ቢቢሲ ከአዲስ ምልምል የሶማሊያ የባሕር ላይ ዘራፊዎች ጋር ያደረገው ቆይታ

ሁለት የሶማሊያ ዓሳ አጥማጆች የፊታቸውን ጥምጣም ፈትተው በሚስጢር ወደተያዘው ቀጠሮ መጡ።
ዓሳ አጥማጆቹ በቅርቡ ነው መሣሪያቸውን ታጥቀው ወደ ዘረፋ የገቡት። ዓላማቸው ደግሞ ሰዎችን አግተው ሚሊዮን ዶላሮችን ማፈስ።
"መቅረፅ ትችላለህ። ችግር የለውም" ሲሉ ለቢቢሲው ጋዜጠኛ ነገሩት።
የባሕር ጠረፍ በሆነችው ኢል ከተማ የተሰናዳው ቀጠሮ ብዙ ወራትን የወሰደ ነው። ዘራፊዎቹ ፍራቻ ይታይባቸዋል። በህንድ ውቅያኖስ ላይ ሰዎችን የሚያሸብሩት ዘራፊዎች እንዲህ ይሸበራሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም።
የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ስትራቴጂካዊ ከመሆኑም ባሻገር የንፁህ ውሀ ምንጭም ነው። በአውሮፓውያኑ 2000 አጋማሽ የባሕር ላይ ዘረፋ ሲስፋፋ የሶማሊያ 'ፓይሬቶች' መቀመጫዎችን እዚህ አደረጉ።
ቦታው "ሀሩንታ ቡርካዳ" ይባላል። የባሕር ዘረፋ መዲና እንዳደማለት ነው። ነዳጅን ጨምሮ ዕቃ ጭነው በዚህ በኩል የሚያቋርጡ ግዙፍ መርከቦችን ዒላማ ያደርጋሉ። ይህ ስጋት ላይ የጣላቸው መርከበኞች መንገድ መቀየር ጀምረዋል።
የክልሉ ባለሥልጣናት ይህን ዝርፊያ የማስቆም ኃይል የላቸውም። የአካካቢው ፖሊስ ወደ ከተማዋ መግባት ይፈራል።
ከአውሮፓውያኑ 2005 እስከ 2012 ባለው ጊዜ የባሕር ላይ ዘራፊዎች ያጋበሱት ገንዘብ 413 ሚሊዮን ዶላር እንደሆ የዓለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል።
ነገር ግን የዓለም የባሕር ኃይሎች ተባብረው አካባቢውን መቆጣጠር ሲጀምሩ የፓይሬቶቹ ገበያ መቀዛቀዝ ጀመረ። የፑንትላንድ የባሕር ኃይል ፖሊስ መቀመጫው ኢል ከተማ ነው።
በዘራፊዎቹ ምክንያት በከተማዋ የኑሮ ውድነት እየጨመረ መጥቷል፤ ዕፆች እና የአልኮል መጠጥ ተስፋፍተው ነበር። ይህ ያስመረራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የባሕር ዘራፊዎቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ትክክል ነው ብለው ያምናሉ።
ነገር ግን ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ዓሳ አጥማጅ መርከበኞች አሁንም በአካካቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። ምክንያቱም አብዛኛው ነዋሪ የገቢ ምንጩ ዓሳ ማጥመድ ነው።
"መርከቦች መጥተው ቁሳቁሶቻችንን ይዘው ሄዱ" ሲል ፋራህ ለቢቢሲ ይናገራል። ፋራህ ከዓሳ አጥማጅነት ወደ ባሕር ላይ ዘራፊነት ተቀይሯል።
ፋራህ እና ጓደኛው ዲሪዬ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል። ፊታቸውን በነጭ ጨርቅ ሸፍነው ነው የመጡት።
ብዙውን ጊዜ ዓሳ አጥማጆች ፀሐይ ሳትወጣ ወደ ባሕር አምርተው እኩለ ቀን አካባቢ ፀሐይ ሳትጠነክር ነው የሚመለሱት።
ፋራህ እና ዲሪዬ እንደሚሉት ከዘመዶቻቸው መካከል አንዱ ዓሳ ለማጥመድ ወጥቶ እንደተገደለ ይናገራሉ።
ፋራህ "ውቅያኖሱ ሕይወታችን ነው" ይላል። "ሥራችን እና ሕይወታችን ውቅያኖሱ ነው። ይህ ውቅያኖስ ቢዝነሳችን ነው" ይላል።
በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉት ወንዶች ባለፈው ዓመት ወደ ባሕር ላይ ዘረፋ ሲሰማሩ ብቻቸውን አልነበሩም።
ኦፕሬሽን አትላንታ የተባለው የአውሮፓ ሕብረት የባሕር ኃይል በአቅራቢያው ቁጥጥር ያደርጋል። ከ2013 እስከ 2019 ባለው ጊዜ 26 ጊዜ የባሕር ላይ ዘረፋ ጥቃቶች ተደርጓል ይላል። ከ2020-2022 ባለው ጊዜ ግን አንድም ዘረፋ አልነበረም።
በ2023 ዝርፊያው በአዲስ መልክ ጀመረ። ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 6 ጊዜ ጥቃት ደርሷል። እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2024 እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ 22 የባሕር ላይ ዘረፋ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።
እርግጥ ነው አብዛኛዎቹ ዘረፋዎቹ ያልተሳኩ ናቸው። ነገር ግን የተሳኩ ሲሆኑ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ያስገኛሉ። ዘራፊዎቹ እንደሚሉት ባለፈው መጋቢት የታገተውን የባንግላዴሽ ንብረት የሆነችው ኤምቪ አብዱላህ ለማስለቀቅ 5 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏቸዋል።
የመርከቡ ባለቤቶች ስለገንዘብ መጠኑ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡም መርከቧ የተለቀቀችው በድርድር ነው ብለዋል።
በከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ፑንትላንድ ግዛት በምትገኘው ኢል ከተማ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደሚናገሩት እያንዳንዳቸው 12 አባላት ያሏቸው 10 የዘራፊ ቡድን አባላት ይንቀሳቀሳሉ።
በአንዳንድ ጊዜ ከ15-30 ቀናት ባሕር ላይ ይቆያሉ። አነስተኛ በሞተር የምትሠራ ጀልባቸውን ይዘው፤ ኤኬ 47 መሣሪያ ታጥቀው ነው የሚንቀሳቀሱት። በተጨማሪ አርፒጂ የተባሉ ፈንጂዎችን፣ ምግብ እና ነዳጅ ይዘው ነው የሚዞሩት።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Lali / BBC
ፋራህ እና ዲሪዬ ዓላማቸው በህንድ ውቅያኖስ ላይ መካከለኛ መጠን ያላትን መርከብ አግተው በጂፒኤስ አማካይነት ተለቅ ወደላው መርከብ መሄድ ነው።
"በፍጥነት የሚበሩ ጀልባዎችን ተጠቅመን መርከቦቹ ላይ ጥቃት መሰንዘር እንችላለን" ይላል ፋራህ።
ሮኬት ተኳሽ ባዙካም ይዘው ይንቀሳቀሳሉ።
"አርፒጂ ተጠቅመን መርከቦቹን እናስቆማለን። የማይቆሙ ከሆነ ደግሞ በላያቸው ላይ እንተኩሳለን። አንገድልም። አንድ ነገር ማግኘት እንጂ መግደል አይደለም ዓላማችን። ዓላማችን ማስፈራራት ነው" ይላል ዲሪዬ።
ቡድኖቹ አንዳንድ ጊዜ ተጣምረው መርከብ ካገቱ በኋላ የማስለቀቂያውን ገንዘብ ይከፋፈላሉ። ።
ለሁለት አስርታት በእርስ በርስ ጦርነት በላሸቀችው ሶማሊያ የጦር መሣሪያ ማግኘት ከባድ አይደለም። በኢል ከተማ ኤኬ-47 በ1200 ዶላር ይሸጣል።
ፋራህ እና ዲሪዬ የባሕር ላይ ዝርፊያ ጥግ በደረሰበት ወቅት አልተሳተፍንም ይላሉ። ጠመንጃቸውን ከሰቀሉ ዘራፊዎችም ምክር አልወሰዱም።
አብዛኛዎቹ የቀድሞ የባሕር ዘራፊዎች በአካካቢው የሉም። የተወሰኑት ሀገር ለቀው ሄደዋል። ሌሎቹ ደግሞ ሥራውን ትተውታል።
የቀድሞ የባሕር ላይ ዘራፊ የነበረው አብዲራህማን ባኬልዬ በ2020 በጋሮዌ ከተማ የገዛቸውን ቤቶች እና ሆቴሎች ለሙስሊም የእርዳታ ድርጅቶች ለግሶ በአሁኑ ወቅት በፑንትላንድ ከተማዎች እየተዘዋወረ ኃይማኖታዊ ትምህርት ይሰጣል።
በኢል ከተማ በባሕር ዘረፋ ምክንያት የአልኮል መጠጥ ተንሰራፍቷል። ብዙውን ጊዜ ከኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገባ ነው። ኦፒዮድስ የተባለው ዕፅም ገብቷል። ከሰዓታቸውን ጫት በመቃም ለሚያሳልፉ ወጣቶች ይህ ተጨማሪ አደንዛዥ ዕፅ ነው የሚል ስጋት አለ።
ምንም እንኳ የአካባቢው ሰው የባሕር ላይ ዘራፊዎችን ባይደግፍም የሌሎች ሀገራት መርከቦች በአካባቢው መንሰራፋታቸውን ግን አይወዱትም።
በቅርቡ ሶስት ዓሳ አጥማጆች በጥይት መገደላቸው ይህን ጥላቻ ከፍ አድርጎታል።
ላለፉት 40 ዓመታት ሎብስተር እና ሻርክ እያጠመደ ሚስቱና 12 ልጆቹን የሚያስተዳድረው አሊ ሙርሳል ሙሴ አጥማጆቹ ምናልባት የባሕር ላይ ዘራፊ መስለዋቸው ይሆናል የገደሏቸው ይላል።
በአንድ ወቅት ዓሳ ለማጥመድ በወጣበት የባሕር ዘራፊዎች ላይ ጥቃት ተከፍቶ ከሞት ለጥቂት እንደተረፈ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Lali / BBC
የ40 ዓመቷ ሃዋ መሀመድ ዙቤሪ ከ14 አመት በፊት ባሏ በጠፋበት ወቅት ተመሳሳይ እጣ ደርሶታል ብላ ታምናለች። ወቅቱ የባሕር ላይ ዝርፊያ የጦፈበት ነበር።
ሙሴ ከኢራን እና የመን የሚመጡት ሐሰተኛ የሶማሊያ የአጥማጅ ፈቃድ የያዙ መርከቦች ትልቅ ችግር እያመጡ ነው ይላል። ሐሰተኛ ፈቃድ የሚሰጧቸው ሰዎች በጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ያምናል።
ይህንን ቅሬታውን ይዞ ለአካባቢው ባለሥልጣናት ቢጠቁምም ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ይናገራል።
የፑንትላንድ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ካይዲድ ዲሪር በአካባቢው ሕጋዊ ያልሆኑ መርከቦች እንደሚንቀሳቀሱ አምነው ነገር ግን ለውጥ እየመጣ ነው ይላሉ።
'ግሎባል ኢኒሺዬቲቭ አጌንስት ትራንዚሽናል ኦርጋናይዝድ ክራይም' የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም በበኩሉ ፈቃድ የሌላቸው አሊያም በጉቦ ፈቃድ ያገኙ መርከቦች እንዳሉ ይገልፃል።
በሳተላይት ምስል የታገዘው የድርጅቱ መረጃ እንደሚያሳው አብዛኛዎቹ መርከቦች ከቻይና፣ ኢራን፣ የመን እና ደቡብ ምስራቅ እስያ የሚመጡ ናቸው።
ሞቃዲሹ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ እንደሚለው ሶማሊያ በባሕር ላይ ዝርፊያ ምክንያት በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች።
ፋራህ እና ዲሪዬ ዓሳ ማጥመድ ስለማያዋጣ ነው ቤተሰቦቻችንን ለመመገብ ወደ ባሕር ላይ ዝርፊያ የተሰማራነው ይላሉ።
የባሕር ላይ ዝርፊያ ትክክል እንዳልሆነ ያውቃሉ። ዲሪዬ የሚሠራውን ሥራ ለእናቱ ለመናገር እንደሚፈራ ይናገራል።
"ካወቀች በጣም ትበሳጫለች። እንደውም አሳልፋ ለፖሊስ ልትሰጠኝ ትችላለች።"












