"እንደምርጫችን ወይ ጥይት ወይ እስራት ይጠብቀናል"

ሞቃዲሹ

የፎቶው ባለመብት, Mohamed Gabobe

በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ የሚሠሩ ባለሱቆች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

መንግሥት ሱቃቸው በር ላይ የደኅንነት ካሜራ (ሲሲቲቪ) እንዲያስገጥሙ መመሪያ ሰጥቷል።

በከተማው ያለውን የኢስላሚስት ታጣቂ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነው የደኅንነት ካሜራው ያስፈለገው።

ሆኖም ግን ነጋዴዎቹ ካሜራ ካስገጠሙ በአል-ሻባብ ታጣቂዎች ዒላማ ተደርገው ስለሚገደሉ ይፈራሉ።

የደኅንነት ካሜራዎችን ካላስገጠሙ ደግሞ ፖሊስ ያስራቸዋል።

የ48 ዓመቱ ሐምዛ ኑር (ስሙ ተለውጧል) "በደኅንነት ካሜራዎቹ ምክንያት ሥራ ትቼ ቤት ዋልኩ" ይላል።

ቤቱ ፎቴ ላይ ከልጆቹ አንዱን አቅፎ ተቀምጧል።

ከመንግሥትም ሆነ ከታጣቂዎች በኩል የሚደርስበትን በመፍራት ሱቁን ሽጧል።

"በአንድ ወገን ካሜራ ስቀሉ እንባላለን። በሌላ ወገን ደግሞ ካሜራ አውርዱ እንባላለን። እንደ ምርጫችን ወይ ጥይት ወይ እስራት ይጠብቀናል" ይላል።

በደኅንነት ካሜራ ምክንያት እንገደላለን ብለው የሚፈሩት የሶማሊያ ነጋዴዎች

ነጋዴዎች በራሳቸው ወጪ የደኅንነት ካሜራ እንዲያስገጥሙ መንግሥት መመሪያ ያወጣው አምና ነው።

ይህም የአል-ሻባብን ጥቃት ለመመከት በሚል ነው።

የሞቃዲሾ ምክትል ከንቲባ መሐመድ አሕመድ ዲሪዬ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የደኅንነት ካሜራ እንዲገጠም መወሰኑ ውጤት አምጥቷል።

"በሞቃዲሾ በወር ውስጥ አራት ወይም አምስት የቦምብ ጥቃት ይደርስ ነበር። አሁን ግን እንደዚያ አይደለም" ይላሉ።

ነዋሪዎች በቤታቸውና መኖሪያ ሕንጻቸው በር ላይ ካሜራ እንዲያስገጥሙም መንግሥት መመሪያ ሰጥቷል።

አል-ሻባብ ጦርነቱን በየቤታቸው እንዳይወስደው ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ ገብተዋል።

አል-ሻባብ እአአ ካለፈው ጥቅምት 2024 ጀምሮ 10 ጥቃቶች አድርሶ 4 ነጋዴዎችን ገድሏል።

ግጭትና ጥቃትን የሚከታተለው ተቋም 'አርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኢቨንት ዳታ' (አክሌድ) እንዳለው፣ ግድያዎቹ የተፈጸሙት ደኅንነት ካሜራ ከማስገጠም ጋር በተያያዘ ነው።

የመንግሥት ዓላማ የአል-ሻባብን የገንዘብ ምንጭ መቁረጥ ነው።

አክሌድ ባወጣው መረጃ መሠረት ግን የመንግሥት ውሳኔ ታጣዊዎቹ የበቀል ጥቃት እንዲፈጽሙ ምክንያት ሆኗል።

"በሞቃዲሾ ብዙ ዋነኛ መገበያያ ሱቆች ለቀናት እንዲዘጉ አስገድዷል" ብሏል ተቋሙ።

የአል-ሻባብ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐምዛ ኑር እንደሚለው፣ መጀመሪያ ላይ የመንግሥትን መመሪያ ችላ ብሎ ነበር።

ሆኖም ግን የፀጥታ ኃይሎች አስገድደውት ካሜራ አስገጠመ።

"ድሃ ነኝ፣ በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ መግባት አልፈልግም አልኳቸው። ተበሳጩና ያስፈራሩኝ ጀመር። ሕይወቴን እንደሚያመሳቅሉት አስፈራሩኝ" ይላል።

የደኅንነት ካሜራውን ሲያስገጥም ከማይታወቁ ቁጥሮች የስልክ ጥሪ ይደርሰው እንደጀመረ ይናገራል።

"ስልኩ ሲጠራ ሰውነቴ መብረክረክ ጀመረ። ማን እንደደወለ አወቅኩ" ይላል ነጋዴው።

የአል-ሻባብ ታጣቂዎች በስለላ መረጃ ስለሚያገኙ ስለ ሐምዛ ካሜራ ማስገጠምም እንዳወቁ ይናገራል።

ሐምዛ ስልክ ቁጥሩን ሲቀይር አንድ ወጣት ሱቁ ሄዶ በሽጉጥ አስፈራራው።

"ካናቴራውን ከፍ አድርጎ አሳየኝ። ወገቡ ላይ ሽጉጥ ታጥቋል። የድሮ ሲም ካርዴን በስልኬ እንዳስገባ ነገረኝ" ሲል የተፈጠረውን ይገልጻል።

የድሮ ሲም ካርዱን እንዳስገባ ስልክ ተደወለለት። የማይታወቅ ቁጥር ነበር።

"የደወለው ሰው 'የመንግሥትን ጥያቄ ከኛ ጥያቄ በላይ አድርገህ ነው የምትወስደው' አለኝ" ሲል ይገልጻል።

"ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ። ሽጉጥ የታጠቀው ወጣት እዛው ቆሞ ነበር። ስልኩን ስዘጋው ተኩሶ እንደሚገድለኝ አሰብኩ። በለሆሳስ ፀለይኩ። ከዚያም ስልኩን ስዘጋው ወጣቱ ከሱቄ ወጣ።"

ሁለት ነጋዴዎች ከተገደሉ በኋላ ሱቁን ለመሸጥ ወሰነ።

"ከሰው ሕይወት በላይ ዋጋ ያለው የለም" ይላል ሐምዛ ኑር።

የመንግሥት መመሪያ የሚተቸው ነጋዴው "ሰዎች ኑሯቸውን መግፋት ነው የሚፈልጉት። ግን መንግሥት ሊያሸንፈው ካልቻለ ኃይል ጋር ጦርነት እንዲገቡ እየተደረጉ ነው። እንደ ሲቪሎች ምን እንደሚሰማን አስቡት እስኪ" ሲልም ያክላል።

የሞቃዲሾ ምክትል ከንቲባ ግን ነጋዴዎች የደኅንነት ካሜራ እንዲያስገጥሙ መገደዳቸውን ያስተባብላሉ። ሱቆችም አልተዘጉም ይላሉ።

አንዳንድ ነጋዴዎች እንደሚፈሩና መንግሥት ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ቃል እንደገባላቸው ተናግረዋል።

"ከተማው ሰላም ነው። ንግዱም ቀጥሏል" ይላሉ ምክትል ከንቲባው።

አይሶ መሐመድ ዋርሳሜ እንደምትለው ግን የፊት ጭምብል ያጠለቁ ታጣቂዎች የ40 ዓመት ወንድሟ ዳሂድ መሐመድ ዋርሳሜን ገድለውታል።

በያቅሺድ ጎዳና በሚገኘው ሱቁ ሳለ ነው ተኩሰው የገደሉት።

ዳሂር ከመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በደረሰበት ጫና ያለፈው ጥቅምት ነበር በሱቁ በር የደኅንነት ካሜራ ያስገጠመው።

"ስድስት ልጆች ጥሎ ነው የሞተው። የመጨረሻ ልጁ ገና አራት ወሯ ነው" ትላለች።

የ33 ዓመቱ ኢስማኤል ሀሺ (ስሙ ተቀይሯል) እንደሚለው ከማያውቀው ቁጥር እየተደወለ ዛቻ ሲደርሰው ሱቁን ለመዝጋት ተገዷል።

የአል-ሻባብ ታጣቂዎች እንደደወሉለት ያምናል።

"ስሜንና ሌላም ስለእኔ መረጃ ነበራቸው" ይላል።

ፖሊስ ለኢስማኤል ደውሎ ሱቁን እንዲከፍት አዘዘው። ሱቁን ሳይከፍት ሲቀር ለጥቂት ቀናት ታስሮ ተፈታ።

አሁን ሱቁን መልሶ ከፍቷል።

"መንግሥት ባዘዘው መሠረት የደኅንነት ካሜራው ሱቄ በር ላይ ይገኛል። አንድ ሰው ሊገድለኝ ቢፈልግ መንግሥት እንደማያድነኝ አውቃለሁ። ሁሌም ሱቅ ውስጥ ሰው ሲገባ ሊገድለኝ የመጣ ስለሚመስለኝ እፈራለሁ።"

የ39 ዓመቱ ሲዶው አብዱላህ መሐመድ (ስሉ ተቀይሯል) በዋጂር ጎዳና ባለው ሱቁ የደኅንነት ካሜራ ሳያስገጥም በመቅረቱ መታሰሩን ይናገራል።

በዛው ጎዳና ላይ 14 ሰዎች መታሰራውንም ያክላል።

"ወደ ዋዳጂር ግዛት ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን። ለሰዓታት ተይዘን ነበር። አንድ የመንግሥት መታወቂያ ያለው ሰው መጥቶ አስለቀቀን" ይላል።

እሱና ሌሎችም ነጋዴዎች ከተለቀቁ በኋላ ካሜራ ቢያስገጥሙም በፍርሃት ተሸብበዋል።

"እኛ ሲቪሎች ነን። ግን ካሜራ እንድንገዛ እንገደዳለን። ቤታችን በር ላይ ካሜራ ገጥመን ለአል-ሻባብ ጥቃት እንድንጋለጥ እንገደዳለን። መንግሥት የእኛን ድጋፍ ማግኘት የሚችለው በዚህ መንገድ ይመስለዋል?"