የካናዳ ቪዛ እናስጨርሳለን በሚሉ ኤጀንቶች የተጭበረበሩ ሰዎች ምስክርነት

የካናዳ ሰንደቅ አላማ

ኬንያዊው ሄነሪ ካቱሪማ ወደ ካናዳ ለመሄድ ሲወስን ያሰበው በአዲስ አገር አዲስ ሥራ እና አዲስ ሕይወት እንደሚጠብቀው ነበር።

“ትልቅ ተስፋ ነበረኝ። እዚያ ሄጄ ቶሎ ሥራ እንደምጀምር ስላሰብኩ ሕይወቴ በፍጥነት ይለወጣል ብዬ ነበር ያሰብኩት” ይላል።

ሄነሪ የመንግሥት የምርመራ ሠራተኛ ነበር። በሥራው ምክንያት ኬንያ ውስጥ ኑሮውን ቢቀጥል ሕይወቱ ለአደጋ እንደሚጋለጥ ያምን ነበር።

“የት ሄጄ ጥገኝነት እንደምጠይቅ ማሰብ ጀመርኩ” ይላል።

ከኬንያ በፍጥነት ለመውጣት ሲል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወዳገኘው ስካይፒንስ የተባለ የጉዞ ወኪል አመራ።

“ትክክለኛ ሥራ የሚሠሩ ይመስሉ ነበር” ይላል ስለ ጉዞ ወኪሉ ሲገልጽ።

እአአ በሚያዝያ 2023 የጉዞ ወኪሉ በካናዳ ያሉ ሥራዎች እና ስንት እንደሚከፍሉ ለሄነሪ አሳየ።

“ጥሩ ዕድሎች እና ጥሩ ገንዘብ ነበር” ይላል ሄነሪ።

ለስካይፒንስ ሰነዶቹን አስረክቦ የቪዛ ሂደቱን ለማስጀመር 930 ዶላር እና ለተጨማሪ የቪዛ ወጪዎች 386 ዶላር ከፈለ።

ኤጀንሲው በስሙ አካውንት ቢከፍትም አካውንቱን መመልከት እንዳልተፈቀደለት ይናገራል።

ሌላ ወደ ስካይፒንስ ያቀናችው ኬንያዊት ሜሪ ናት። ሜሪ (ስሟ ተለውጧል) ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነበር የጉዞ ወኪሉን ያገኘችው።

የመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ነርስ ናት። ዓለም አቀፍ የነርሶች ፈተና ከመውሰድ ይልቅ በኤጀንሲ በኩል ወደ ካናዳ መጓዝ ቀላል እንደሆነ አምና ነው ሂደቱን የጀመረችው።

“እንክብካቤ የመስጠት ሥራ እንደማገኝ ነገሩኝ። በዚህ ሥራ አማካይነት ሄጄ በሙያዬ ለመቀጠል ትምህርት እንደምጀምር አስቤ ነበር” ትላለች።

በኤጀንሲው የተጠየቀችውን ገንዘብ መክፈል ስላልቻለች ብድር ወሰደች።

“ውል ተፈራረምን። 150 ዶላር ለቪዛ እና 930 ዶላር ደግሞ ለኤጀንሲው ክፍያ ሰጠሁ” ትላለች ነርሷ።

ልክ እንደ ሄነሪ ሁሉ ሜሪም በስሟ የተከፈተውን የካናዳ ቪዛ መጠየቂያ አካውንት እንድትመለከት አልተፈቀደላትም።

ሄነሪ ካቱሪማ

የፎቶው ባለመብት, Henry Kathurima

የምስሉ መግለጫ, ሄነሪ ካቱሪማ

ለቪዛ ለማመልከት አማካሪም ሆነ ኤጀንሲ አያስፈልግም

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሄነሪ እና ሜሪ ለቪዛ ቅድመ ክፍያ መጠየቃቸው እና አካውንታቸውን እንዲያዩ አለመፈቀዱ ኤጀንሲዎቹ ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ ማድረግ እንደነበረበት በኬንያ የሚገኘው የካናዳ ከፍተኛ ኮሚሽን ይገልጻል።

በናይሮቢ የሚገኘው የካናዳ የስደተኞች፣ ዜጎች እና ቪዛ ክፍል የፕሮግራም ኃላፊ ማሪፒር ኮቴ “ማንኛውም ሰው በቀጥታ አካውንት መክፈት እና አካውንቱን መመልከት ይችላል። አካውንቱን የሚከፍት እና የሚከታተል አማካሪ ወይም ኤጀንት መቅጠር አያስፈልግም” ትላለች።

ኤጀንቶች ወይም ወኪሎች በቪዛ ጠያቂዎች ስም ማመልከት እንደሌባቸው የካናዳ ከፍተኛ ኮሚሽን ያስጠነቅቃል።

“ቪዛ የሚጠይቁት ሰዎች በአካውንታቸው ላይ ለሚያስገቡት መረጃ ኃላፊነት ይወስዳሉ። ሐሰተኛ መረጃ ቢኖር የቪዛ ጠያቂዎቹ እንጂ የኤጀንቶቹ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ቪዛ የሚጠይቁ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ ማረም አለባቸው። ኤጀንቶች ብዙ የማጭበርበር ሥራ እየሠሩ ነው” ስትል ማሪፒር ኮቴ ታክላለች።

ሄነሪ እንደሚለው ኤጀንሲው በሐሰተኛ መንገድ 40,000 የካናዳ ዶላር ባንኩ ውስጥ እንዳለ የሚጠቁም ሰነድ አዘጋጅቷል። እንደዚህ ያሉ ማጭበርበሮች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ።

የካናዳ መንግሥት ሄነሪን ቪዛ ከመከልከሉም በላይ ለአምስት ዓመት ካናዳ እንዳይገባ ዕገዳ ተጥሎበታል።

አውስትራሊያ፣ ኒው ዚላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ እንዳይገባም ታግዷል።

“ለመዋሸት አላሰብኩም ነበር። እየተሳሳትኩ ወይም እያጭበረበርኩ መሆኑንም አላወቅኩም” ይላል።

ሜሪ ደግሞ “ስሜ ላይ የአያቴን ስም ጨምረው የቪዛ ማመልከቻውን አስገቡ። እናስተካክላለን ቢሉም አላስተካከሉትም” ትላለች።

“ያስገቡት የባንክ ሰነድም እኔ የሰጠኋቸው አይደለም። እንዴት እንዳገኙ ባላውቅም የእኔ ያልሆነ እና የተሳሳተ የባንክ ሰነድ አስገቡ” ስትልም ታክላለች።

የቪዛ ጥያቄዋ አወንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጋ ስትጠባበቅ ነበር።

“ስካይፒንስ በትዕግስት ጠብቂ አሉኝ። ከኤምባሲው ኢሜይል ይደርሰኛል ብዬ ብጠብቅም ምንም አልመጣም” ትላለች።

ከአንድ ዓመት በኋላ ሜሪ እንደተጭበረበረች መጠርጠር ጀመረች።

ለስካይፒንስ ጥያቄ ስታቀርብ የቪዛ ጥያቄዋ ውድቅ መደረጉ ተነገራት።

የሄነሪ እና ሜሪን ቅሬታ ይዞ ቢቢሲ ከስካይፒንስ የጉዞ ወኪል ኃላፊ ዴኒስ ኪሞቶ ምላሽ ጠይቋል። ዴኒስ ድርጅታቸው ላይ የቀረበውን ክስ አስተባብሏል።

ተቋሙ የሠራተኞች ምልመላ እንደማያደርግ እና በብሔራዊ ደረጃ እንዳልተመዘገበ ገልጾ፣ ሥራቸው የጉዞ ወኪልነት እና አስጎብኚነት እንደሆነ እንዲሁም በአገሪቱ ቱሪዝም ቢሮ መመዝገባቸውን ተናግሯል።

የሄነሪን ጉዳይ በተመለከተ “ስለ ጉዳዩ አውቃለሁ። ማንኛውም ቅሬታ ካለው ኤጀንሲያችንን በቀጥታ ማነጋገር ይችላል። እኛ በቀጥታ ከደንበኞቻችን ጋር ነው የምናወራው። ማንኛውም የሚፈልጉትን መረጃ ሊጠይቁን ይችላሉ” ሲል ዴኒስ ምላሽ ሰጥቷል።

የሥራ ቪዛ መጠየቃቸውን እንዲሁም ለቪዛ ሂደት ሐሰተኛ ሰነድ ማስገባታቸውን አስተባብሏል።

የቪዛ መጠየቂያ ሰነድ

የማኅበራዊ ሚዲያ ማስታወቂያዎች

ሄነሪ እና ሜሪ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሥራቸውን በሚያስተዋውቁ ኤጀንሲዎች ገንዘብ የተጭበረበሩ ብቸኛ ሰዎች አይደሉም።

ቢቢሲ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን አግኝቷል። ወደ ካናዳ መጓዝ ለሚፈልጉ ኬንያውያን ሁነኛ አማራጭ እንደሆኑ ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ።

እነዚህ ገጾች በዋናነት በቲክቶክ፣ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሥራ ፈላጊዎችን በዋናነት ያጠምዳሉ።

የካናዳ መንግሥት የስደተኞች፣ ዜጎች እና ቪዛ ክፍል እንደሚለው፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት አጭበርባሪ የቪዛ ኤጀንቶች ቁጥር ጨምሯል።

በናይጄሪያ፣ በታንዛንያ እና በኡጋንዳም ቁጥራቸው ተበራክቷል።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 29,577 የሚጠጉ የካናዳ ጊዜያዊ የመኖሪያ ቪዛ ጥያቄዎች በኬንያውያን ቀርበው 47 በመቶ የሚጠጉት ቪዛ ሲሰጣቸው 53 በመቶ ያህሉ የቪዛ ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጓል።

የቪዛ ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገባቸው መካከል 14 በመቶ የሚሆኑት ተቀባይነት የሌለው ወይም ሐሰተኛ ይዘት ያለው መረጃ አስገብተዋል።

በ2024 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የቪዛ ጥያቄ ተቀባይነት በ8 በመቶ ቀንሷል። 26 በመቶ የካናዳ ጊዜያዊ የመኖሪያ ቪዛ ጥያቄዎች ተቀባይነት የሌለው ወይም ሐሰተኛ ይዘት ያለው መረጃ በማስገባት ውድቅ ተደርገዋል።

ካለፈው ዓመት ቁጥሩ በእጥፍ ጨምሯል።

ችግሩ የቪዛ መከልከል ብቻ አይደለም።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባለፈው ዓመት የተለቀቁ ቪድዮዎች ኬንያውያን መግቢያ አጥተው በካናዳ ጎዳናዎች ላይ ታይተዋል።

አብዛኞቹ ሥራ እናገኛለን ብለው በጊዜያዊ የቱሪስት ቪዛ ካናዳ የገቡ ናቸው።

ሥራ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ የጥገኝነት ጥያቄ ከማቅረብ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም።

የናይሮቢ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ቤንሰን ካስዬኪ እንዳሉት፣ የሥራ ቅጥር እናስገኛለን የሚሉ ሐሰተኛ ኤጀንሲዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው።

“263 ኤጀንሲዎችን የተመለከቱ 615 ቅሬታዎች ደርሰውናል። ምርመራ እያደረግን ነው። እንደ ካናዳ ያሉ አገራት እንወስዳችኋለን በሚል ገንዘባቸውን እንደተጭበረበሩ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ጠቁመዋል። እነዚህ ሰዎች የቪዛ መጠየቂያ ሰነድ በኤጀንሲዎቹ አልገባላቸውም፣ ካናዳም አልሄዱም” ብለዋል።

ከእነዚህ ኤጀንሲዎች መካከል የተወሰኑት ሥራ ማቆማቸው ወይም ስማቸውን ለውጠው ወደ ገበያው በድጋሚ መግባታቸው የምርመራ ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል።

የተጭበረበረው ገንዘብ

ሄነሪ እና ሜሪ ለፖሊስ በተደጋጋሚ ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ከከፈሉት ገንዘብ የተወሰነውን መልሰው አግኝተዋል።

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገረው ፖል (እውነተኛ ስሙ አይደለም) ገንዘቡ አልተመለሰለትም።

ፖል 37 ዓመቱ ነው። የረዥም ርቀት የጭነት መኪና በማሽከርከር ጥሩ ገቢ ያገኝ ነበር።

ነገር ግን አዲስ የባቡር መስመር ሲዘረጋ ሥራው ተስተጓጎለ።

“ሥራዬን መቀየር እንደሌለብኝ ጓደኛዬ ነገረኝ። ካናዳ እና ኢራቅ የሠራተኛ እጥረት ስላለ ከሁለቱ አገራት ወደ አንዱ ሄጄ መሥራት እንደምችል ነገረኝ። ብዙዎች የጭነት መኪና አሽከርካሪ ይፈልጋሉ አለኝ። ከዚያም ወደ ታዋቂ ኤጀንሲ መራኝ” ይላል።

ኤጀንሲው የስደተኞች አማካሪ እንደሆነ በመግለጽ ራሱን ያስተዋውቃል።

የጭነት መኪና በማሽከርከር በወር ውስጥ 4,000 እስከ 7,000 የካናዳ ዶላር ማግኘት እንደሚቻል ኤጀንሲው ለፖል ገልጿል።

ለኤጀንሲው ክፍያ ለመፈጸም ፖል ያለውን ሃብት መሸጥ ነበረበት።

“ባንክ ውስጥ ምንም ገንዘብ አልነበረኝም። ያለኝን መሬት መሸጥ ነበረብኝ” ይላል።

ለኤጀንሲው ለአውሮፕላን ትኬት ክፍያ፣ ለቪዛ እና ካናዳ ማረፊያ ለማመቻቸት 5,454 ዶላር ከፍሏል።

ከኤጀንሲው ጋር ውል አልተፈራረመም። አካውንቱን እንዲመለከት ፈቃድ አልተሰጠውም። ሙሉ ሂደቱን የሚቆጣጠረው ኤጀንሲው ነበር።

“ቪዛ ሲጠየቅ የባንክ ሒሳብ ማሳየት እና ባለትዳር መሆን አለመሆንን መግለጽ እንደሚያስፈልግ ተረዳሁ። ነገር ግን ኤጀንሲው እነዚህን መረጃዎች አልጠየቀኝም” ይላል ፖል።

በስተመጨረሻ ፖል ቪዛ ተሰጠውና ለጉዞ መዘጋጀት ጀመረ።

ቤተሰቡን ተሰናብቶ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ አቀና።

አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ግን በቪዛ መጠየቂያ ሂደቱ ላይ በተገኘ ስህተት ምክንያት የካናዳ መንግሥት ቪዛውን እንዳገደው ተገለጸለት።

ኤጀንሲው ገንዘቡን እንዲመልስለት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም አልተሳካም። ጉዳዩንም ለፖሊስ አስታወቀ።

ጉዳዩ በፖሊስ እየተመረመረ ቢሆንም እስካሁን ፖል የሚጠብቀውን ፍትሕ አላገኘም።

“ሥራ እንደማገኝ እና አዲስ ሕይወት እንደምጀምር ቃል ተገብቶልኝ ነበር። አሁን ግን የተገባልኝ ቃል እውን ሳይሆን፣ ባዶ የባንክ አካውንት ይዤ ቁጭ ብያለሁ” ይላል።