አወዛጋቢውን የኬንያ መንግሥት የአየር ማረፊያ ስምምነትን ያጋለጠው ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኬንያዊው የቢዝነስ ተማሪ ኔልሰን አሜኒያ እንደ ጀግና እየተወደሰ ይገኛል።
በተለይም መንግሥታቸው ከግል ኩባንያዎች ጋር በሚያደርጋቸው ስምምነቶችን ግልጽነት በተሞላ መልኩ እንዲያደርግ ዘመቻ በሚያካሂዱት ዘንድ።
የቅርብ ጊዜ የኬንያ ታሪክ በሙስና በተዘፈቁ ግዙፍ የኩባንያ ውሎች የተሞላ ነው።
ከሕዝብ ዓይን በተደበቀ መልኩ ውሎች እንዳይፈረሙ የሚከለክሉ ሕጎች አገሪቷ ብታስቀምጥም አሁንም እየተፈጸሙ ስለመሆኑ ጥርጣሬዎች አሉ።
የ30 ዓመቱ ኔልሰን በፈረንሳይ በቢዝነስ ትምህርት ማስተርሱን እየተማረ ይገኛል።
ኔልሰን በሐምሌ ወር በኬንያ መንግሥት እና የህንዱ አለም አቀፍ ኩባንያ አዳኒ መካከል ሊደረግ የታቀደ ነው ያለውን ሚስጥራዊ ስምምነት በማኅበራዊ ሚዲያ አጋራ።
ስምምነቱ የኬንያውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጆሞ ኬንያታ አስተዳደርና እድሳትን የተመለከተ ነው።
ስምምነቱ አዳኒ ግሩፕ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ 2 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ያፈሳል፤ በምላሹም አዳኒ ዓለም አቀፍ ማረፊያውን ለ30 ዓመታት ያህል በሊዝ ተቆጣጥሮ ያስተዳድራል የሚል ነው።
በዚህም ዕቅድ መሰረት በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን አዲስ ማኮብኮቢያ እና የተሻሻለ የመንገደኞች ተርሚናል ግንባታን ያካተተ ነው።
"መጀመሪያ ሰነዱን ሳገኘው የተሰማኝ ስሜት ሌላ የመንግሥት ስምምነት የሚል ነበር። ክብደቱና አሳሳቢነቱ አልገባኝም ነበር" ይላል በጸረ- ሙስና አክቲቪስትነቱ ታዋቂ የሆነው ኔልሰን
ሰነዶቹን በጥልቀት ሲገመግም ይህ ስምምነት የሚፈጸም ከሆነ "የኬንያን ምጣኔ ኃብት በመጉዳት" የህንዱ ዓለም አቀፍ ኩባንያ እንደሚጠቀም ተሰማው።
ለኔልሰን ይህ ስምምነት ለአገሪቱ ፍትሃዊ እንዳልሆነ ታየው።
ኔልሰን በነዚህ ሰነዶች ትክክለኛነት ጥርጣሬ አልነበረውም፤ ምክንያቱም "እነዚህን ሰነዶች የሰጡኝ ግለሰቦች ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዳመጡት አውቃለሁ" ይላል።
ከኬንያ መንግሥት ጋር ስምምነት ውስጥ የገባው የአዳኒ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሰረተ ልማት፣ በማዕድን እና በኢነርጂ ፕሮጀክቶች ላይ ይሳተፋል።
ኩባንያው በእስራኤል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ፈረንሳይ፣ ታንዛንያ፣ አውስትራሊያ እና ግሪክ ባሉ አገሮች ተሰማርቷል።
የኩባንያው መስራች ጋውታም አዳኒ በህንድ ምጣኔ ኃብት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እና የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የቅርብ አጋር ነው።
ሰነዱ በተጨማሪም አገሪቷ ኢንቨስትመንቱን መመለስ ካልቻለች ኩባንያውን የመክፈል ግዴታን የጫነባት እንደሆነ ኔልሰን መረዳቱን ይገልጻል።
"ይህ በፕሬዚዳንቱ አመራር፣ በኬንያ አየር ማረፊያ ባለስልጣናት፣ በሚኒስትሩ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ የእምነት ጥሰት ነው። ሁሉም ሕዝቡን ከድተዋል" ሲል ኔልሰን ይናገራል።
በእጁ ላይ እነዚህን ማስረጃዎች ቢይዝም መጀመሪያ ላይ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለበት ለመወሰን ከብዶት ነበር።
ከኬንያ ርቆ ፈረንሳይ መሆኑ የተሻለ ቦታ ቢያስቀምጠውም ደህንነቱ ስጋት ውስጥ እንደሚገባ አላጣውም። በኬንያ የጸረ- ሙስና አክቲቪስቶች ዒላማ የሚሆኑ ሲሆን አንዳንዶችም ተገድለዋል።
"ትንሽ ፈርቼ ነበር። ምን እንደሚፈጠር አላወቅኩም ነበር። ሙያዬን፣ ትምህርቴን እንዲሁም ሕይወቴን አደጋ ላይ እንደምጥል አውቃለሁ። እናም ለምን እዚህ አደጋ ውስጥ እወድቃለሁ?" ብሎ እንደጠየቀ ይገልጻል።
በመጨረሻም ዝም ማለት አማራጭ እንዳልሆነ ተሰማው።
"ታውቃላችሁ፣ ረጅም ዕድሜ የሚኖሩት ፈሪዎች ብቻ ናቸው" ይላል።
ኔልሰን የተላከለትን ሰነድ ለሳምንታት ካነበበ በኋላ ሐምሌ ወር ላይ ኤክስ ገጹ ላይ አጋራው።
ይህ የሾለከው ሰነድ ወዲያውኑ ነበር ከፍተኛ ቁጣ በኬንያውያን ዘንድ የፈጠረው።
የጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ ማረፊያ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ አስነሱ። ስምምነቱ እንዲሰረዝ ጠየቁ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ለአገሬ የምወጣው ግዴታ እንደሆነ ተሰማኝ። ብርቅም ለአገሬ ግዴታ አለብኝ። የተሻለች ኬንያን ማየት እፈልጋለሁ። አገሬ ያደገች፣ ኢንዱስትሪ የተስፋፋባት እና ሙስና የሌለባት ሆና ማየት ምኞቴ ነው" ይላል።
ለኔልሰን ስጋት ያሳደረበት እነዚህ ያልተለመዱ ውሎች ግልጽነት በሌለው መልኩ መደረሳቸው ብቻ ሳይሆን የኬንያ ሕጎች ችላ መባላቸው እንደሆነ ይናገራል።
"ባለስልጣናቱ ስለ ኩባንያው ተገቢውን ማጣራት አላደረጉም። የስምምነቱን ትክክለኛ ሂደት አልተከተሉም" ይላል።
አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት የግብር ከፋዩን ሕዝብ ገንዘብ አላግባብ እንዳይውሉ የሚከላከለውን ሕጋዊ መስፈርቶችን እንዲሁም ሕዝባዊ ምክክሮች ለመተላለፍ ሞክረዋል ሲል ኔልሰን ይከሳል።
የኬንያ አየር ማረፊያዎች ባለስልጣን በሚያዝያ ወር ባወጣው ሪፖርቱ በቀረበው ስምምነት ላይ ባለድርሻ አካላትን የማማከር ዕቅድ እንደሌለ አመልክቷል።
"ይህንን ስምምነት ሐምሌ ላይ ካጋለጥኩ በኋላ የማስመሰል ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲሁም የኬንያ አየር ማረፊያዎች ባለስልጣናትን ጠርተው የባለድርሻ አካላት ስብሰባ ማድረግ ጀመሩ" ብሏል።
የተለያዩ የመንግሥት ባለስልጣናት በስምምነት ሂደቱ ውስጥ ሙስና ተፈጽሟል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገው ከአዳኒ ግሩፕ ጋር ሌላ የሚሊዮን ዶላሮች ስምምነት ተፈራረሙ። ይህኛው ስምምነት የኤሌክትሪክ መስመሮች ግንባታ ነው።
ኔልሰን ያቀረባቸው ክሶች "መሰረተ ቢስ" እንዲሁም "በተንኮል የተሞሉ" ናቸው ሲል አዳኒ አጣጥሏል።
ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ዕቅዱ የቀረበው የኬንያን የግልና የመንግሥት አጋርነት ሕጎችን ተከትሎ ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አውሮፕላን ማረፊያ ለማቋቋም እና በርካታ አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር የኬንያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳግ ያለመ ነው" ብለዋል።
አዳኒ የቀረቡበትን የኬንያ ሕጎችን ጥሷል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጓል።
"የምንሰራው እያንዳንዱ ፕሮጀክት ግልጽነት በተሞላው መልኩ እና የምንቀሳቀስባቸውን አገራት ሕጎች አክብሬ ነው" ሲል አዳኒ መግለጫ አውጥቷል።
ሆኖም የኬንያ መንግሥት ከአዳኒ ጋር የገባውን ስምምነት ለመሰረዝ ተገደደ።
የመንግሥትን ሃሳብ ያስቀየረው ኔልሰን አሾልኮ ያወጣው ሰነድ አልነበረም።
የአሜሪካ መንግሥት ጉታም አዳኒን ከኃይል አቅርቦት ጋር በተገናኘ በ250 ሚሊዮን ዶላር የጉቦ ክስ ሲመሰርት ነው የኬንያ ባለስልጣናት ስምምነቱን የሰረዙት።
የአዳኒ ግሩፕ ተወካዮች የአሜሪካን አቃቤ ሕግ ውንጀላ ውድቅ በማድረግ "መሰረተ ቢስ" ሲሉ አጣጥለውታል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ባለፈው ወር በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ሁለቱም የአዳኒ ስምምነቶች ተሰርዘዋል ብለዋል።
"በሙስና ላይ የማያጠራጥር እና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ሲቀርብ ቆራጥ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ አልልም" ሲሉም ነው የተናገሩት።
ውሳኔውን ኬንያውያንን ያስደሰተ ነበር።
"ይህ ዜና ሲነገር ክፍል ውስጥ ነበርኩ። ማመን አልቻልኩም" ይላል ኔልሰን።
አክሎም "እንባዬ መጣ። በጣም ደስተኛ ነበርኩ" ብሏል።
ኔልሰን ራሱን እንደ ጀግና ባይመለከትም በርካቶች የአድናቆት መልዕክቶቻቸውን አጉርፈውለታል።
ኔልሰንም አሁን ታዋቂ የሆነው 'አዲዮስ አዳኒ' (ደህና ሁን አዳኒ) በሚል መልዕክቱን አሰፈረ።
"ታሪካዊ ነበር። ያደረግኩት ነገር በሙሉ በመጨረሻ ፍሬያማ ሆነ" ብሏል።
ይህ የድል ስሜት ግን ከወራት ትግል እና ጫና በኋላ የተገኘ ነው።
ኔልሰን የአውሮፕላን ማረፊያውን ስምምነት ካጋለጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአዳኒ ግሩፕ ተወካዮች እና በኬንያ ፖለቲከኛ ስም የማጥፋት ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል። ይህም ራሱን ጥርጣሬ ውስጥ የከተተው እንደሆነ ይናገራል።
"አንዳንድ ከመንግሥት የተላኩ አካላት ያናግሩኝ ነበር። ገንዘብ ለመክፈልም ዝግጁ ነበሩ። 'ገንዘብህን ተቀበልና ከመንግሥት ጋር የሚደረገውን ትግል አቁም' ያሉኝ ነበሩ" ሲል ያስታውሳል።
"ይህንን ብተወው በሕይወቴ ትልቁ የፈጸምኩት ስህተት ይሆን ነበር። ለኬንያ ሕዝብ ክህደት ነው" ይላል።
ፕሬዚዳንት ሩቶ ስምምነቱን ከሰረዙ በኋላ ኬንያውን ይህንን እና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን ለምን እንደተቃወሙ ጠይቀዋል። አየር ማረፊያውን ለማሻሻል መንገድ እፈልጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።
"የአየር ማረፊያውን ማሸሻያ ያስቆሙት ጀግኖች ናቸው ሲሉ ሰምቻለሁ። ጀግኖች? ግንባታን በማስቆም ምን ታገኛላችሁ?"
ሲሉ የጠየቁት ሩቶ አክለውም "እንዴት እንደሚገነባ ሃሳቡም የላችሁም። ይህንን የሚቃወሙም አውሮፕላን ማረፊያን በእግራቸው ረግጠው የማያውቁ ናቸው። መቃወም ብቻ ነው የምትፈልጉት" ሲሉ ወቅሰዋል።
በስም ማጥፋት ክሶች የተመሰረቱበት ኔልሰን የፍርድ ቤት ሂደቱን ለመሸፈን ገንዘብ እያሰባሰበ የሚገኝ ሲሆን ወደ አገሩ የመመለስ ዕጣፈንታውን በተመለከተ እርግጠኛ አይደለም።
"ከታማኝ የስለላ ኤጀንሲዎች እና ግለሰቦች ወደ አገር እንዳልመለስ ማስፈራሪያዎች እና ማስጠንቀቂያዎች ደርሰውኛል" ይላል።
የከፈለው ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም ኔልሰን በድጋሚ አደርገዋለሁ ይላል።
"ማንም ሰው እንዲያድነን መጠበቅ አያስፈልገንም" ብሏል።












