሄደ ነው።

ራትክሊፍ በመግለጫቸው ሲአይኤ "ታማኝ እና ትክክለኛ ከሆነ ምንጭ ያገኘው አዲስ መረጃ በርካታ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ወድመዋል እና መልሶ ለመገንባት ዓመታትን ይወስዳል" ብለዋል።

የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሯ ቱልሲ ጋባርድ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ስለደረሰው ጉዳት ትራምፕ የሰጡትን አስተያየት ደግፈዋል

ዳይሬክተሯ በኤክስ ልጥፋቸው ላይ "ኢራናውያን ሦስቱንም ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከወሰኑ (ናታንዝ ፣ ፎርዶ፣እስፋሃን)፤ ሙሉ በሙሉ መገንባት አለባቸው።ይህ ደግሞ ዓመታት ሊወስድ ይችላል" ብለዋል።

አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት የፈጸመችው ድብደባ ሦስቱ ዋና ዋና የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን 125 የጦር ጄቶችን ያሳተፈ ነበር።

አዲስ የሳተላይት ምስሎች በፎርዶ ሁለት የመግቢያ ስፍራዎች ዙሪያ ስድስት ጉድጓዶች መፈጠራቸውን ያሳያሉ።

እንዲሁ በተመሳሳይ በእስፋሃንም ከጥቃቱ በኋላ ጉድጓዶች ተፈጥረዋል።

ነገር ግን ከመሬት በታች የሚገኙት የኒውክሌር ማብላያዎች ስለ መውደም አለመውደማቸው ግልጽ አይደለም።

ማክሰኞ ዕለት ከፔንታጎን የመከላከያ ደህንነት ኤጀንሲ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሾልኮ የወጣ ዘገባ የአሜሪካ የቦምብ ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን ምናልባት በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ያሳያል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ግምገማው የተደረገው "ዝቅተኛ እርግጠኛነት ባላቸው" ነው ብሏል።

ግምገማውን የሚያውቁ ባለስልጣናት መረጃው የመጀመርያ ደረጃ መሆኑን ገልፀው ተጨማሪ መረጃ ሲወጣ ሊለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

አሜሪካ 18 የስለላ ኤጀንሲዎች ያሏት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በተልዕኳቸው እና ባላቸው ክህሎት ላይ ተመስርተው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ዘገባዎችን ያዘጋጃሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ቴህራን ጥቃት ሲፈጸምባት በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገውን ዩራኒየም ወደ ሌላ ቦታ አዛውራለች።

ነገር ግን የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ ረቡዕ ዕለት ለአልጀዚራ እንደተናገሩት "የኒውክሌር ተቋሞቻችን በእርግጠኝነት ክፉኛ ተጎድተዋል" ያሉ ሲሆን ተጨማሪ ማብራርያ ግን አልሰጡም።

የእስራኤል የአቶሚክ ኢነርጂ ኮሚሽን በፎርዶ ላይ የተፈጸመው ድብደባ "የቦታውን ወሳኝ መሠረተ ልማት አውድሟል" ብሏል።

መግለጫው አክሎም በሁሉም ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት የኢራን የኒውክሌር ግንባታ "በበርካታ ዓመታት" ወደ ኋላ የመለሰ ነው ብሏል።

ሆኖም የኢራኑ ፓርላማ ሊቀመንበር አማካሪ መህዲ መሃሙዲ አሜሪካ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ ብዙም ሳይቆይ በፎርዶ ላይ "የከፋ ጉዳት አልደረሰም" ብለው ነበር።

ለረዥም ጊዜ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ አገልግሎት መሆኑን ትናገራለች። ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ቴህራን የአቶሚክ ጦር መሳሪያ እየገነባች አይደለም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።